Tuesday, January 24, 2017

ከየት እንደመጣ ማብራሪያ የማይሰጥበት ሀብት የፊት ለፊት ማስረጃ ነው!! ፎቆቹ በአደባባይ ይናገራሉ፡፡ ቤቶቹ መሬቶቹ በይፋ ያሳብቃሉ፡፡


   

ማር መላስ የማይፈልግ የለም፡፡ ያም ሆኖ ግን አንዱ አንዱን እየጠለፈ፣ አንዱ የአንዱን እየዘረፈ ወይም ከመንግስት እየመዘበረ፣ የሚኖርበትን ሥርዓት ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ እጅግ የተወሳሰበና የተቆላለፈው የሙስና መረብ፣ በተለይ ከፖለቲካው ጋር ሲተበተብ ለያዥ ለገራዥ ማስቸገሩን እያየነው ነው!! የሙስናን አሻጥር ለመረዳት በተለይ ዛሬ ዓይንን ማሸት አይፈልግም፡፡ ምን ያህል የሀገርና የህዝብ ገንዘብ ለግል ጥቅም እየዋለ መሆኑን፣ የተጠረጠሩ የሙስና ባለ እጆችን ማስተዋል ብቻ በቂ ነው፡፡ ሆን ተብሎም ሆነ ለጥንቃቄ ተብሎ አሊያም በስህተት የሙስና ክስ ዘግይቷል ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ አሁንም መፍጠን አለበት፡፡ የሙስና ዘዴው በአብዛኛው የሚታወቅ ነው፡፡ በዘመኑ ቋንቋ የተበላ ዕቁብ ነው
‹‹እኔም ሌባ፣ አንተም ሌባ
ምን ያጣላናል፤ በሰው ገለባ!››
የሚባልበት ያፈጠጠ፣ ያገጠጠ ጊዜ ነው፡፡ አለቃና ምንዝር ሳንለይ የሚሠርቁ እጆች መያዝ አለባቸው፡፡ ቁጥጥሩ መጥበቅ አለበት፡፡ ፎቆቹ
በአደባባይ ይናገራሉ፡፡ ቤቶቹ በይፋ ያሳብቃሉ፡፡ መሬቶቹ ሊያሸሿቸው የማይችሉ የምዝበራው አካል ናቸው፡፡ ከየት እንደመጣ ማብራሪያ
የማይሰጥበት ሀብት የፊት ለፊት ማስረጃ ነው!! ለባንክ ዕዳ መክፈያ ለሀራጅ የሚቀርቡት ንብረቶች፣ በማያወላውል መልክ በመሞዳሞድ የታጀሉ ብዝበዛዎችን ያጋልጣሉ!!
‹‹አንድ አንኳር ጨው ውቂያኖስን አያሰማ›› የሚለውን ተረት በጥሞና እያስተዋልን፣ እርምጃው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ዘምቶ የሚቆም መሆን እንደሌለበት መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ፤ አንድም ሙስናው ውቂያኖስ አከል በመሆኑ፣ አንድም ሙስና የቀጣይነት ባህሪው ሥር-ሰደድ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ የሙስና ሂደት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የመንግሥት አባላት፣ የፓርቲ አባላት፣ ነጋዴዎች፣ ደላሎችና ዐይን ያወጡ ኤጀንሲዎች ወዘተ … የቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝሙ ፓኮ ውስጥ ያሉ ናቸው። እንዲህ በአገር ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ምዝበራን እንዲያጥጥና እንዲናኝ የሆነው መዝባሪዎቹ ማንን ተማምነው ነው? የሚለውን ጥያቄ ማቅረብ የአባት ነው፡፡ ምነው ቢሉ፤ ‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች›› የሚለው ተረት ፊታችን ድቅን ይላልና! አሁንም ውስጣችንን እንመርምር፡፡ ጥልቅ ተሐድሶ የዕውነት ጥልቅ መሆኑን በተግባር እናረጋግጥ! ልባዊ እንጂ አፍአዊ አለመሆኑን እናጣራ!
‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህንም›› አስብ! ‹‹ባለቤቱን ካልናቁ፣ አጥሩን አይነቀንቁን›› አንርሳ!
“ያሳር እሳት የሚጫረው”
ጥንትም በእፍኝ ጭራሮ ነው!
የሚለውን በመሰረቱ እንገንዘብ፡፡
በሼክስፒር ብዕርና በፀጋዬ ገ/መድህን አንደበት፤
“ነበርን ማለት ግን ከንቱ ነው፣
ተው ነው መጀነኑ በቅቶን፤
ጉራ መንዛት መዘባነን፣
የሚያዛልቅ ዘዴ ባይሆን!”
የሚለውን በጭራሽ አንዘንጋ፡፡

No comments:

Post a Comment