Tuesday, January 24, 2017

ተሐድሶን የምናይበት መነጽር ላይ እንስማማ!! – በያሬድ አውግቸው

   


የተለያዩ ፍላጎቶችና አመለካከቶችን ለማስተናገድ  የሚፈቅዱ ህጎችና አሰራሮችን መቅረጽ  ሳይቻል በመቅረቱ በንጉሱም ሆነ በደርግ አገዛዝ ብዙ ተቃውሞዎች ተቀስቅሰው እንደነበር ይታወሳል። ተቃውሞዎቹን ተከትሎ የተነሱ ግጭቶችም መጠነ ሰፊ የህይወት መስዋእትነት አስከፍለውናል፡፡ የመስዋዕትነቶቹ ዋነኛ ምክንያት የህዝቦች ድምጽ የሚደመጥበት  የፖለቲካ ስርዓትን በሚፈልጉ ወገኖችና ስልጣንን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ልዩ መብት አለን በሚሉት መካከል ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ነበር፡፡
ከእነዚያ ግጭቶችና ቀውሶች በኋላም ግን፣ ከማዋከብ ነጻ የሆነ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትንና  ሰላማዊ  የስልጣን ሽግግርን ብቸኛ ምርጫችን ለማድረግ ከስምምነት ላይ አለመድረሳችን ግራ አጋቢም አስገራሚም ነው። በተመሳሳይ መልኩ፤ ከማናቸውም  ሃገራት በተሻለ ለመደማመጥ የሚያስችሉን እንደ የገዳ ስርዓት አይነት ነባር ሃገራዊ  የዲሞክራሲያዊ ባህሎች ባለቤት ብንሆንም ቅሉ አልተጠቀምንበትም፡፡
በቅርቡ ገዥው ፓርቲ ምክንያታቸው፣ “የውስጤ ችግሮች ናቸው” ያላቸው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች  መከሰታቸው ይታወቃል። ገዥው ፓርቲ የችግሮቹ ዋና መነሻ፣ ስልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና  ሙስና መሆናቸውን ገልጾ፣ ህዝቡ በኢህአዴግ  መሰረታዊ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና እምነቶች ላይ ምንም አይነት ጥያቄዎች የሉትም የሚለውን ለረጅም ጊዜ የቆየ እምነቱን አሁንም ደግሞታል። እንደ ተቃዋሚ ሃይሎች (በዚህ ጽሁፍ አማራጭ የፖለቲካ ሀይሎች እየተባሉ የሚገለጹት) እምነት ግን የሃገሪቱ የፍትህና የምርጫ ስርዓቶች ነጻ ያለመሆን፣ በሁለቱ ክልሎች ለተከሰቱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች  በዋነኛ ምክንያትነት ይቀርባሉ። በእኔ ምልከታ ገዥው ፓርቲና አማራጭ ሃይሎች  ለችግሩ መነሻነት ያቀረቧቸው ምክንያቶች፤ “እሳትን የማጥፋት” እና “የስትራቴጂክ” የመፍትሄ አማራጮችን ያህል ልዩነት ያላቸው ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡
እንደ አማራጭ ፓርቲዎች እምነት፤ ከመሰረታዊ ችግሮቹ ውስጥ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ብቻ ነጥሎ ማውጣት፣ ከችግሮቹ ይልቅ የበሽታው ምልክቶችን ለማከም እንደ መሞከር ይሆናል። ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የተለያዩ ህጎችና አደረጃጀቶች መሻሻል አስፈላጊነቱ ባይካድም፣ በብዙ ምክንያቶች  ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ፍትህን ለመድፈቃቸው ዋነኛው ምክንያት፣ በገዥው ፓርቲ በኩል የተጠያቂነትና የቁርጠኝነት አለመኖር፤ የፍትህና የጸጥታ ሃይሎች ፍትህን ሳይሆን አስፈጻሚውን አካል ወክለው መስራታቸው፤ በአጠቃላይ ህገመንግስቱና እሱን ተከትለው የወጡ ማስፈጸሚያ ህጎች ላይ ክፍተቶች መኖርና ወደ ስራ መግባት አለመቻላቸው ይጠቀሳሉ። በቀጣይነት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ወይም ጎን ለጎን  በመንግስትና በአማራጭ የፖለቲካ ሀይሎች በኩል መወሰድ የሚገባቸው  እርምጃዎችን  አስመልክቶ  የተወሰኑ አስተያየቶችን  አቀርባለሁ።
ከላይ እንደገለጽነው ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀምና ሙስና፣ የጥያቄዎቹ መነሻ ናቸው የሚል  ድምዳሜ  በመንግስት በኩል መቅረቡ ይታወቃል። ከበፊቱ የተሻለ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ግለሰቦች  በፌደራልና በክልል ካቢኔዎች የተካተቱ ሲሆን በሙስና የተዘፈቁ የመንግስት ሃላፊዎች  ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የሚገልጹ ዜናዎች ሰምተናል፡፡ በመሰረታዊነት በገዥው ፓርቲ የተገለጹትም  ሆነ በሌሎች ወገኖች የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት  ለመፍታት ከግለሰባዊነት  የጸዳ /Objective/ ተጠያቂነትን ማጠናከር፤ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ለመደገፍ የቆረጡ ፖሊሲዎችና ህጎች መኖር (ለምሳሌ ለአማራጭ የፖለቲካ ሃይሎች የሚደረጉ  ድጋፎችን ማሻሻል ዙሪያ)፤ ከተጽዕኖ የጸዱ የፍትህና የጸጥታ ተቋማት መኖር፤ እንዲሁም ፖሊሲዎቹንና ህጎቹን ለመደገፍ የሚደረጉ የአደረጃጀት ለውጦች አስፈላጊነት  እሙን ነው። የሌሎች በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ልምድ ያላቸው ሃገሮች ተሞክሮም ይህንኑ ያሳያል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ በአማራጭ ሃይሎችና በገዥው ፓርቲ በኩል የሚታዩ የቃላትና የጽሁፍ ምልልሶች፣ ገዥው ፓርቲ አማራጭ ሀይሎቹን  ለማንኳሰስ፤ አማራጮቹም የሚደርስባቸውን ተጽዕኖ ለማሳየት  ከመሞከር የዘለለ አልነበረም። በመሰረታዊነት  ችግሮቹን ለመቅረፍ ከተፈለገ መወሰድ ያለበት መፍትሄ፣ ሁሉም አካላትን ያካተተ፣ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ  ግዜ  መፍታት የሚያስችሉ ከላይ የተገለጹ ህጎችና አደረጃጀቶች ማዘጋጀት ይሆናል።
የህግ ማእቀፎቹና እነሱን ለማስፈጸም የሚገነቡ አደረጃጀቶች፣ ከገዥው ፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ የሚያደርጋቸው ስርዓትም ሊዘጋጅላቸው ይገባል። ለምሳሌነት ሃላፊነት የሚሰማቸው ጠንካራ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በጠንካራ የህግ ከለላና ጥበቃ መውለድ የሚያስችል የተለጠጠ ህግ አንዱ ነው። ከዚህ በፊትም አንዳንድ ወሳኝ የህዝብ ወኪሎችን ከጥቃት ለመከላከል ሲባል ልዩ ከለላ  የሚሰጡ ህጎችን ስንጠቀም ቆይተናል። ለምሳሌነት ከሃላፊነታቸው እስኪነሱ ድረስ የፓርላማ አባላት ያለመከሰስ መብት እንዲኖራቸው የሚደነግገው ህግ ይታወሳል።  በተመሳሳይ  አማራጭ ሀይሎችን  ከጥቃት ለመጠበቅ ሲባልም፣ ለአማራጭ ሀይሎች የሚደረጉ የገንዘብ ድጋፎች  በህግ ጥበቃ በሚደረግላቸው፣ ሆደ ሰፊ ተቋማት እንዲተዳደሩ ማድረግ ይገባል (ለምሳሌ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካውንስል ሊቋቋምና ሊያስተዳድራቸው ይችላል)። ፓርቲዎቹ ስራ ላይ እስካሉ ድረስ በምንም መስፈርት የማይነጠቁት፣ ኪራይ የማይከፈልባቸው ወይም አነስተኛ ኪራይ የሚጠየቅባቸው፣  ለስራና ለስብሰባ  ምቹ የመንግስት ቤቶችን ለአማራጭ ሀይሎች ማቅረብም ሌላው አማራጭ ሊሆን ይችላል። ገዥው ፓርቲ የያዘውን የመንግስት ስልጣን ተጠቅሞ፣ በሃገር ሃብት ድርጅቱን ያጠናከረበት ተሞክሮ እዚህ ላይ ማስታወስ ግድ ይላል።  ለፓርቲዎች የስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት የሚያጎናጽፉ ህጎችም፣  የገዥው ፓርቲ  አባላት በህግ ማስከበር ሰበብ ጫናዎች እንዳያደርሱ ከለላ በሚሰጥ መልኩ መዘጋጀት  ይገባቸዋል።
የምርጫ ህጉ፤ የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፤ የቦርዱ አባላት ምርጫ እንዲሁም  የምርጫ ቦርድን ጽ/ቤት ሃላፊዎችና ሰራተኞች አመላመል የተመለከቱ ህግና ደንቦች፣ አማራጭ ፓርቲዎችን ባሳተፈ መልኩ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ የፖሊስና የሃገር መከላከያ ሰራዊት አደረጃጀቶችን በተመለከተ በሃገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ጠንካራ አማራጭ ሃይሎች ነጥረው እስኪወጡና ገዥውን ፓርቲ በማናቸውም መልኩ መፎካከር እስኪችሉ ድረስ ለተወሰኑ ዓመታት የሰራዊቶቹ የበላይ አመራሮች ሹመትና ሽረት  ቢያንስ አንድ ወንበር በፓርላማ ያላቸው አማራጭ ሃይሎችን ስምምነት የግድ እንዲያገኝ ገዥው ፓርቲ በህግ ማዕቀፍ ቁርጠኝነቱን ማሳየት ይኖርበታል።  ሌሎች የጸጥታና የሰብአዊ መብት  ተቋማትም በተመሳሳይ ስምምነት ሊኖርባቸው ይገባል።  በሌላ በኩል የሲቪክ ማህበራት፣ ህዝቦች በተደራጀ መንገድ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ጉዳዮቻቸውን የሚያንሸራሽሩባቸው ተቋማት በመሆናቸው ገዥው ፓርቲ  ለጥንካሬያቸው  በህግ ማዕቀፍ መስራት አለበት። የገንዘብ ምንጫቸውን በተመለከተ ያለበትን ከልክ ያለፈ ፍርሃትም ማስወገድ ይኖርበታል።
ሌላው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ተቀባይነት ለማግኘት በሚያስችል መልኩ ፕሮግራማቸውን ከማዘጋጀት ይልቅ  ተአማኒነትንና  ዘላቂ ልማትን በሚያረጋግጥ መልኩ ማዘጋጀት  ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም የጥናትና ምርምር ክፍል በፓርቲያቸው መዋቅር ስር ማቋቋምና በቅጡ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። ለምሳሌነት በገዥው ፓርቲ በኩል በጥንት ዘመን ስነ-ልቦናና ግንዛቤ የተተገበሩ ግጭቶችን ዛሬ እንደተደረጉ አጉልቶ  ማቅረብ ይስተዋላል። በተመሳሳይ  በገዥው ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ እንደ አቅጣጫ ተቀምጠው በመንግስታዊ ተቋሞቻችን ውስጥ እቅድ እንዲዘጋጅላቸው መመሪያ የሚሰጥባቸው ከጥናት ያልተናነሱ አንዳንድ ወሳኝ ስራዎችን አይተናል፤ ሰምተናልም።
ተጨባጭ መነሻ ስለሌላቸው ስራዎቹ   በአፈጻጸም ወቅት ተደጋጋሚ ስር ነቀል  ክለሳ ወይም ለውጥ ሲደረግባቸው ይታያል። በአንዳንድ ተቋማት በፍጥነት የሚለዋወጡ ባለስልጣናት ለስራው ባይተዋር መሆናቸውን ተከትሎ የሚመጡ የአመራር ክፍተቶችም  ለችግሩ የበኩላቸውን ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። ሌላው ትልቅ ድርሻ መያዝ የሚገባው እርምጃ  የፖለቲካ ባህላችንን መገምመገምና ማስተካከያ ማድረግ ነው፡፡ የፖለቲካ ባህላችንን በጥልቀት ስንገመግም፣ እኛ እና እነሱ በሚለው፣ ጽንፍ በረገጠ ማእቀፍ ወይም መነጽር  ስር ካልሆነ  በቀር ፖለቲካን ማራመድ የማንችል ይመስላል።  “እኔን   ያልደገፈ ሁሉ የሃገር ጠላት ነው” ዓይነት ጽንፍ የረገጠ ንቀት፣ ለትብብርና ለውይይት ቦታ የማይሰጥ በመሆኑ፣  ለፖለቲካው ስርዓት እድገት ማነቆ መሆኑ አያጠያይቅም። ከዚህ አስተሳሰብ ለመውጣት ገዥው ፓርቲም ሆነ ሌሎች አካላት ቁርጠኝነት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።  ምክንያቱም ዘላቂ ሰላምና የዜጎች ነጻነት እውን የሚሆኑት ሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች የሚፈልጉትን ተወካይ፣ ወደ  ውሳኔ ሰጭ ወንበሮች ማውጣት ሲችሉ ብቻ ነው። የምድራችን  የዲሞክራሲ ስርዓቶች ታሪክም ያለአንዳች ልዩነት ይህንኑ ያጸኸያሉ፡፡

No comments:

Post a Comment