Wednesday, January 4, 2017

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ዋስትና ተከለከለ



ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ዋስትና ተከለከለ
ከሽብርተኝነት ክስ ነጻ ተብሎ በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ እንዲከላከል ብይን የተሰጠው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጎበታል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 13/2009 ዓ.ም ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ከቀረበበት የሽብር ክስ ነጻ በማለት ክሱ ወደ መደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ተቀይሮ አንቀጽ 257 (ሀ) ላይ የተመለከተውን እንዲከላከል ሲል ብይን መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ እንዳለውና ለአንድ አመት በእስር መቆየቱን በማንሳት አሁን ተከላከል የተባለበት የህግ ክፍል የዋስትና መብት እንደማይከለክል ጠቅሶ የዋስ መብቱ እንዲከበርለት ታህሳስ 19/2009 ዓ.ም ፍ/ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ በዕለቱ አቃቤ ህግ ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ ከሀገር ሊወጣ ስለሚችል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
ፍ/ቤቱ ዛሬ ታህሳስ 25/2009 ዓ.ም በተነሳው የዋስትና ጥያቄ ላይ መርምሮ ብይን ሰጥቷል፡፡ በዚህ መሰረት ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ ‹‹ከሀገር ሊወጣ እንደሚችል ግምት የተወሰደ በመሆኑ›› የዋስትና ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም ሲል ፍ/ቤቱ ዋስትና ከልክሎታል፡፡ ፍ/ቤቱ ተከሳሹ በዋስ ቢወጣ ከሀገር ሊወጣ ይችላል የሚለውን ግምት ለመውሰድ የቀረበለት ማስረጃ ስለመኖሩ በብይኑ ላይ አላመለከተም፤ አቃቤ ህግ ተቃውሞውን ባስመዘገበበት ወቅትም ተቃውሞውን በማስረጃ አስደግፎ አላቀረበም ነበር፡፡
‹‹ተከሳሹ ተከላከል የተባለበት የህግ አንቀጽ በመርህ ደረጃ ዋስትና ባያስከለክልም፣ በሁኔታ የሚከለከልበት ጊዜ ግን ስለመኖሩ ተመልክቷል፡፡ እኛም ይህን ተከሳሹ ከሀገር ሊወጣ ይችላል የሚለውን ሁኔታ አይተን በሙሉ ድምጽ ተከሳሹ ዋስትናው ይነፈግ ብለን ወስነናል›› ብሏል ችሎቱ የዳኞችን ውሳኔ በተመለከተ ሲገልጽ፡፡
ፍ/ቤቱም መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለየካቲት 7/2009 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡
የዜና ምንጭ. Ethiopia Human Rights Project

No comments:

Post a Comment