Monday, January 30, 2017

በጎንደር/በጌምድር ኦሮሞዎች ይገዙ ነበር – #ግርማ_ካሳ

   


አንዳንድ የኦሮሞ ብሄረተኞች አንደኛ ኦሮሞው ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ማንነት እንዳለውና ኦሮሞነት እና ኢትዮጵያዊነት የተለያዩ እንደሆኑ ፣ ሁለተኛ በኢትዮጵያ ይገዛና “ጨቋኝ” የነበረው “አማራ” የሚሉት ማህበረሰብ ብቻ መሆኑን ሊነግሩን ይሞክራሉ።
ታሪክ ግን የሚለው ሌላ ነገር ነው። አጼ ቴዎድሮስ ከመንገሳቸው በፊት እንደ አባ ሰሩ ግዋንጉል፣ ራስ አሊ አንደኛ፣ ራስ አሊጋዝ፣ ራስ ጉግሳ መርሳ፣ ራስ ይማም፣ ራስ ማሪዬ፣ ራስ ዶሪ እና ራስ አሊ ሁለተኛ ያሉ የየጁ ኦሮሞ መኳንንት ሰሜን ኢትዮጵያን ይገዙ ነበር። ከሰለሞን ነገድ ናቸው የሚባሉ ንገስታትን እንደው እንደ ምልክት አስቀምጠው ነበር እነዚህ ኦሮሞዎች አገሪቷን ሲያሽከረክሩ የነበሩት።
አንድ ወቅት እንደዉም በጎንደር ቤተ መንግስት አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ እንደነበረም ይነገራል።
ጀግናዋ እቴጌ ጣይቱ “ኦሮሞ ናቸው” ብዬ መጻፌን ተከትሎ “ከበጌምድር ናቸው” የሚል አስተያየት ቀርቦልኛል። ትክክል ነው። እቴጌ ከበጌምደር ነበሩ። ግን ግንዳቸው ወደ የጁም ይሄዳል። የእቴጌ ጣይቱ አባት ራስ ብጡል ሃይለማሪያም፣ የየጁ ኦሮሞ መኳንንትና የንጉሱ እንደራሴ ሆነው ሲገዙ የነበሩት የራስ ጉግሳ መርሳ የልጅ ልጅ ናቸው።
የትግሬው ራስ መንገሻ ሚስት ከፋይ ወሌ ፣ የንግስት ዘዉዲቱ ባለቤት ራስ ጉግሳ ወሌ፣ የሰሜን (የተወሰነ ጊዜም የትግራይ እና የባህር ምድሪ/ኤርትራ ) ገዢ የነበሩትና የእቴጌ ጣይቱ አጎት ራስ ዉቤ ሃይለማሪያም፣ የየጁ ራስ ጉግሳ መርሳ ልጅ ልጆች ናቸው። የአጼ ቴዎድሮስ ባለቤት እቴጌ ተዋበች አሊ፣ የራስ አሊ ሁለተኛ ልጅ ነበሩ። የበጌምድር ራስ የነበሩት ራስ አሊ አንደኛ፣ የራስ ሚካኤል ስሁልን ሞት ተከትሎ የኢትዮጵያ ንጉስ እንደራሴ ሆነው ይገዙ በነበረበት ወቅትም፣ ዋና ከተማቸውን ወደ መግደላ ከማዞራቸው በፊት የአጼ ቴዎድርስ መቀመጫ የነበረችዋን ታሪካዊቷን የደብረ ታቦር ከተማ የመሰረቱት፣ እኝኑ የየጁ ኦሮሞ ገዢ እንደነበሩም ይነገራል።
እንግዲህ አስቡት አሁን ሕወሃት/ኢሕአዴግ በዘር ሸንሽኖ የአማራው ክልል ብሎ በመሰረተው ግዛት እምብርት ምን ያህል በትልቁ የኦሮሞዎች አሻራ እንዳለ። አስቡት ምን ያህል የኦሮሞው ማህበረሰብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የተሳሰረና የተዋለደ እንደሆነ።
ዘረኝነትን ለመስበክ፣ አንድን ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር ሆን ብለው ለማጣላት ጥቂቶች የሚሸርቡት እንጅ፣ ኦሮሞዎች ሌላው ይገዛቸው እንደነበረው ሁሉ እነርሱም የገዙ፣ ሌላው እንደበደላቸው እነርሱም የበደሉ፣ ከሌላው ጋር የተደባለቁ መሆናቸውን ነው ታሪክ የሚያስተምረን። የጸዳ፣ የጠራ የኦሮሞ ማንነት የለም።
እቴጌ ጣይቱ ኦሮሞ ነበረች ስንል፣ ኦሮሞ ብቻ ነበረች ማለታችን አይደለም። ከኦሮሞም፣ ምናልባትም ከትግሬው፣ ከአገው የተደባለቀች ናት። አንድ ወዳጄ እንደተናገረው “ኦሮሞ”፣ “ትግሬ”፣ “አማራ”…..ትል ያልነበረች ማንነቷ ኢትዮጵያዊነት ብቻ የነበረ ታላቅ የኢትዮጱያ ብቻ ሳይሆን የጥቅር ህዝብ እናት ነበረች።
ይሄን ግሩም ሙዚቃ ተጋበዙ።

No comments:

Post a Comment