Friday, January 27, 2017

የጅቡቲ አፋሮች ትግል እንዴት ከሸፈ? ክፍል 3 – ከይገርማል


ጉዞ ወደጅቡቲ በረሀ  

ወደጅቡቲ ይዞኝ ከሚሄደው ሰው ጋር ለመገናኘት ባቲ ከተማ ፍኖተ ሰላም ከሚባል ሆቴል በሀምሌ 1984 ዓ.ም የወሩ የመጀመሪያ ቀናት አካባቢ ቀጠሮ ተይዞልኛል። ከሆቴሉ ስደርስ ቀጠሮ የያዘችልኝ ልጅ ከአንድ መካከለኛ ቁመት ካለው ቀጠን ካለ ጠይም የአፋር ወጣት ጋር እያወራች ነበር። “ኦ! እንኳን ደህና መጣህ፡ ስንጠብቅህ ነበር” አለችኝ እንዳየችኝ። የሩጫ ያህል ተጣድፌ ከእቅፌ አስገባኋት። በጭንቅ ጊዜ የደረሰችልኝ እህቴን ምን ማለት እንዳለብኝ ማወቅ ተስኖኛል። ለረጅም ጊዜ ተለይቶ ሲናፍቅ እንደኖረ ፍቅረኛ ተጠምጥሜ ይዠ አልለቃት ብል “ኧረ በቃ!” አለችኝ እየሳቀችና ከእቅፌ ለማምለጥ እየሞከረች። “ላደረግሽልኝ ሁሉ አመሰግናለሁ!” አልኋት ሀፍረት ቢጤ ሽው እያለብኝ። “ደግሞ እንዲህ የሚያስብል ምን ውለታ ውየልህ ነው? አጋነንኸው እኰ! ለማንኛውም ይዞህ የሚሄደው እሱ ነው፤ ተዋወቁ!” አለችኝ ወደ ወጣቱ እየጠቆመች። የትውውቁ ሥነስርዓት እንዳለቀ ቡናና ሻይ አዝዘን ፉት እያልን በእርሷ አስተርጓሚነት ብዙ አወራን። በመጨረሻ ጉዟችን በሚቀጥለው ቀን እንዲሆን ተስማምተን የምንገናኝበትን ሰዓት ቆርጠን ስናበቃ መልካሙን ሁሉ ተመኝታልኝ ከአፋሩ ወጣት ጋር ሄደች።

ወጣቱ በቀጠሯችን መሰረት በበነጋታው እኩለቀን አካባቢ አልጋ ከያዝሁበት ሆቴል መጣ። ተዘጋጅቸ ጨርሸ የርሱን መምጣት እየጠበቅሁ ስለነበር እንደደረሰ ሻንጣየን አንጠልጥየ መኪና ፍለጋ ወጣን። ብዙም ሳንቸገር ወደአሰብ  የሚሄድ አንድ የጭነት መኪና አግኝተን እስከማንዳ ድረስ ለሁለታችን 30 ብር ከፍየ ጉዟችንን ጀመርን።
ሚሌን እልፍ እንዳልን አንድ ወንድና አንድ ሴት አፋር አስቆሙን። “እኒህ ሰዎች 5 ሣንቲም ያወጡበት ይመስል በንብረታችን ያዝዛሉ” አለ ሾፌሩ እየተነጫነጨ። ምን ለማለት እንደፈለገ ስላልገባኝ ዝምታን መረጥሁ። ለነገሩ አብሮኝ ያለውም ወጣት አፋር ስለሆነ በአማርኛ ስናወራ በርሱ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ስሜትም ስለማላውቅ ነው። ጥቂት ከተጓዝን በኋላ ከሴቲቱ ጋር ያለው አፋር በተሰባበረ አማረኛ መኪናውን እንዲያቆም ሾፌሩን ጠየቀው። ዝናብ ዘንቦ ስለነበር በመንገዱ ዳርቻወች ጎርፍ ይታያል። አፋሩ ከዚያ ጎርፍ በሆነ ዕቃ ጨልፎ ግጥም አድርጎ ጠጣ። ለሴትዮዋም ሰጣትና እርሷም እንደሱ ጭልጥ አድርጋ ጠጣች። “አሃ! ባቲን ካለፉ ውሀ ወለድ በሽታ የለም ማለት ነው!” አልሁ ለራሴ።
ማንዳ የደረስነው አመሻሽ ላይ ነው። ርሀብ እየተሰማኝ አይደለም። ቢሆንም አብሮኝ ላለው ልጅ ስል ምግብ ቤት መሄድ ይኖርብናል። እራት እንድንበላ በምልክት ስነግረው ገባው። ከዚህ የበለጠ መግባቢያ፣ ከዚህ የበለጠ ቋንቋ ምን አለ! እንድከተለው በምልክት ነግሮኝ ወደአንዲት ደሳሳ ጎጆ መራኝ። በዚች ደሳሳ ምግብ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ “ሉህሉህ”ን ተዋወቅሁ። ሉህሉህ ማለት በመጥበሻ የምትጋገር ዝርግ ሳህን የምታህል እንጀራ ናት። አንድ ሉህሉህ በድፍን ምስር ወጥ ዋጋው ሁለት ብር ነበር።
ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ሲሆን ወደጅቡቲ የሚሄዱ የአፋር ነጋዴወች ግመሎቻቸውን ሸክፈው ለጉዞ ተነሱ። አብሮኝ ያለው የአፋር ወጣት የእንከተላቸው ምልክት ስላሳየኝ አብረናቸው ለመሄድ ተጣደፍን። ግመሎች ሥነስርአት ያላቸው ናቸው። አንድ ሰው ብቻ ከፊት ያለውን ግመል የታችኛውን ከንፈሩን በገመድ አስሮ ይመራል። ከኋላ የሚከተለው ግመል ከንፈር ከፊተኛው ግመል ጅራት ጋር ይታሰራል። ለጉዞ የተሰናዱ ግመሎች በሙሉ በዚህ መልክ ይያያዛሉ። ከፊት የሚስበው ሰው የሚሄድበትን ተከትሎ ሁሉም ግመል እንደ ጉንዳን ሰራዊት በሰልፍ ይጓዛል። ወደግራ እሄዳለሁ፣ ወደቀኝ አዘነብላለሁ ብሎ የሚያስቸግር የለም። ብዙም ርቀን ሳንሄድ ልቤ ስልብ አለብኝ። ወበቁም ከአቅሜ በላይ ነበር። ከነጋዴወች ጋር እኩል መራመድ አቅቶኝ ከኋላ ቀረን። ከንፈሬም ጉሮሮየም ደረቁ። ችግሬን የተረዳው ጓደኛየ እየመራ ውሀ ወደምናገኝበት ቦታ ይዞኝ ሄደ። በዚያ መንገድ ብዙ ጊዜ የተመላለሰ ስለሆነ ምን የት እንዳለ ያውቃል። የተቋጠረ ውሀ ካለበት ጐድጓዳ ቦታ ላይ ስንደርስ ወደውሀው እያመለከተኝ እንድጠጣ ጋበዘኝ። ጨልፈን የምንጠጣበት እቃ እንኳ አልያዝንም። እኒያ አፋሮች ጎርፍ ጠጡ ብየ ስገረም የነበርሁት ሰውየ ሰውነቴን ዘረጋግቸ በሆዴ ከመሬት ተስማማሁና ያንን ተቋጥሮ የከረመ ውሀ እዘርፈው ጀመር። ሆዴ እየተነፋ ሄደ እንጅ እርካታን አላገኝ አልሁ። በቃህ አለኝ ጓደኛየ በምልክት። ሆዴ እየቆየ እየተነረተ ጉሮሮየ ደረሰ። ወደላይ የለ ወደታች የለ! ከዚህ በኋላ አልሄድም አልሁና ከመንገድ ወጣ ብየ ብትንትን ብየ ተኛሁ። ጠዋት ስነቃ አፋሩ ጓደኛየ ከጎኔ ተቀምጧል። ስለውለታው የማመሰግንበት የተረፈ አቅም አልነበረኝም። ለማመን ይከብዳል፤ ገና በጠዋቱ ሙቀቱ አንጀት ስልብ ያደርጋል። እንደምንም ተጎትቸ ተነስቸ እያዘገምን ቡያ ከምትባል የጅቡቲ መንደር ደረስን። ከኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተለየሁ ማለት ነው። አሁን ያለሁት ውጪ ሀገር ነው።

No comments:

Post a Comment