Wednesday, January 18, 2017

የትግራይ ተወላጆች “በጦርነት ሳቢያ ለተጎዳችው” ትግራይ የኢትዮጵያ ህዝብ ካሳ ይከፍል ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጠየቁ



የትግራይ ተወላጆች “በጦርነት ሳቢያ ለተጎዳችው” ትግራይ የኢትዮጵያ ህዝብ ካሳ ይከፍል ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጠየቁ
(አቻምየለህ ታምሩ)
የጉድ አገር!
“ጉዳዩ ያሳሰባቸው የትግራይ ተወላጆች” የበታችነት ስሜቱን “በወታደራዊ የበላይነት” ለማሳየት ወያኔ ከቀድሞው አሳዳሪው ከሻዕብያ ጋር ባደረገው የእብሪት ጦርነት ሳቢያ “ለተጎዳችው” ትግራይ የኢትዮጵያ ህዝብ ለትግራይ ካሳ ይከፍል ዘንድ ጠየቁ። ለወያኔ ኪሳራ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲከፍል የሚጠየቅባት አገር! ግፈኞች!

የጠያቂዎቹ መቆርቆር ግላዊ ሳይሆን ሰብዓዊ ቢሆን ኖሮ ማቅረብ የነበረባቸው አቤቱታ ግፈኛው የወያኔ አገዛዝ የበታችነቱ ወይም መንፈሰ ደካማነቱ የሚሽርለት መስሎት በገባበት ጦርነትና እስካሁን ስላጠፋው ጥፋት፤ “ባድመ ለኢትዮጵያ ተወሰነች” ብሉ አደባባይ ወጥተን እንድንጨፍር ስላደረገው አገዛዝና አካባቢውን ለሁለት አስርት አመታት ያህል የጦርነት ቀጠና በማድረጉ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቆ ከስልጣን እንዲወርድ መጠየቅ ነበረባቸው።
ወያኔዎች የሻዕብያ ጀሌ ሆነው አዲስ አበባ እንደገቡ “ሽግግር” ባሉት ወቅት ባዘጋጁት ቻርተርና “ሕገመንግሥታዊ ሰነድ” “የልማት ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ ክልሎች” የሚል አንቀጽ በማስገባት የአገሪቱን ሁለንተናዊ ኅሊናዊና ቁሳዊ ሀብት ወደ ትግራይ በማፍሰስ ትግራይን “የአፍሪካ ታይዋን” ለማድረግ ቀን ተሌሊት ሲሰሩ እንደከረሙ ለቀባሪው ማርዳት ነው። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ለተጎዳው አካባቢም “የልማት ቅድሚያ” እና “ልዩ ድጎማ” ሲሰጠው እንደነበር ያለፉትን የኢትዮጵያ አስራ አምስት በላይ አመታት የበጀት አመዳደብ ቀመር ለምናውቅ ግልጽ ነው። እንግዲህ “ጎበዞቹ” “ጉዳዩ ያሳሰባቸው የትግራይ ተወላጆች” የሚጠይቁት ወያኔ ባለፉት ሀያ አመታት አካባቢ “የልማት ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ ክልሎች” እያለ የአገር ሀብት ወደ ትግራይ ሲያሸሽ ከነበረው ተጨማሪ ነው።
“ጎበዞቹ” ትግራይ እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው በጦርነቱ የተጎዳው መላው የኢትዮጵያ ህዝብና ሀገሪቱ እንጂ አንድ ክፍለ ሀገር ብቻ እንዳልነበረ ስናስታውስ ነው። “ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው በጦርነቱ ሰማንያ ሺህ ልጆቻቸውን የገበሩ ኢትዮጵያውያን ወላጆች እድሜ ልካቸውን በልጆቻቸው ሞት ተጎድተው መኖራቸውን ስናስታውስ ነው።
“ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው የትግራዩ ወያኔ በጫረው ጦርነት ወደ ሰማንያ ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ረግፋውና ሰማንያ ሺህ እናቶችና አባቶች ያለጧሪ፤ በመቶ ሽዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህጻናት ደግሞ ያለ ወላጅና አሳዳጊ ቀርተው የሚያስታውሳቸው ጠፍቶ ሜዳ ላይ መውደቃቸውን ስናስታውስ ነው።
“ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው ሁለት አመት በፈጀው የወያኔና የሻዕብያ ጦርነት የመላው ኢትዮጵያ በጀት ለጦርነቱ ይውል ሲውል እንዳልነበር ትግራይ ብቻ እንደተጎዳች ተደርጎ ተለይታ ትካስ ተብሎ መቅረቡን ስናስታውስ ነው።
“ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ግፍ የሚሆነው በጦነተ ለተጎዱ አካባቢዎች እየተባለ የበጀት ቀመር ወጥቶለት ከኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀት ጦርነት ወደተካሄደበት “ክልል” ፈሰስ ይደረግ እንደነበር ስናስታውስ ነው።
“ጎበዞቹ” ትግራይ ለሁለት አስርት አመታት ያህል በጦርነቱ ስለተጎዳች እንድትካስ የሚጠይቁት ምጸት የሚሆነው ወያኔ የሚመራው “መንግስት” “ወዲ አፍሮ” ለስልጣኑ አደጋ ስለሆነ አስመራ ድረስ ዘምቶ ያስወግደው ዘንድ በትግርኛ ሲማጸኑ የነበሩ ጦርነት ናፋቂዎች መሆናቸውን ስናስታውስ ነው። የጉድ አገር!
*********
የትግራይ ተወላጆች “በጦርነት ሳቢያ ለተጎዳችው” ትግራይ የኢትዮጵያ ህዝብ ካሳ ይከፍል ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን የጠየቁበትንና በአውራምባ ታይምስ ላይ የወጠውን ከዚህ በታች ያንብቡ።

No comments:

Post a Comment