Friday, January 27, 2017

በታሪክ ወራሪዎች ነበሩ ፥ ተወራሪውችም ነበር ፥ የሰው ባሮች ነበሩ ፥ የሰው ጌቶችም ነን የሚሉ ነበሩ ። ኄኖክ የሺጥላ


ኢሳት የ ሃይሌ ላሬቦን ቃለ መጠይቅ "ያልተገባ ነገር የተላለፈበት"በማለት የእከክልኝ ፥ ልከክልህ መግለጫ አውጥቷል። ያልተገባነቱ ከምን አንፃር ነው ? ከታሪክ አንፃር ከሆን እርሳቸው ( ሃይሌ ላሬቦ ) ያሉት ወይም ( የተናገሩት እና የጠቀሱት ) ነገር ልክ እንዳልሆነ የሚያብራራ የታሪክ ምሁር ጋብዞ እውቀት እና እውነት ላይ በተመሰረተ ውይይት ችግሩን መፍታት።
"ጋላ" መባል እልነበረበት ከሆነ፥ ሃይሌ ላሬቦ አይደሉም ጋላ የሚለውን ስም ያወጡት ወይም ያመጡት። በታሪክ « ጋላ» ይባል ነበር አሉ! ይህም ልክ አለመሆኑን የሚያስረዳ ምሁር መጋበዝ፥ ማወያየት ፥ የተሸነፈው ( ወይም በውይይቱ ) ነጥብ የጣለው አካል እጅ ይስጥ!
በታሪክ ወራሪዎች ነበሩ ፥ ተወራሪውችም ነበር ፥ የሰው ባሮች ነበሩ ፥ የሰው ጌቶችም ነን የሚሉ ነበሩ ። ሰዎች እንደ ...መጋዣ በገመድ ታስረው ወፍጮ ያዞሩ ነበር፥ ወይን ይጨምቁ ነበር፥ ረራራ ይምሱ ነበር ፥ መንገድ ይሰሩ ነበር፥ ቋጥኝ ይፈልጡ ነበር ! ባርነተታቸው የምድራዊ ታሪካቸው እና የህይወት ውጣ ውረዳቸው አንዱ አካል ነው ። በቀኝ የተገዙ ሃገሮች ለቀኝ ገዢዎቻቸው አሽከሮች ነበሩ። አሽከርነታቸው ሰዋዊ ክብራቸውን ሙሉ በሙሉ አሳልፎ እስተመስጠት ይደርሳል። በጌቶቻቸው ተደፍረው ያረገዙ ባሮች ከገደል ላይ የሚወረወሩበት ዘመን ነበር ! እኒህ ባሮች አሽከርነቱን በፍቃድ ባያደርጉትም ስንኳ ፥ በታሪክ አሽከር ሁነው ያለፉ ናቸው። ህንዶች ባንድ ወቅት ተገደውም ቢሆን የእንግሊዝ አሽከሮች ነበሩ ፥ እንግሊዝ ደቡብ አፍሪካን ስትወር በባርነት የተያዙ ህንዶች ባምቡ መንጣሪዎች ነበሩ ! ዛሬ የነዛ ህንዶች የልጅ ልጅ ልጆች በደቡብ አፍሪካ ትልቅ ባለ ሃብቶች ናቸው ! ደቡብ አፍሪካን ሃገሬ ፥ ደርባንን የኛ ወደብ ይላሉ ! ደደብ ስለሆኑ ይሆን እንዲህ የሚያስቡት ? ፊሊፒኖዎች በስፓንያርድ ኮሎኒ ስር በወደቁ ጊዜ ፥ የስፔን አሽከሮች ነበሩ ፥ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የመቶ አመት ጦርነት ሲያደርጉ እንደ ዧን ዷ አርክ አይነት ታጋይን ፈረንሳይ ያፈራችው ከባርነት ለመውጣት የቆረጡ ልጆች ስላላት ነበር ፥ እነ ስኮትላንድ ፥ አየር ላንድ እና ወዘተም እንዲሁ የባርነት ግፍ እዳ ቀማሾች ነበሩ ። ቡሮች በወረሯት ደቡብ አፍሪካ ፥ አይናቸውን የጣሉ እንግሊዞች ከቡሮች ጋር ጦርነት ገጥመው ከብዙ ትግል በኋላ ታሸነፏቸው በኋላ ፥ ቡሮቹን ( አፍሪካንስ ( ወይም ደቾች ናቸው )) ባሪያ አድርገዋቸዋል ! ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ጣልያን ኤርትራን በወረረ ጊዜ ፥ በምፅዋ እና አስመራ የሚኖሩ ኤርትራዊያኖች በተወሰነ ደረጃ የጣልያን አሽከሮች ነበሩ ፥ በትግራይም እንዲሁ የትግሬ የጣልያን አሽከር ነበር። አሽከርነቱ ታሪክ ነው ፥ አሽከር ሆኖ መቆየት ግን የግለሰቡ ፍቃድ ነው !
ስለዚህ ውይይቱ መሆን ያለበት ፥ ለምን እንዲህ ትሉናላችሁ ሳይሆን ፥ የተባለው ነገር የነበረ ነው ወይ ? ማስረጃ አለው ወይ ? ምስክር መዛግብቶች መጥቀስ ይቻላል ወይ ፥ ከዚያ ባሻገር እንዲህ ያለው ታሪክ ለነገ ያለው ጠቀሜታው ምንድን ነው የሚሉት ይመስሉኛል አብይ ቁም ነገሮች።
ሃይሌ ላሬቦ ለምሳሌ « ግራኝ መሃመድን » እንደ አንድ ለስልጣን እንደሚዋጋ ኢትዮጵያዊ እንደሚያዩት ተናግረዋል ፥ ምክንያታቸውንም አስቀምጠዋል ። ይህንን ትንታኔያቸውን ልንገረምበት ሳይሆን ፥ ልንመረምረው ፥ አፍራሽ ከሆነ ማስረጆቻችን አቅርበን ልንፋለው ይገባል እንጂ ፥ እንዲሁ በደፈናው « የማሪያም ጠላት » ብሎ መፈረጅ አግባብ አይመስለኝም ! ኢሳትም በውስጡ የታሪክ እውቀት ያላቸው ምሁራኖች ቢኖሩት « ላሩም ለሽንቱም » መግለጫ ከማውጣት እና በማያቀጥነው ሁሉ ከመቅጠን ፥ ሰፊ ውይይቶች አድርጎ ፥ የተሻለ የታሪክ መግባባት እና መረዳት ላይ ታዳሚው እንዲደርስ ባደረገ ነበር ! ይህንን ከማድረግ ይልቅ፥ እንደለመደው በ ሶሻል ሚዲያ ላይ በሚወነጨፉ ተወርዋሪ ማስጠንቀቂያዎች ቅዘን በቅዘን በመሆን ፥ ለለንደኑ ቃለ መጠይቅ ከ ዋሽንግተን ዲስ ማስታባበያ ሲወጣ እያየነው ነው ! ይህ መታረም አለበት ባይ ነኝ! በተጨማሪ የግንቦት ሰባት ከነ ሌንጮ ጋር ያለው ውህደት እንዲህ ባሉ ነገሮች ይፈርስም ስለሚመስላቸው ፥ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የጌቶቻቸውም ቁጣም ይኖርበት ይሆናል ! የጎባጣ አሽከር ሆነና ነገሩ ግንቦት ሰባት ላቅለሰለሸው ኢሳት የሚያስመልሰው ከሆነ ችግር ነው!
በመጨረሻ
ፓፕሎ ፒካሶ ናዚ ሂትለር የስፓኒሽ ከተማን ሲያወድም የሚያሳይ አንድ ኩቢዝም ስዕል ሰርቶ ነበር። የስዕሉ ስም ጉሬንሺያ ይባላል። ታዲያ የቢካሶን ጋለሪ ሂትለር የመጎብኘት እድል አጋጥሞት ነበርና ፒካሶን እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል
አንተ ነህ ይህንን የሰራኸው ?
ፒካሶም ፈጠን ይልና « አይ እንተ ነህ !» በማለት ለሂትለር ይመልስለታል !
እና ምን ለማለት ነው ፥ ሃይሌ ላሬቦ ተናገሩት እንጂ ታሪኩን አልሰሩትም !!!
ኄኖክ የሺጥላ

No comments:

Post a Comment