አኖሌን ምእራብ አርሲ ዞን፣ ጨለንቆ ደግሞ ምስራቅ ሃረርጌ ዞን ያሉ ከተሞች(መንደሮች) ናቸው። በሁለቱ ከተሞች በሚሊኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወጭ ሆኖ ሁለት ሃዉልቶች ተሰርተዋል። ክሊኒክና ትምህርት ቤት ሊገነባበት ሲችል።
በነዚህ ቦታዎች ከመቶ አመታት በፊት ጦርነቶች ተደርገው ነበር። ጦርነቶቹ በአጼ ሚኒሊክ ጦር አሸናፊነት የተጠናቀቁ ናቸው። የሃዉልቶቹም አላማ ታሪክን ለማስታወስ፣ ወይንም ከታሪክ ለመማር ሳይሆን፣ በኢትዮጵያዉያን መካከል ጥላቻን ለመርጨትና ኢትዮጵያን ያቀኑ ታላቅ መሪን ስም ለማጉደፍ ነው።
እነዚህ ሃዉልቶች ምን ያህል የታሪክ መሰረት እንዳላቸው በራሱ አጠያያቂ ነው።
በጨለንቆ ጦርነቱ በጥቂት ሰዓታት የተጠናቀቀ ጦርነት ነበር። በጥቂት ሰዓታት ዉስጥ ያዉም ዘመናዊ ባልሆኑ መሳሪያዎች የተደረገ ጦርነት ብዙ እልቂትም እንዳስከተለ አድርጎ ማቅረቡ በታሪክ አንጻር አያስኬድም። አንድ በሉ።
ጦርነቱ የተደረገው ከኦሮሞ ገዢዎች ጋር አልነበረም፤ ከአዳሉ ገዢ ከሃረሩ ኤሚር አብዱላሂ ጋር ነበር። በሃረር የነበረውን ኤሚር፣ የኦሮሞ ብሄረተኞች እንደ ረቢ(መምህር) የሚቆጥሯቸው ዶር አሰፋ ጀለታ፣ የቱርክ ግብጽና አደሬዎች ጥምረት ( Turko-Egyptian and Adare alliance ) ብለው ነው የሚገልጹት። ይህ ጥምረት ለዶክተር አሰፋ ጀለታ ኦሮሞውን የጨቆነና አደሬዎችን ያፈረጠመ ጸረ-ኦሮሞ ጥምረት ነው። “ The gada system was attacked in eastern Oromia by the Turko-Egyptian and Adare alliance. The interethnic alliance and interdependence between the Adare and the eastern Oromo were shattered when the faction of the former invited the Turko-Egyptian power to colonize the Hararghe region in 1875.132 Under the Turko-Egyptian rule, between 1875 and 1885, the Adare consolidated their power and accumulated wealth and capital at the cost of the majority Oromo.” ሲሉ ነው ዶር አሰፋ የጻፉት። ዶር አሰፋ የ”ኦሮሞ ጠላት” አድርገው ያቀረቡትን አገዛዝ፣ አጼ ሚኒሊክ ማስገበራቸው በምን መልኩ በኦሮሞ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ጥቃት ተደርጎ መወሰዱ በራሱ አስቂኝ ነው። ሁለት በሉ።
የጨለንቆ ጦርነት ከመደረጉ በፊት፣ አጼ ሚኒሊክ ልክ በወለጋና በጂማ እንዳደረጉት የሃረሩ ኤሚር፣ እንዲገብሩና ስልጣኑን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ተማጽኖ አቅርበዉላቸው ነበር። ሆኖም የሃረሩ ኤሚር “ክርስቲያኖች ገናን ስለሚያከብሩ ይዘናጋሉ” በማለት፣ በገና ቀን በአጼ ሚኒሊክ ጦር ላይ ጦርነት ከፈቱ። ሆኖም ተሸንፈው አፈገፈጉ። በጨለንቆ የመጨረሻው ድል ሆነ። እንግዲህ የጨለንቆ ጦርነት በዚህ መልኩ፣ በወቅቱ በነበረው አስተሳሰብ ሰላማዊ የሆኑ አማራጮች ሁሉ በመሟጠጣቸው የተደረገ ጦርነት ነበር። ሶስት በሉ።
በአኖሌ፣ የአጼ ሚኒሊክ ወታደሮች የሴቶችን ጡት ቆርጠዋል በሚል እንደ አቶ ተስፋዬ ገብረአብ ያሉና አንዳንድ የኦሮሞ ብሄረተኞች ሲጽፉና ሲናገሩ ሰምተናል። ሆኖም ይሄን ታሪክ አፈታሪክ ነው ከማለት ዉጭ የጽሑፍ ማረጋገጫ ያቀረበ አንድም አካል የለም። በወቅቱ፣ ከዚያም በፊት የነበሩ ታሪኮችን የዘገቡ ብዙ የሙስሊም ጸሃፊዎች፣ ከአዉሮፓ የመጡ፣ እዚያው አገር ቤት የተወለዱ ነበሩ። ሆኖም አንድም ይሄ በአኖሌ ተደረገ የተባለውን በጨረፍታ እንኳን ( remotely)ያሰፈረ የለም። አፈ ታሪክ ብቻ ነው። አፈ ታሪክም በወቅቱ የነበሩ የአርሲ ተዋጊ መሪዎች ወታደሮች ለመመልመል የነዙትና እና ከመደጋገሙ የተነሳ እንደ እውነት ተደረጎ በአንዳንዶች የተወሰደ ሊሆን ይችላል።አራት በሉ።
እርግጥ ነው በአርሲ ለንጂሶ ዲጋ የተባሉ የአርሲ ኦሮሞ መሪ፣ ለአጼ ሚኒሊክ አልገብርም በማለት ከአራት አመት በላይ ከፍተኛ ትንቅንቅ እንዳደረጉና በኋላ እጅ እንደሰጡ ይነገራል። በጦርነት ብዙ ሰው መሞቱ የማይቀር ነው። በአርሲ ብቻ ሳይሆን በወላይታም ተመሳሳይ የሆነ ጠንክራ ጦርነት አጼ ሚኒሊክ ገጥሟቸውም ነበር።
ሌላ የአርሲ ኦሮሞ መሪ ሮባ ቡቤ ይባሉ የነበሩና በኋላ ሮባ ቡታ የሚል መጠሪያ የተሰጣቸው ፣ ሲጄመር ለአጼ ሚኒሊክ የመገበር ፍላጎት ያልነበራቸው፣ በኋላ ግን በሰላም የገበሩ መሪ ነበሩ። ይሄንን የሚገልጽ ብዙ የጽሁፍ መረጃዎች አሉ። እንግዲህ በአኖሌ ተፈጸመ የተባለው በተፈጸመበት ወቅት የነበሩ የነ ለንጂሶ ዳጋ እና ሮባ ቡታ ገድል በስፋት ተጽፎ፣ የአኖሌ ታሪክ በጽሁፍ አለመቅረቡ በራሱ አጠያያቂ ነው።
ለንጂሶ ዲጋ እና ሮባ ቡታ በአርሲ ኦሮምዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ የነበሩና የተከበሩ መሪዎች ነበሩ። ምንም ጥላቻን እና መከፋፈልን ከመንዛት ዉጭ ለኦሮሞው ማህበረሰብ የማይጠቅመውን የአኖሌና የጨለንቆ ሃዉልቶችን ከማቆም፣ እነዚህን የኦሮሞ መሪዎችን ታሪክ የሚዘክር፣ ያደረጉት አስተዋጾ የሚያስተምር ሃዉልቶች በአርሲ ቢሰሩ ባልከፋ ነበር። አስተማሪም ነበር የሚሆነው።
ከመቶ አመታት በፊት ጠንካራ የኦሮሞ ግዛት በሚባለው በጂማ ይገዙ የነበሩት ኦሮሞው አባ ጂፋር፣ ከአጼ ሚኒሊክ ጋር ስምምነት ስላደረጉ ምንም አይነት ጦርነት በዚያ አልተደረገም። አባ ጅፋር አጼ ሚኒሊክ ከሞቱ በኋላ እስከ 1932 ዓ.ም በጂማ አገረ ገዢ ነበሩ። በወለጋ የለቂ ነቀምቴ ሞቲ ወይም ገዢ የነበሩት ሞሮዳ በቀሬ፣ በሰላም ለራስ ጎበና የአጼ ሚኒሊክ ጦር የጦር አዛዥ ገብረው፣ የወለጋ ገዢ ሆነው መቀጠላቸው ተጽፏል።
አጼ ሚኒሊክ ተነጥለው ይከሰሳሉ እንጅ፣ ከአጼ ሚሊኒክ ጀርባ ሆነው አገሪቷን ያሽከርክሩ የነበሩት በአብዛኛው ኦሮሞዎች ነበሩ። ያለ ኦሮሞዎች የአጼ ሚኒሊክ መንግስት የትም አትደርስም ነበር። የአጼሚኒሊክ ጦር የ”ኦሮሞ” ጦር ነበር ማለት ይቻላል። አጼ ሚኒሊክን ራሱ ከአጼ ቴዎድሮስ ካመለጡበት ጊዜ ጀምሮ ተንከባክበው ጠንክራ ሆነው እንዲወጡ ያደረጉት በዋናነት ኦሮሞዎች ነበሩ።
እንግዲህ በኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ ጦርነቶች ተደርገዋል። ለምሳሌ የተወሰኑትን ብንጠቅስ፡
– በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ግራኝ መሀመድ ድፍን ኢትዮጵያን ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ ጦርነቶች ተደርገዋል። የግራኝ ጭፍጨፋ ለማስታወስ ስንት ሃዉልቶች መሰራት አለባቸው ?
– እነ አጼ አምደጺዮንም ሃዲያ የመሳሰሉትን ሳይቀር በጦርነት አስገብረዋል። ስንት ሃዉልቶች መሰራት አለባቸው ?
– ከዚህ በፊት የተያዘብንን መሬት ለማስለቀቅ እንደሆነ አድርገው ነው የሚናገሩት። ግን ራሳቸው የኦሮሞ ልሂቃን ( እንደ ዶር አሰፋ ጀለታ ያሉ) ከ1522 እስከ 1612 የቡታ ጦርነቶች የሚባሉ አወጀው ኦሮሞዎች እንደተስፋፉ ይገልጻሉ። ዶር አሰፋ ሲጽፉ “ The Oromo fought twelve butta wars between 1522 and 1618, recovering, expanding, and establishing Oromia to its present boundaries.19 In the course of their continued expansion into various regions, different groups established autonomous gada governments” ነበር ያሉት። “recovering” የሚለው ጦርነቱ ለመደረጉ ምክንያት ለመስጠት ተብሎ የቀረበ አጠያያቂ ቢሆንም “ expanding, and establishing “ የሚለው ግን ትክክለኛና ሊሰመርበት የሚገባው። በድፍን ኢትዮጵያ ነው የቡታ ጦርነት የተደረገው። እንግዲህ ስንት ሃዉልት ማሰራት ሊኖርብን ነው ?
– ከሃረሩ ኤሚር ጋር አጼ ሚኒሊክ ብቻ አይደለም የተዋጉት። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የሃረሩ ኤሚር ኑር ኢብን ሙላሂድ በኦሮሞ ተዋጊዎች በጦርነት ተሸንፎ ነበር። በሃረር ሌላ ሃዉልት ሊያስፈለግ ነው ማለት ነው ?
– በዘመነ መሳፍንት ንጉሶች ስም ብቻ እንጂ ስልጣን የነበራቸው መሳፍንቱ ነበሩ። ከመሳፍንት ጠንካራ የሆነ የንጉሱ እንደራሴ ተብሎ ይጠራ ነበር። ከ1828 እስከ 1831 በደብረ ታቦር የንጉሱ እንደራሲ ሆነው የነበሩ የየጁ ኦሮሞው ማሪዬ ተከዜን ተሻግረው በትግራይ ከነበሩ ደጃዝማች ሳባጋዲስ ጋር ባደረጉት ከፍተኛ ጦርነት ብዙ ሰው ሞቷል። በትግራይ መቀሌ ካለው የሰማእታት ሃዉልት በተጨማሪ ሌላ ሃዉልት መሰራት ሊያስፈልግ ነው ማለት ነው ?
– በ1844 የጂማ ኦሮሞ ሞቲ በሲዳማ ጃንጃሮ ግዛት ላይ ጦርነት ከፍቶ ብዙ ሲዳማዎች አልቀዋል። በ3 አመታት በኋላ የጃንጃሮ ንጉሱ መልሶ ከጂማ መንግስት ነጻ ሊወጣ ችሏል። በ1880 አባ ጂፋ የጂማው እንደገና ጦርነት ከፍተዉ የጃንጃሮችን ግዛት ወረው ከግዛታቸው ጋር ጠቅልለዋል። በጃንጃሮ ሃዉልቶች ያስፈለጋሉ ማለት ነው ?
– በ1882 የእምባቦ ጦርነት በሚባለው በሸዋ ንጉስ ሚኒሊክ ጦርና በጎጃም ንጉስ ተክለሃይማኖት ጦር መካከል ከፍተኛ ደም መፋሰስ የነበረበት ጦርነት ተደርጓል። በጦርነቱ ንጉስ ተክለሃይማኖት ይሸነፋሉ። አጼ ዩሐነስ እና ዋግ ሹመ ጎበዜ ወይም አጼ ተክለጊዮርጊስ ከፍተኛ ዉጊያ አድርገው ። ዋግ ሹም ጎበዜ ተሽንፈዋል። በሸዋ አጼ ቴዎድሮስ ከአጼ ሚኒሊክ አባት ንጉስ ሃይለመለኮት ጋር ተዋግተው ሸዋን አስገብረዋል።
የሰገሌ ጦርነት በሚባለው በኦሮሞው የወሎ ንጉስ ሚካኤል እና በጨቦ ኦሮሞ ፊታወራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ(አባ መላ) መካከል የተደረገው ጦርነት በአባ መላ አሸናፊነት ተጠናቋል።
የሰገሌ ጦርነት በሚባለው በኦሮሞው የወሎ ንጉስ ሚካኤል እና በጨቦ ኦሮሞ ፊታወራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ(አባ መላ) መካከል የተደረገው ጦርነት በአባ መላ አሸናፊነት ተጠናቋል።
እንግዲህ እንዲህ እያልን እጅግ በጣም ብዙ የጦርነት ታሪኮችን መዘርዘር እንችላለን። ለዚያ ሁሉ ጦርነቶች ሃዉልት ልናቆም ነው ማለት ነው ?
የአገራችን ብቻ ሳይሆን የሌሎች አገሮች ታሪኮችም የጦርነት ታሪኮች ነው። አገሮች የተገነቡት በጦርነትና በመስፋፋት ነው። የድሮ ዘመን ሰዎችን አሁን ባለን ሊበራል ዴሞክራሲ አስተሳሰብ መመዘኑ ደካማነት መሆኑን ተረድተን፣ ተበደልኩ፣ ጦርነት ተከፍቶብኝ ነበር ያለ ሕዝብ እርሱም በሌላ የታሪክ አጋጣሚ ጦርነት የከፈተና የበደለ መሆኑ አስበን፣ ስንት የከፉ ጦርነቶች እያሉ ሁለቱን ብቻ ነጥሎ በማውጣትና ሃዉልት በማቆም፣ አንድ ማህበረሰብ ብቻ ለማጥቃት የሚደረገው ደባ ቆሞ፣ በዚህም ሆነ በዚያ ሁላችንም አሁን ኢትዮጵያ በምትባል አንዲት አገር ዉስጥ ያለን መሆናችንን ተረድተን፣ ከዘረኝነት በጸዳ መልኩ ተያይዘን፣ ተከባብረን በፍቅር አገራችንን ብንገነባ ነው ይሻላል። ከታሪክ እንደምንማረው አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ከአማራው፣ ከትግሬው ባልተናነሰ የኦሮሞው አሻራ አለበት። ኦሮሞነት ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮዮጵያዊነትን የሚጠላ ኦሮሞ ኦሮሞ አይደለም። ታሪክን የማያውቅ፣ በጥላቻ የታወራ የዉሸት ኦሮሞ ነው።
No comments:
Post a Comment