Monday, January 30, 2017

የባቡሩም የስኳሩም… ያስደነግጣል! ( ኤልያስ )

 


የባቡሩም የስኳሩም… ያስደነግጣል! ( ኤልያስ )
“ፊዚቢሊቲ ስተዲ” እንኳን ለፕሮጀክት … ለትዳርም ያስፈልጋል
ባለፈው ረቡዕ ለንባብ የበቃው የአማርኛው “ሪፖርተር” ጋዜጣ በፊት ገፁ ላይ ያወጣው ዜና በእጅጉ ያስደነግጣል፡፡ (እንኳን ተበዳሪን … አበዳሪንም ጭምር!) ርዕሱ እንዲህ ይላል፡- “የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበጀት ዕጥረትና የዕዳ ጫና ፈተና ውስጥ መሆኑን ይፋ አደረገ” ጋዜጣው ላይ የወጣው የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ጌታቸው በትሩ ፎቶግራፍም የዜናውን ድባብ  የሚገልፅ ነው (ድንግጥ ብለዋል!) እውነት ለመናገር ፎቶግራፈሩን አድንቄዋለሁ!፡፡
በነገራችን ላይ … ገና ወደ ውስጥ ሳንገባ፣ ከርዕሱ በላይ የተደረደሩት ቁጥሮች (ዕዳዎች ማለቴ ነው!) የኛ ብቻ ሳይሆን፣ “የሶማሊያንም የሚጨምር ይመስላል፡፡ (ግን እሷ ደግሞ ባቡር የላትም!)
“የዕዳ ክምችቱ 102.5 ቢ. ብር ደርሷል”
“የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኪሳራ 1.8 ቢ. ብር ነው፡፡”
“የቦንድ ሽያጭ ብድር 17.6 ቢ. ብር ደርሷል።”
የሚገርማችሁ ደግሞ መረጃውን ራሱ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ነው ይፋ ያደረገው። (ወዶ ይሁን ተገዶ አልታወቀም!) የጋዜጣው ዘገባው ይቀጥላል፡- “የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የፋይናንስ እጥረትና የብድር ግዴታ ክፍያዎች የ2009 ዓ.ም ፈተናዎች እንደሆነበት፣ በይፋ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የመንግስት ልማት ድርጅት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳወቀ” ይላል፡፡ (የምን ዱብ ዕዳ ነው?!)
“ለበጀት ዓመት የገንዘብ ፍላጎት ታሳቢ የተደረጉት 25.9 ቢሊዮን ብር ወይም 43 በመቶ ከውጭ አገር የፋይናንስ ምንጭ በብድር፣ ቀሪውን 34.3 ቢሊዮን ብር ወይም 57 በመቶ ከአገር ውስጥ ምንጮች ለመሰብሰብ ነበር” የሚለው ዘገባው፤ ከውጭ ብድር ይገኛል የተባለው እስካሁን አለመገኘቱን ጠቁሞ፣ ከአገር ውስጥ ይገኛል ተብሎ የታቀደው 10.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ከየት ሊገኝ እንደሚችል መታወቁን ገልጿል – ብሏል፡፡ (የአገር ውስጡም ቢሆን እርግጠኛ አይመስልም!)
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ስለ ስኳር ፕሮጀክታችን መጓተት አውስተው ሲያበቁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የባቡር ፕሮጀክቶቹ (የአዲስ አበባውም ይሁን የጅቡቲው) በአመርቂ ስኬቱ (በፍጥነት መጠናቀቁንም ይጨምራል!) ተጠቃሽ መሆኑን፣ በዓለም ላይ በዚያ ፍጥነት የሀዲድ መስመር ዘርግቶ ያጠናቀቀ እንደሌለ በመግለፅ … ደረታችንን እንድንነፋ የልብ ልብ ሰጥተውን ነበር፡፡
ለተጓተተው የስኳር ፕሮጀክትም ማካካሻ ሆኖን ነበር፡፡ (‹‹ባቡሬ መፅናኛዬ›› ዓይነት!) ግን እንዳለመታደል ብዙም ሳንቆይ… ባቡሩ የዕዳ ክምር እንዳለበት በይፋ ተነገረን (አናሳዝንም!) እናላችሁ …  “በአጠቃላይ የኮርፖሬሽኑ የዕዳ ክምችት በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ከነበረበት 95.97 ቢሊዮን ብር፣ ወደ 105.52 ቢሊዮን ብር አድጓል” ይላል – የሪፖርተር ዘገባ። (ዱብዕዳ ነው!) በኋላ ላይ ግን ከዕዳውም በላይ ያስገረመኝ የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስኪያጅ የገለጡት የማይታመን እውነታ ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፡- “የባቡር ፕሮጀክቶቹ ሲጀመሩ ዕዳ ውስጥ እንደሚገቡ ይታወቅ ነበር፡፡ እንደዚህ ያለ ፕሮጀክት ውስጥ ደፍረን የገባነው መውጫ እንፈልጋለን በሚል መርህ ነው” (ዓይን እያየ ዕዳ ውስጥ!) እኔ የምለው ግን በየፕሮጀክቱ በድፍረት መግባት ፋሽን ሆነ እንዴ?!
የሚቀጥለው አንድ ዓመት ለኮርፖሬሽኑ ፈተና እንደሚሆንበት የተናገሩት ዶ/ር ጌታቸው፤ በ2018 ግን መፍትሄ አለኝ ባይ ናቸው፡፡ (የተጠና ነው ያልተጠና?!) “የ2018 መውጫ መንገድህ ምንድን ነው ካላችሁ፣ የባቡር መስመሩን ከቱሪዝምና ከመሳሰሉት እሴት የሚጨምሩ ቢዝነስ ስራዎች ጋር እናቀናጀዋለን” በማለት ለም/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አብራርተዋል – ሥራ አስኪያጁ፡፡ (ይሄ የበለጠ አስፈራኝ!) እዚህኛውም ውስጥ ያለ ጥናት ቢገቡበትስ?!
የኮርፖሬሽኑ ኃላፊ እንደ መፍትሄ ካቀረቧቸው ሀሳቦች ውስጥ ለእኔ የተዋጠልኝ የመጨረሻው ብቻ ነው፡፡ (“ጨለምተኛ” የሚለውን ፍረጃ አልወደውም!) እናም … ዋና ሥራ አስፈፃሚው ምን አሉ መሰላችሁ? “የከፋ ነገር ቢመጣ ደግሞ የኮርፖሬሽኑን የተወሰነ ድርሻ ለውጭ ኢንቨስተሮች በመሸጥ የዕዳ ጫናውን መቀነስ ይቻላል” ዕዳ የተከመረበትን የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የ6 ወር ሪፖርት ያደመጠው የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ … ምን ቢል ጥሩ ነው? ትችትና ተግሳፅ ግን እንዳትጠብቁ፡፡  (“በርቱ አንበሶቼ!” ነው ያላቸው፡፡)
እንደውም የኮርፖሬሽኑን የፕሮጀክት አፈፃፀም አድንቋል፤ ቋሚ ኮሚቴው፡፡ ያልተጠናቀቁ ቀሪ ስራዎች እንዲያልቁም አሳስቧል ተብሏል፡፡ በተረፈ ግን … “ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመሆን የገንዘብ ችግሩ መፈታት አለበት” ብሏል፡፡  ግን ሌላው ቢቀር… የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ፤ “የባቡር ፕሮጀክቶቹ ሲጀመሩ ዕዳ ውስጥ እንደሚገቡ ይታወቅ ነበር፤ እንደዚህ ያለ ፕሮጀክት ውስጥ ደፍረን የገባነው መውጫ እንፈልጋለን … በሚል መርህ ነው” ሲሉ የተናገሩት ብቻውን … ፓርላማውን ሙሉ ቀን አያከራክረውም? በነገራችን ላይ የአስሩ የስኳር ፋብሪካዎች … ለአስር ዓመት መዘግየትና የ70 ቢ. ብር ኪሳራም … መንስኤው ሌላ ሳይሆን ‹‹በድፍረት ዘሎ መግባት›› መሆኑን … ጠ/ሚኒስትሩ በቅርቡ ለፓርላማ ሲያስረዱ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ በአንድ ጊዜ 10 የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች መጀመራቸው … ፋብሪካዎቹ እንዲቋቋሙ የተመረጡባቸው ቦታዎች አስቸጋሪነት … የአቅምና የባለሙያ ውስንነት … ፕሮጀክቱን እንዳጓተቱ አስረድተዋል። (ሁሉም ግን ራሱ መንግስት የፈጠራቸው ችግሮች ናቸው!!) በእነዚሁ ሁሉ ችግሮች ላይ ደግሞ “የአዋጭነት ጥናት” (feasibility study) ሳይሰራ በድፍረት በቀጥታ ወደ ፕሮጀክቶቹ ተገባ፡፡ (Adios! አለ ፈረንጅ!) ከዚያስ ውጤቱ ምን ሆነ? 10 ዓመት ሙሉ ጠብ የማይል የስኳር ፕሮጀክት!! (ላም አለኝ በሰማይ…!) እና .. እዚህ ገባ የማንለው የ70 ቢ. ብር ኪሳራ!! (ይሄም የብድር ዕዳ ሆኖ ብቅ ማለቱ አይቀርም!) እኔ አሁን እንደገባኝና ጠ/ሚኒስትሩም በፓርላማ ሊያስረዱ እንደጣሩት … በስኳር ፕሮጀክቶቹ ላይ የጠፋው ገንዘብና የባከነው ጊዜ፣ አገራዊ አቅምን ለመገንባት እንደዋለ ብንቆጥረው ነው የሚሻለው!”  (‹‹ውሾን ያነሳ ውሾ ነው!”)
ዋናው ቁም ነገር ግን የቢዝነስ ፕሮጀክት ውስጥ… ትዳር ውስጥም Feasibility Study ሳይሰራ ዘው ተብሎ አይገባም፡፡ (ፍቺ ይከተላላ!) ሽማግሌዎች እንኳን “ተጠናንታችኋል?” ይላሉ-ወጣቶች ትዳር ለመያዝ ሲቸኩሉ! (“ፊዚቢሊቲ ስተዲ ማለታቸው ነው!”)

No comments:

Post a Comment