በሰበታ ማየት ለተሳናቸው ያሰሩት ባለ 120 አልጋ ሆስፒታል በቅርቡ ይመረቃል
3 ትላልቅ አምቡላንሶችን ለሆስፒታል ለግሰዋል ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ›› ለተባለው ማህበር 1ሚ.ብር ሰጥተዋል
ግሪካዊው ሚስተር ባምቢስ ቺማስ ከአገራቸው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በ1944 ዓ.ም ነው።ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ገና የ21 ዓመት አፍላ
ወጣት እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ ባምቢስ ሱፐር ማርኬትን ከከፈቱበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 65 ዓመታት አካባቢው በስማቸው መጠራቱ ደስታ
እንደሚሰጣቸውና እሳቸው ካለፉም በኋላ፣ስማቸው ለዘላለም ኢትዮጵያ ውስጥ መቀጠሉን ሲያስቡት ኩራት እንደሚሰማቸው ይገልጻሉ፡፡ ሚስተር ባምቢስ፤ከሱፐር ማርኬት ስራቸው ጎን ለጎን ኢትዮጵዊያንን ለማገዝ በርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ። ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ››ለተሰኘው የኩላሊት ህሙማን ማህበር ሰሞኑን የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ለማህበሩ ያደረጉትን
ድጋፍና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ ያነጋገረቻቸው ሲሆን ለኢትዮጵያ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርም በጥልቀት አጫውተዋታል- “ልቤን
ብትከፍቺው ኢትዮጵያዊ ነኝ” በማለት፡፡ ሌላስ? እነሆ ቃለ ምልልሱን፡-
————
ሰሞኑን 1 ሚ. ብር ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ›› ለተሰኘው ማህበር፣ በሮተሪ ክለብ በኩል ለግሰዋል፡፡ ለምን በሮተሪ በኩል መለገስ ፈለጉ?
እኔ በሮተሪ ክለብ በኩል ብሩን የሰጠሁት ክለቡ ተጨማሪ ገንዘብ ለህሙማን እንዲሰበስቡ ለማበረታታትና ህሙማኑ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እንጂ ሌላ የተለየ ዓላማ ኖሮኝ አይደለም፤ ለማህበሩም በቀጥታ ማስገባትና መስጠት እችል ነበር፡፡
ብሩን ለመለገስ ማህበሩን እንዴት መረጡት?
የማህበሩ መስራች አቶ ኢዮብ ቀጥታ አነጋገረኝ፡፡ የኩላሊት ህመም በአሁኑ ወቅት ፋታ የሚሰጥ ህመም ስላልሆነ የምችለውን ለማድረግ ወደ ኋላ አላልኩም። እርግጥ እኔ የሰጠሁት 1 ሚ. ብር ከአራት የኩላሊት እጥበት ማሽን በላይ አይገዛም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከ200 እና 300 መቶ ማሽን በላይ ያስፈልጋል። በዚህ በኩል ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት፡፡ ሁሉም የድርሻውን ቢወጣ፣ራስ ወዳድነት ቢጠፋ፣ በኩላሊት ህመም የሚሰቃይ አንድም ወገን አይኖርም ነበር፡፡ እኔ ከ65 ዓመት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሬያለሁ፤ ልቤን ብትከፍቺው ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ስለዚህ ወገኖቼ ልጆቼ ሲሰቃዩ ማየት ያመኛል። ወገናዊነቴን ለማሳየት የምችለውን እያደረግሁ ነው፤ ሌላውም የበኩሉን ማድረግና ወገኖቻችንን ከስቃይ መታደግ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚህ በፊት በበጎ አድራጎት ስራ ተሰማርተው ያውቃሉ?
የምችለውን እያደረግሁ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰበታ ውስጥ ለአይነ ስውራን ህክምና የሚያገለግል ሆስፒታል ሰርቻለሁ፡፡ የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ነበሩ፡፡ 5 ሚ. ብር ወጥቶበታል፡፡ 120 አልጋዎች ያሉትና ባለ ሶስት ፎቅ ነው፡፡ በቅርቡ ክቡር ፕሬዚዳንቱ መርቀው ይከፍቱታል፡፡ ሌላው ከዚህ ቀደም ሶስት ትልልቅ አምቡላንሶችን ለሁለት ሆስፒታሎች ለግሻለሁ፡፡ ሁለቱን ለፖሊስ ሆስፒታል፣ አንዱን ደግሞ ለየካቲት ሆስፒታል፡፡ በህይወት እስካለሁ ድረስ ለወገኔ የምችለውን በማድረግ እቀጥላለሁ፡፡
ሱፐር ማርኬቱ ብቻ ሳይሆን አካባቢውም ጭምር በእርስዎ ስም ነው የሚጠራው —–
እኔ ይህን ሱፐር ማርኬት ለመክፈት ህንጻውን ስሰራ፣ አንድም ቤት በአካባቢው አልነበረም። ጫካ ብቻ ነበር፡፡ ቤቱን እዚህ ስሰራ፣ ባምቢስ አበደ ነበር የተባለው፡፡ ጅብ ይበላዋል ተብዬ ነበር። ቀስ በቀስ አካባቢው እየለማ፣ ቤቶች እየተሰሩ መጡ። እኔ የመጀመሪያው ስለነበርኩ አካባቢው በእኔ ስም ተጠራ፤ እስካሁን ቀጥሏል፡፡ ባንኩ ባምቢስ ቅርንጫፍ ይባላል፤ መንገዱና አካባቢውም እንደዛው፡፡ እኔም ባልፍ አካባቢው በስሜ መጠራቱ ለዘላለም ይቀጥላል፤ ይሄንን ሳስብ ደስታ ይሰማኛል፤ እኮራለሁ፡፡
እዚሁ ትዳር መስርተው፣ ልጆች አፍርተዋል አይደል——–
በደንብ እንጂ! ባለቤቴ እዚሁ አዲስ አበባ ሰንጋተራ የተወለደች ግሪካዊት ነች፡፡ አራት ሴት ልጆችን ወልጃለሁ፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም በታተነን እንጂ ከ5 ሺህ በላይ ግሪካዊያን ነበርን፤ እዚህ አገር። አሁን 50 ብንሆን ነው፡፡ ልጆቼ እዚያም እዚህም ይኖራሉ፤ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ምግብ እንኳን ሽሮ ሰርተው በእጃቸው እንጂ በማንኪያ አይመገቡም፡፡ እዚህ ብቻ አይደለም፤ እዛም ግሪክ በእጃቸው ነው የሚመገቡት፡፡ ብቻ ኢትዮጵያን እወዳታለሁ፡፡ ሞቴም መቃብሬም እዚሁ ነው የሚሆነው፡፡
አሁን 86 ዓመትዎ ነው፡፡ ነገር ግን ጡረታ አልወጡም?
(ረጅም ሳ…ቅ) እኔ አንደኛዬን ነው ጡረታ የምወጣው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ጡረታ ሲወጣ፣ ከመስሪያ ቤቱ ለጡረታ ያስቀመጠውን ገንዘብ ወስዶ እየበላ ይኖራል፡፡ እኔ ህይወቴ በዚህ ስራ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ጡረታ የምወጣው ያው አንደኛዬን ወደ ሌላው ዓለም ስሄድ ነው፡፡ ምን አይነት ጥያቄ ነው እባካችሁ?
ከዚህ ሱፐር ማርኬት ውጭ ሌላ ቢዝነስ ላይ አልተሰማሩም?
በፍፁም! ይሄው ነው፡፡ ልሰማራ ብፈልግ ታዋቂ ስም አለኝ፤ ነገር ግን አልፈለግኩም፡፡ ስራዬም የገቢ ምንጬም ይሄ ሱፐር ማርኬት ነው፤ በቂዬም ነው፡፡
አሁን ጤናዎት እንዴት ነው?
ጤናዬ ምንም አይልም፤ደህና ነኝ እንደምታይኝ፤ ሁሌም ስራዬን በንቃት እሰራለሁ፡፡ እግዜር ይመስገን —– ጥሩ ነኝ፤ የኢትዮጵያ አየር ጥሩ ነው፡፡ ምግቡ ተስማሚ ነው፤ ስለዚህ ደህና ነኝ፡፡
ከኢትዮጵያ ባህል የትኛው ይበልጥ ይማርክዎታል?
ሁሉም ይማርከኛል፤ መደጋገፉ አብሮ መብላቱ፤ ሁሉም፡፡ እኔ ሃይማኖቴ ኦርቶዶክስ ነው፤ 20 ያህል የክርስትና ልጆች አሉኝ፡፡ በጣም ትልልቅ ሆነዋል፤ አሜሪካና በሌላው አለም አሉ። እኔ የቆዳዬን መንጣት አትመልከቺ፤ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬሻለሁ፤አኗኗሬም አመጋገቤም የኢትዮጵያ ነው፡፡ ደግሞም ቆዳችን ነጭ፣ ጥቁር፣ ቢጫ ቢሆን —- የአንድ የእግዚያብሄር ልጆች ነን፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ባህል ሁሉም ያስደስተኛል። እዚህ በኖርኩባቸው በርካታ አመታት ደስተኛ ሆኜ ነው የኖርኩት፤ እየኖርኩም ያለሁት፡፡
በመጨረሻ እውን ሆኖ ማየት የሚፈልጉት ነገር አለ?
እኔ ህልሜ፣ የኩላሊት ህመምተኞችን እፎይ የሚያሰኝ ትልቅ ተቋም ተመስርቶ ማየት ነው፡፡ ይህን አይቼ ብሞት፣ በሰላም የማርፍ ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለውን የኩላሊት ህመምተኞች ስቃይ ያየ፣ በሰላም የሚተኛ አይመስለኝም፡፡ ብንተባበር እኮ ልናግዛቸው ልንረዳቸው እንችላለን፡፡ ይሄ ተቋም እውን እንዲሆን የምችለውን አድርጌ ብሞት አይቆጨኝም፡፡
ለሮተሪ ክለቦችም ብር እንዲፈላልጉና፣ይሄንንም የሰጠሁትን ብር በአግባቡ ለታማሚዎቹ ማሽኑ ተገዝቶ ጥቅም ላይ እንዲውል አደራ ብያቸዋለሁ። ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ›› ማህበር መስራች አቶ ዳዊት፣ ማሽኖቹ ተገዝተው፣ ዘውዲቱ ሆስፒታል እንደሚገቡና አገልግሎት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል፡፡ ወደፊትም ውጤቱን እያየን የምንችለውን እናደርጋለን፡፡
No comments:
Post a Comment