ከሙሉቀን ተስፋው
በከተማ አስተደደሩ ፖሊስ ጽ/ቤት ውስጥ ሾልኮ የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ማንነታቸው ያልታወቁ 112 ሰዎች በጥይትና በድብደባ ተገድለው ተገኝተዋል፡፡ ከዐማራ ልዩ ኃይል ፖሊስ ደብረ ታቦር ምድብ እና የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽ/ቤት ካሉ ሠራተኞች ማረጋገጥ እንደተቻለው በርካታ ሰዎች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተገድለው ተገኝተዋል፡፡ መረጃውን የሰጡን የፖሊስ አባላት ‹‹ከዚህም ቀደም አፍልፎ አልፎ ሰዎች ሞተው የሚገኙ ቢሆንም ሕዝባዊ ተጋድሎው ከተጀመረበት ከነሐሴ ወር ወዲህ ግን የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር አሳሳቢ በሆነ መልኩ ጨምሯል›› ብለዋል፡፡
አብዛኛዎቹ ሟቾች የተገደሉት በጥይት እንደሆነ የሚያመልከተው መረጃ አስከሬኖች ከሌላ ቦታ ተገድለው መንገድ ላይ ሊጣሉ እንደሚችሉም ተጠቁሟል፡፡ የሟቾችን ማንነት ለመለየት የሚያስችል መታወቂያም ሆነ ማንኛውም ዓይነት መረጃ ስለማይኖር የሟቾችን ማንነት መለየት አልተቻለም ተብሏል፡፡ የተገደሉበትን ምክንያት ለማወቅ የሚደረግ የአሻራና የአስከሬን ምርመራም ተደርጎ እንደማያውቅ ነው የተነገረው፡፡
በአጅባር፣ ሐሙስ ገበያ፣ ሰኞ ገበያ፣ ታቦር፣ አይጋጥ፣ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጀርባ፣ አባ በላይ ውኃ የመሳሰሉ ሰፈሮች አስከሬን በሌሊት ተጥሎ ከሚገኝባቸው ሰፈሮች ዋነኛዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡ አስከሬኖቹ የማይታወቁ ከሆነ ከየት እንደመጡና በማን እንደተገደሉ ግምታቸውን ሲያስቀምጡ ‹‹ምናልባት ከጎጃም ወይም ከሰሜን ጎንደር ራቅ ካሉ አካባቢዎች ታስረው በደኅንነት ወይም በኮማንድ ፖስት ተገድለው ማንነታቸውን አጥፍተው ጥለዋቸው ሊሆን ይችላል›› ብለዋል፡፡
በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ለማጣራት ምንም ሙከራ ያልተደረገ ከመሆኑም በላይ በየቀኑ የሚነሳ አስከሬን እና የተበላሸ ሰውነት ሰላማቸውን እንደነሳቸው ጭምር የፖሊስ አባላቱ ገልጸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment