Friday, February 17, 2017

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር አከላለል ጉዳይ በመቀሌ እየተመከረበት ነው




BBN News በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር መካከል ያለውን አከላለል እና ችግሮች በተመለከተ በመቀሌ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ በዛሬው ዕለት በተጀመረው በዚሁ ውይይት ላይ የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት የታደሙ ሲሆን፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ክልሎች ባለስልጣናትም የውይይቱ ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በዚህም መሰረት ከሱዳን በኩል የገዳሪፍ፣ የጥቁር አባይ፣ የሴናር እና የከሰላ ግዛቶች ኃላፊዎች ሲታደሙ፣ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የትግራይ፣ የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ኃላፊዎች ተወክለዋል፡፡
ይኸው ስብሰባ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ ያለውን ተደጋጋሚ ግጭት ለማስቀረት የታለመ ነው ቢባልም፣ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ግን፣ የሱዳን ባለስልጣናት ወደ ኢትዮጵያ ተወስዶብናል የሚሉትን መሬት ለማስመለስ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ድንበሮቻቸውን ለማካለል ከሁለት ዓመታት በፊት ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ሲሆን፣ ሆኖም ስምነቱ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስደፈረ እንደነበር በወቅቱ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ይህን ስምምነት በጽኑ ሲቃወሙት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
መሬታችን በኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ተወስዶብናል የሚሉ የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በመግባት የአማራ ክልል አርሶ አደሮችን ሰብል አውድመው በመውጣት ተደጋጋሚ ጥቃት መፈጸማቸው ይታወቃል፡፡ እነዚሁ ሰርጎ ገቦች በአካባቢው የሰፈሩ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን በማፈናቀል ጥቃት ሲያደርሱ መቆየታቸውን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

No comments:

Post a Comment