Thursday, February 16, 2017

የክስ ቻርጅ ያልቀረበባቸው ዶክተር መረራ ጉዲና በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ጠበቃቸው ዶክተር ያዕቆብ ገለጹ

   


የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበርና የመድረኩ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር በመገናኘት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሶስት ወር የሞላቸው ሲሆን ጤንነታቸው አለመታወኩን ጠበቃቸው ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም ለሰንደቅ ጋዜጣ ገለፁ።
የደንበኛቸውን የጤንነትና የምርመራ ሁኔታ የተጠየቁት ዶክተር ያዕቆብ “በሳምንት ለሁለት ቀናት (ረቡዕ እና ዓርብ) ለ30 ደቂቃዎች እኔና ሌላኛው ጠበቃቸው አቶ ወንድሙ ኢብሳ እንድናነጋግራቸው በተፈቀደልን መሰረት እየጎበኘናቸው ነው። ጤንነታቸው በተመለከተ ደህና መሆናቸውን ነግረውናል” ሲሉ የዶክተር መረራ ጤንነት በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ዶክተር መረራ በቁጥጥር ስር ውለው በቀድሞ ማዕከላዊ የምርመራ ጣቢያ የሚገኙ ሲሆን ላለፉት ሶሰት ወራት ለሶስት ጊዜ ፍርድ ቤት ቢቀርቡም እስካሁን የክስ ቻርጅ አለመነበቡን የገለጹት የህግ ባለሙያው “በተለይ በሶስተኛው ቀጠሯቸው የክስ ቻርጁ መነበብ እንዳለበት ለፍርድ ቤቱ ብናቀርብም አቃቢ ህግ የሰውና የሰነድ ማስጃዎችን አሰባስቤ አልጨረስኩም በማለቱ ዳኛው ለአራተኛ ጊዜ በደንበኛዬ ላይ ቀጠሮ ሰጥተዋል” ሲሉ ገልጸዋል።
የዶክተር መረራ ጉዲና ቤተሰቦች ስንቅ ከማቀበል በዘለለ ለማነጋገር ያልተፈቀደላቸው መሆኑን የገለጹት ዶክተር ያዕቆብ ደንበኛቸው የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል። ዶክተር ያዕቆብ አክለውም “ዶክተር መረራ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ሰሞን ከእኛ ጋር የምንገናኘው እጃቸውን በካቴና ታሰረው ነበር። ሆኖም ይህ ድርጊት ተገቢ አለመሆኑን በመገናኛ ብዙሃን ከገለጽኩ በኋላ እጃቸውን በካቴና ሳይታሰሩ ነው የምናገኛቸው” ብለዋል።

No comments:

Post a Comment