Saturday, February 18, 2017

ህወኃት /ኢህአዴግ ሆይ – ‹‹ ጀምበር ሳለች እሩጥ-

   



ህወኃት /ኢህአዴግ ሆይ – ‹‹ ጀምበር ሳለች እሩጥ- (2) ›› //
ዛሬም ባለፈው በጻፍኩት ‹ምክር› መግቢያ  ባልኩት ‹‹ እኔን የሚያሳስበኝ የዛሬው ዘረኛ ገዢ ቡድን መወገድ አይደለም፡፡ ይህ አገዛዝ የሚወገድበት መንገድ ነው፡፡ በተለመደው  ከሆነ – ማለትም ይህን አገዛዝ አጥፍተን ቀብረን በከርሰ መቃብሩ ላይ አዲስ ሥርዓት ለመገንባት ከሆነ ለውጥ አይደለም፡፡ እንዲሁም በከርሰ መቃብሩ ላይ የለማች ፣ የበለጸገች ፣ የሰው ልጆች መብት የተከበሩባት ፣ ሁሉም ከችግር ወጥቶ ተብነሽንሾ የሚኖርባትን  … ኢትዮጵያ በቀላሉና ያለችግርና ፈተና   በማግስቱ ተገንብታ የምናገኝ/ ወይም የምንገነባ  የሚመስለን ከሆነ አሁንም የምንጠብቀውን የምንታገልለትን ዓላማ የተረዳነው በተሳሳተ መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ›› በሚለው ልጀምር፡፡
ያለፈው ደርግ አገዛዝ በህዝብ ትግል ተገርስሶ  በባለ ጠብመንጃው ህወኃት/ኢህአዴግ ተቀብሮ ፣ ብሶት ወለደኝ ያለን  ሥልጣን ላይ እንደወጣ የተገቡልንን ቃላት እና ያለንበትን እውነት በማሳየት ከላይ የተቀመጠውን  ሃሳብ ለማስረገጥ አንዳንድ ነገሮችን በአጭር ላንሳ፡- በጥቅል ፕሮፖጋንዳና በህዝብ ሕይወት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የተለያዩ ናቸው፡
  1. ምርትና ምርታማነት፣  የሁለት አሃዝ/ ዲጅት ተከታታይ ዕድገት ፡- አዎን ዝናብ ጠብቀን በበሬ እያረስን በየዓመቱ በሚሊዮኖች እየተራቡብን ባለው ሁኔታ የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር ሥልጣን ላይ እንደወጡ   ‹‹ በቀጣይ አስር ዓመታት ህዝባችንን ሶስት ጊዜ እናበላለን ››፣ ቀጥለውም ‹‹ በምግብ እህል ራሳችንን ችለን በቆሎ ለጎረቤት አገሮች መሸጥ ጀምረናል›› እንዳሉት ለሌላው  መሸጡ ቀርቶ ህዝባችንን ማብላት ቀላል አይደለም፡፡ እንዲህ መዋሸት ይቻላል፤ ግን ለውጥ ካሰብን እነርሱ/አገዛዞች በጠገቡት ህዝብን ‹ጠግበሃልና  አግሳ› ፣ ምርታማነታችን አድጎ በሄክታር ይህን ያህል ደረሰ፣ በዚህ መቶኛ አደገ፣ ተመነደገ ማለት  እንጂ  ረሃብን ማጥፋት አይቻልም፡፡ለዚህም በየዓመቱ የልመና አቁማዳ ይዞን የመዞራችን ሃቅ፣ በሴፍቲኔት የሚኖሩ ዜጎች ብዛት፣ ድርቅ ኮሽ ባለ ቁጥር በሚሊዮኖች ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ መዳረጋቸው፣… የሚያረጋግጠው ነው፡፡ በመሆኑም   ነገ ማንም ቢመጣ እነዚህን ዓይነት ችግሮች በበነጋውና  ያለህዝብ ተሳትፎ በራሱ/በመንግስት ብቻ ያስወግዳል ማለት አይደለም ፡፡ የዜጎች መብት ባልተከበረበት፣ የህግ የበላይነት ባልሰፈነበት፣ ዜጎች የአገሪቱን ችግሮች ተረድተውና ነባራዊና ተጨባጩን ሁኔታ ተቀብለው   ለመፍትሄው በጋራ ለመስራት ባልቆረጡበት ፣ …… በአገራቸው ሉዓላዊነትና በራሳቸው ክብር ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ባልተመለሰበት … ምርትና ምርታማነትን አፍነው /ሰንገው የያዙ ፖሊሲዎች ባልተስተካከሉበት … በፕሮፖጋንዳ፣  በኃይል አፈና፣፣ …. ዘላቂ መፍትሄ አይመጣም ነው፡፡ ፕሮፖጋንዳ  እንጀራ አይሆንም፡፡
  2. ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፡- ህወኃት/ኢህአዴግ በአገራችን  ከመቼውም ጊዜ በላይ ተከብረዋልል ይለናል፡፡ ህዝቡ ደግሞ ከዕለት ተዕለት ኑሮው ተነስቶ ‹ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ› እያለ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ቢገፋም አሁን ግን ‹ቀልዱን ተዉት› በማለት ከዳር አስከዳር ማለት በሚያስችል ሁኔታ ‹ እምቢኝ › በማለት ተነስቷል፡፡ ለዚህ ህዝባዊ የበቃኝ ህዝባዊ እንቅስቃሴ መንግስት/ገዢው ፓርቲ ራሱን  ወደ ውስጥ ከመመልከት ይልቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተቃውሞውን ለማፈን የሚያደርገው ሁሉ ለጊዜው እንቅስቃሴውን ያረግበው እንደሆን እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣ ለመናገር የፖለቲካ ተንታኝነት ወይም ነቢይነት አይጠይቅም ፡፡ ከያቅጣጫው የሚሰማው የህዝብ ብሶት ፣ በየማጎሪያው በዜጎች ላይ የሚፈጸመው አሰቃቂና ዘግናኝ ኢሰብዐዊ ድርጊት /ቶርቸር / ከእኛ አልፎ በዓለም  አደባባይ የዋለ ተጨባጭ ሃቅ ነው፡፡ ዜጎችን በፖለቲካ አመለካከታቸው እያሰሩና እያሰቃዩ፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን እያቀጨጩ ወይም እያጠፉ የሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ  መብት ጠበቃ ነኝ ማለት በህዝብ ላይ ከማሾፍ የዘለለ፣ ወይም ህዝብን ከመናቅ የተለየ ትርጉም  የለውም፡፡ ህዝብን እያሰቃዩና እያፈኑ መብትህ ተጠብቆልሃል ማለት ፣ ያለፉትን አገዛዞች ጭቆና ሃያ አምስት ዓመት እያወሩ ‹‹ እኔ ከሌለሁ ያለፉ አገዛዞች ከመቃብር ተነስተው ይመጡብሃል ፣ አገርህ ትበታተናለች›› የሚለው ማስፈራሪያ  አልሰራም ፡፡ በህዝብ ሥም እየማሉ የሚሰራ ፕሮፖጋንዳና የህዝብ መብት ማክበር ለየቅል ናቸው፡፡ ስለዚህ መፍትሄው የህዝቡን ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ  መብት ካሳለፍነው ነባራዊ ሁኔታና ካለንበት ተጨባጭ እውነታ የህዝቡን ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ካሳለፍነው ነባራዊ ሁኔታና ካለንበት ተጨባጭ እውነታ በሚጣጣም መልኩ( የዕድገት፣ እውቀት … ) ደረጃችን ባገናዘበና በሚጣጣም መልኩ  በተግባር ማረጋገጥ ብቻ ነው ፡፡
  3. የህግ የበላይነትና ፍትሃዊ ሥርዓት፡- የገዢው ፓርቲ አባል ከህግ የበላይ በሆኑበት  /በህግ  በማይጠየቁበት አገር መኖራችን  አደባባይ የሞቀው ምስጢር በሆነበት ፣ የፍትህ ተቋማት ገለልተኝነት አጠያያቂነት ሳይሆን በገዢው ፓርቲ አገልጋይነት በህዝብና በሙያው በተሰማሩ  በተረጋገጠበት፣ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸውና ዘራቸው  በፈጠራ ተወንጅለው ክስ ሳይመሰረትባቸው ለዓመታት በሚታሰሩበት፣ በተጠረጠሩበት ወንጀል ፍትህ ሳያገኙ ለዓመታት በወህኒ በሚማቅቁበት፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተነገሩ በህዝብና አገር ሃብት ላይ የተፈጸሙ ዘረፋዎች በማያስጠይቁበት፣  ዳኞች የፍርድ ውሳኔ በስልክ በሚቀበሉበት . . . የመኖራችንን እውነት የዕለት ተዕለት ህይወታችን እየነገረን ባለበት ህወኃት/ኢህአዴግ ራሱን የህግ የበላይነት ተምሳሌት ፣የፍትሃዊነት አራማጅ አድርጎ በማቅረብ ህዝቡ  ‹አይሰማም›  ብሎ ከጀመረው ትግል ‹ ጥልቅ ተሃድሶ › በሚል ግርግር ወደኋላ መመለስ አይቻልም፡፡
ህወኃት/ኢህአዴግ የራሱን ህገመንግስት ራሱ እየረገጠና እየጨፈለቀ ‹‹ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ፣ የሚቀናብን ህገ መንግስት ባለቤቶች ነን›› ብሎ ቢናገርና በምሁር ተብዬዎች ቢያስነግር ፤ ህዝብን ከላይ በተገለጹት ሁኔታዎች የማሰቃየው ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር ነው ብሎ በጠመንጃና ወታደር  የዜጎችን ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ማፈን ለጥቂት ጊዜ እፎይታ ቢሰጥ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ካሳለፍነው ህይወት ህያው ምስክር ነን፡፡
  1. የህዝብ የሥልጣን ምንጭነትና ባለቤትነት፡- ይህ በህገመንግስቱ መቀመጡ አያጠያይቅም ፡፡ ቀስቃሽና ወስዋሽ አያስፈልገውም ፡፡ እያጠያየቀ ያለው ታዛኝ ‹ ስልኩት ወዴት ሲጠሩት አቤት › እንዲል የተዋቀረው በህዝብ ድምጽ  ዘረፋ ከገዢው ፓርቲ ጎን በመቆሙ የህዝቡን አመኔታና የሥልጣኑን ክብር ያጣው ምርጫ ቦርድ ይህን ህገመንግስታዊ የህዝብ መብት ሊያስከብር አልቻለም፣ አይችልም ነው፡፡ የራሱን በህገመንግስት የተቀመጠለትን  መብትና በህግ የተሰጠውን ሥልጣን ማስከበር፣ መጠቀምና መተግበር ያልቻለ ምርጫ ቦርድ የህዝብን የሥልጣን ምንጭነት ሊያረጋግጥ ፣ባለቤትነቱን ሊያስከብር አይችልም ነው፡፡ህዝብ የሥልጣን ምንጭነቱንና ባለቤትነቱን  በዚህ ምርጫ ቦርድ አመራር በሚደረግ ምርጫ አስመልሳለሁ፣ ለውጥ ይመጣል፣ ድምጼ ይከበራል የሚል ተስፋው የተሟጠጠው ዛሬ ሳይሆን  ከምርጫ 97 ወዲህ ነው፡፡ ዛሬማ ከመሟጠጥ አልፎ ተንጣፎ በማለቁ ምርጫ 2007 ማግስት ጀምሮ የሚያሰማውን ‹በቃን› መፈክርና የሚያደርገውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል እያየን ነው፡፡
  2. የብሄር ብሄረሰቦች መብት መረጋገጥና ፍትሃዊ ልማት፡- ይህ በህወኃት/ኢህአዴግ ህዳር 29 በሚከበረው በዓል ላይ ብሄር/ብሀሄረሰቦች በሚያሳዩት ጭፈራ፣ የህዝብን ተጠቃሚነት ባላረጋገጠ የሁለት ዲጅት ተከታታይ እድገት ህዝቡ በኢቢሲ እየቀረበ በሚሰጠው ምስክርነት (ፕሮፖጋንዳ ) መረጋገጡ በየዕለቱ ኢቢሲን ስንከፍት ምንመለከተው ነው፡፡በግልጽ  የማይነገረን  በክልሎች መካከል የተፈጠሩ ግጭቶች በወቅቱና በህግና ታሪክ አግባብ መፍትሄ ሳይበጅለት የሚደርሰው  የህይወት፣ አካልና ቁሳዊ ጥፋትና ማኅበራዊ ቀውስ  ነው (በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች፣በትግራይና  አማራ፣ …) እንዲሁም ብሄር/ብሄረሰቦች የሚያነሱት የማንነትና ህገመንግስታዊ የመብት  ጥያቄን በማፈን የሚወሰደው የአፈና እርምጃ ( ኮንሶ፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ ሃመር ) የሚያሳዩት የተገላቢጦሹን ነው፡፡ እነዚሁ ችግሮች ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ካጠሉት የቀጣይ ግንኙነት ጥቁር ግርዶሽ አልፈው  በኢህአዴግ  አባል ድርጅቶች መካከልም ያለውን ግንኙነት እያወኩ ስለመሆኑ የ‹‹ጠባብነትና ትምክህተኝነት ፍረጃዎች አመላካች ናቸው፡፡ ይህ በሆነበት በፕሮፖጋንዳ የህዝቦችን መብት የሚያከብር፣ የሚያነሱትን ጥያቄ የሚመልስ፣ ያላቸውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጠናክር ፣… ዘላቂ መፍትሄ አይመጣም ፡፡
ሌሎች በፕሮፖጋንዳውና የህዝብ  ተጨባጭ ህይወት መካከል ያሉትን  ተቃርኖዎች በስፋትና ጥልቀት ማሳየት ይቻላል፡፡ ግን ‹ ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም › እንዲሉ ነውና እናጠቃለው፡፡
ህወኃት/ኢህአዴግ ዲሽ ለማውረድ በሰው ጣሪያ መንጠልጠል፣ ኢሳትን ኦኤምን አትስሙ የሚል አዋጅ፣ ሰማያዊ፣ ቄይ ፣ ጥቁር አትልበሱ መመሪያ፣ ህዝብ ( ሴቶች፣ ወጣቶች ፣ ህጻናት)  ለመሰብሰብ የ50 ብር ጉቦ ማቅረብ፣….፣ ስለኑሮኣችን ‹የሚያስረዱን› ሆድአደር ምሁራንና ልማታዊ ጋዜጠኞች ፣ ድምጽ አስዘራፊ ምርጫ ቦርድ፣  በአምሳልህ የፈጠርካቸው ‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች›  … ሳያስፈልጉህ  ኑሮኣችንና  እኛው ከህይወታችን ፣ በመሰከረልህና ደጋግመን በመረጥንህ  ነበር፡፡ እስከዛሬ የሄድክበትና አሁንም የሙጥኝ ብለህ የያዝከው መንገድ  ሩጫህን ጨርሰሃል ከምንልበት አሳልፎህ  ‹ ሩጫዬን ጨርሻለሁ › ብለህ ለመጻፍ ቁልቁለቱን  በፍጥነት እየነዳህ መሆኑን አስተውል፡፡
ከነዚህ የምናየው በፕሮፖጋንዳ ህዝብን ለተወሰነ ጊዜ ማታለል፣ በማስፈራራት መግዛት ይቻላል፡፡ ግን ሁሌም አይቻልም፣ አሁን ላይ ህዝብ በፕሮፖጋንዳ ጠግቦ ማግሳት፣ በጠመንጃ ፈርቶ መገዛት ፣ የዘር የበላይነትን ተቀብሎ መሸማቀቅ፣…  ‹‹በቃኝ›› ብሎ አደባባይ መውጣቱ ያረጋገጠውም ይህንኑ ነው፡፡ እያልኩ ያለሁት ህወኃት/ኢህአዴግ ቢሄድ ፣ቢቀበር የፖለቲካ ባህላችን ካልተቄየረ፣ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ካልፈጠርን ፣ ትግላችን ፓርቲን ከማጥፋት/መቅበር  ወደ አመለካከቱን መታገል፣ አድራጎቱን መቃወም ካልተሸጋገረ፣ በፖለቲካ አመለካከታችንና ትግላችን ከዘረኛነት ወደ ኅብረትና የጋራ ጉዳዮቻችን  ካላደግን …  መንግስት ልንቀይር እንችላለን እንጂ የሥርዓት ለውጥ ስለማምጣታችን ማረጋጫ የለንም፡፡ ከዚህ በመነሳት እያልን ያለነው ከላይ ያነሳናቸው እውነታዎች ሥር ሰደው ባሉበት  ነገ ማንም ቢመጣ  በበነጋውና  ያለህዝብ ተሳትፎ በራሱ/በመንግስት ብቻ ያስወግዳል ማለት አይደለም ፡፡ የዜጎች መብት ባልተከበረበት፣ የህግ በላነት ባልሰፈነበት፣ ዜጎች የአገሪቱን ችግሮች ተረድተውና ነባራዊና ተጨባጩን ሁኔታ ተቀብለው   ለመፍትሄው በጋራ ለመስራት ባልቆረጡበት ፣ …… በአገራቸው ሉዓላዊነትና በራሳቸው ክብር ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ባልተመለሰበት … ምርትና ምርታማነትን አፍነው /ሰንገው የያዙ ፖሊሲዎች ባልተስተካከሉበት …፣ በፕሮፖጋንዳ፣ በኃይል አፈና፣ …. ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ ያለመቻሉን  ነው፡፡
በመሆኑም – አዎን ስለቀጣዩ ጊዜና ዘላቂው መፍትሄ እናተኩር ማለቴ  ህወኃት/ኢህአዴግ  በያዘው መንገድ ለመቀጠል የሚያደርገው ሁሉ ‹‹ ላታመልጪኝ  – ምናለ ባታደክሚኝ› እንደተባለው ስለመሆኑ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ፈላስፎችም  ‹እርግጠኝነትን› የፍልስፍና  እንጂ ‹የፖለቲካ › ጠላት ነው አላሉም ፡፡ ስለቀጣዩ ጊዜና ዘላቂው መፍትሄ  እንጨነቅ ስል በተለመደው በኃይል ላይ የተመሰረተ የቀደመውን የሚቀብር፣ ያለፉትን ተደማማሪ የዕድገት እርምጃዎች ደምስሶ/ክዶ ከዜሮ የሚጀምር፣የወር ባለተራ ገዢ መንግስት  የመተካት  አዙሪት ልንወጣ  አንችልምና  በሥርኣት  ለውጥ የዜጎችን ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብትና ክብር የሚያረጋግጥ ፣ ዘላቂና ቀጣይ ሠላምና ልማት የሚያጎናጽፍ የሁላችን፣  በሁላችን ፣ለሁላችን መፍትሄ ለማምጣት በኅብረት እንነሳ  ማለቴ ነው፡፡
ይህ ማለት ሲጠቃለል ‹‹ ህወኃት/ኢህአዴግ በየቱም መንገድ መሄዱ አይቀሬ መሆኑ ሃቅ ነው፡፡ እኔ እያልኩኝ ያለሁት እና የሚያሳስበኝ  ኢህአዴግ ሲሄድ የሚከተለው/የሚተካውን እንዴት እናምጣው ብለን እንመካከርበት ነው፡፡ ከተቻለ ኢህአዴግንም የዘላቂው መፍትሄ አካል አድርገን/አሳትፈን  ከተለመደው  የመቀባበር አዙሪት  ወጥተን ፣ ካልተቻለም ማለትም ህወኃት/ኢህአዴግ  የቀረበለትን አማራጭ ካልተቀበለና በለመድኩት የአፈና መንገድ እቀጥላለሁ ካለ የኢትዮጵያ ህዝብና የለውጥ ኃይሎች ከአዙሪቱ ውጪ ዘላቂ መፍትሄ እንዴት እናምጣ በሚለው ላይ ስለአገራችንና ህዝባችን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ  በኢህአዴግ ላይ እንምከርበትና በሠላም እናስወግደው በሚለው ላይ በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ዓላማ ይዘን  በጋራ በትብብር/ኅብረት እንስራ ›› ማለት ነው፡፡
ስለዚህ ህወኃት/ኢህአዴግ በፕሮፖጋንዳ የመቀጠል ጀንበር አዘቅዝቃበታለች፣ ከመጥለቋ በፊት ሊፈጥን ይገባል ፡፡ እንደመግቢያው ባለፈው የዘላቂ መፍትሄ መደምደሚያ ላብቃ፡፡
‹‹….ስለዚህ ህወኃት/ኢህአዴግ ሆይ- በጥልቅ ተሃድሶና ‹ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር አደረግሁ› በሚል  በሚሰራ ፕሮፖጋንዳም ሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚፈጸም አፈና ዕድሜ የማራዘም ጀንበር እያዘቀዘቀች  ከመጥለቂያው ተቃርባለችና ‹ ጀንበር ሳለች እሩጥ› ምክራችን ሲሆን ከዚህም ከማንም በላይ ተጠቃሚው አንተ ነህና እወቅበት ማለታችን ለሁላችንም ጠቃሚ ስለሆነና በመሳሪያ ኃይል አምላኪ የመንግስት ለውጥ  ታሪካችንን ስለሚቀይር ነው፡፡››
ለአገራችንና ህዝባችን ደግ ደጉን ያሳስበን፣ መልካሙን ያስተግብረን ዘንድ ቀና ልቡና ብሩህ አዕምሮ፣ ብልህ አመራር … ያድለን ዘንድ ትግላችንን በጸሎት እያገዝን ወደማይቀረው ዘላቂና ቀጣይ መፍትሄ –  የሥርዓት ለውጥ – ጉዞኣችንን በህብረት እናፋጥነው፡፡
10/ 06/09 ግርማ በቀለ ወ/ዮኃንስ ፡፡

No comments:

Post a Comment