Monday, February 13, 2017

በድርድር የሚሳተፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በ3 ቡድን ተከፍለዋል

   


ድርድሩ በማን መሪነት እንደሚካሄድ ረቡዕ ይወሰናል”
– የተቃዋሚ ተደራዳሪዎች፣ ደህንነታቸው በመንግሥት እንዲጠበቅ ጠይቀዋል
– ኢህአዴግ – “ለድርድር እና ለክርክር ተዘጋጅቻለሁ”
በድርድር ጉዳይ ላይ ከኢህአዴግ ጋር ለመነጋገር ለረቡዕ የካቲት 8 የተቀጣጠሩት ከደርዘን በላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በሶስት ጎራ ተሰባስበውና ተከፋፍለው ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ወስነዋል፡፡ ድርድሩ በማን መሪነትና ታዛቢነት እንደሚካሄድ ገና አልተወሰነም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋግረው ውሳኔ ለማስተላለፍም ነው ለረቡዕ የተቀጣጠሩት፡፡
ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የድርድር መነሻ ሀሳቦችን በጋራ እና በተናጠል ለፓርላማ ጽ/ቤት እንዳስገቡ ገልፀዋል፡፡
የእነ ኢዴፓ ቡድን …
ኢዴፓ፣ ሠማያዊ፣ መኢአድ፣ ኢራፓ፣ መኢዴፓ እና ኢብአፓ፣ በጋራ ለመደራደር መሰባሰባቸውን ገልፀው፣ ከኢህአዴግ ጋር የሚደረገው ድርድር እንዴት መካሄድ እንዳለበት የራሳችንን ሀሳብ አቅርበናል ብለዋል፡፡ የፈጠሩት ቡድን ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ በአደራዳሪነትና በታዛቢነት እነማን እንደሚሳተፉ በመዘርዘር የጋራ አቋም መያዛቸውን ስድስቱ ፓርቲዎች ጠቅሰው፣ ሚዲያዎች ድርድሩን እንዴት እንደሚዘግቡትም አስታውቀዋል፡፡
6ቱ ፓርቲዎች የህዝብ ጥያቄዎች በሙሉ እስኪመለሱ እንደሚደራደሩና አስፈላጊ ከሆነ ህገ መንግስቱን የማሻሻል ድርድር ከገዥው ፓርቲ ጋር ለማድረግ እንደተዘጋጁ ጠቁመዋል፡፡
በድርድሩ ወቅት የህዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ፓርቲዎቹ ገልፀው፣ ድርድር የሚያካሂዱት የፓርቲ ጉዳይ ለማስፈፀም ሳይሆን ህዝቡ በተቃውሞ ሲያነሳቸው የነበሩትን ጉዳዮች በማንገብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ ተቀስቅሶ የነበረው ተቃውሞና አመፅ፣ “በስርአቱ አምባገነንነት ሳቢያ የተፈጠረ ነው” የሚል አቋም መያዛቸውንም ፓርቲዎቹ ገልጸዋል። ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ ሲያቀርቧቸው የነበሩ የማሻሻያና የማስተካከያ ሃሳቦች፣ በመንግስት በኩል ተቀባይነት ተነፍጓቸው ቆይቷል፤ ይህም ሃገሪቱን ዋጋ አስከፍሏታል ብለዋል – ፓርቲዎቹ፡፡
የተጀመረው ድርድር በገዥው ፓርቲ በኩል በቅንነትና ቁርጠኝነት የሚከናወን ከሆነ፣ ውጤት ያመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ፓርቲዎቹ ጠቅሰዋል፣ የድርድሩ ውጤት አንዱን ከስልጣን አውርዶ ሌላውን ወደ ስልጣን ማምጣት አይደለም፤ የኛ ፍላጎት መንግስት በምርጫ የሚቀየርበትን ዘላቂና ቋሚ ስርአት እውን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ገና ድርድሩ ሳይጀምር ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን በጠቆምም፣ በድርድሩ ላይ የሚሳተፉ አመራሮቻችን ከስጋት ነፃ እንደሆኑ የደህንነት ዋስትና ያስፈልጋቸዋል፤ ይህም በመንግስት እንዲጠበቅላቸውም ጠይቀዋል ፓርቲዎች፡፡
ድርድሩ ከወዲሁ የህዝብ ተአማኒነት እንዲያተርፍ፤ መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ይጠበቅበታል ሲሉም ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
የእነ አንድነት ቡድን
በአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር በአቶ ትዕግስቱ አወሉ አስተባባሪነት የሚንቀሳቀሱ ሌሎች 6 ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ የጋራ ቡድን በመፍጠር ለድርድር እንደተዘጋጁ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ የህዝብ ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ እንዲያገኙና ህዝባዊ ስርአት እንዲመጣ እንደራደራለን በማለት ፓርቲዎቹ ገልፀው፤ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ የህዝብ ጥቅምን አስቀድመው እንዲደራደሩ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ቡድኑን የመሰረቱት ፓርቲዎች፣ ቅንጅት፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት፣ የኢትዮጵያ ሠላማዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ ናቸው፡፡ መድረክን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ በተናጥል ለድርድር ለመቅረብ ወስነዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የምርጫ ስነምግባር ደንብ ፈርመው የጋራ ም/ቤት አባል የነበሩ ፓርቲዎች “በምክር ቤቱ የነበረንን ቆይታ ስንገመግመው ምንም ውጤት አላስገኘልንም” ብለዋል፡፡
‹‹ምክር ቤቱ የተቋቋመበትን አላማና ግብ አላሳካም›› ያሉት የአንድነት ሊቀመንበር አቶ ትዕግስቱ፣ በምክር ቤቱ የነበሩ ተቃዋሚዎች የአቅም ውስንነት ነበራቸው ብለዋል፡፡
የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፣ የምክር ቤቱ ቆይታችን ውጤት አልባ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የራሱን የመደራደሪያ ሀሳቦችን እንዳዘጋጀ የገለፀው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ፣ ሁሉም ፓርቲዎች ባቀረቧቸው የመነሻ ሃሳቦች ላይ ለመወያየት የካቲት 8 ቀን በፓርላማው አዳራሽ እንገናኝ በማለት ቀጥሯቸዋል፡፡
የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ ድርጅታቸው የውይይት ሀሳቦችን ፕሮፖዛል ለፓርላማ ማስገባቱን የገለፁ ሲሆን፣ ድርድር በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በግልፅ ለመደራደር፣ ክርክር በሚያስፈልጋቸው የፖሊሲ ጉዳዮች ላይም ለመከራከር ወስነናል ብለዋል፡፡
ረቡዕ በሚደረገው ውይይት፣ “ድርድሩን ማን ይምራው? በምን መልኩ ይካሄድ?” በሚለው ጥያቄ ላይ ፓርቲዎቹ በውይይት ይወስናሉ ብለው እንደሚጠብቁ አቶ ሽፈራው ጠቁመዋል፡፡ በድርድሩ ስምምነት ላይ የሚደረስባቸው የህግ ለውጦችና ማሻሻያዎች፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል፤ – አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፡፡

No comments:

Post a Comment