Friday, February 10, 2017

የብዙኃን መገናኛዎቻችን የመዝናኛ ዝግጅቶች ጠንቀኝነት! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው



ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ይሄንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሣኝ ጉዳይ እንዲያው ደበር ሲለኝ ቅድም (ሐሙስ ከሰዓት በኋላ 08:20, 2009ዓ.ም.) የሸገር ሬዲዮን (ነጋሪተ ወግ) ስከፍት ምን እሰማላቹሀለሁ! ሰዓቱ የጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሞያ አንዷለም ተስፋዬ የዝግጅት ሰዓት ኖሮ “አንድ ፈላስፋ ነው!” አለና በመቀጠል “”ስሕተት፣ ወንጀል፣ ኃጢአት የሚባሉ ነገሮችን ዘርዝሮ በመጻፍ “ፈጽሜያቸዋለሁ!” በሚላቸው ላይ ምልክት ምልክት አደረገና “መንግሥት ይሄንን ማድረጌን ቢያውቅ ምን ያህል እስራት ይቀጣኝ ነበር?” ብሎ ሲያሰላው አራት ዓመታት ያህል እስራት እንደሚያስቀጣው አየ፡፡ በተመሳሳይ የሃይማኖት መጽሐፍ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ገለጠና ሲመለከት የሠራው ኃጢአት ለዘለዓለሙ ገሃነመ እሳት ውስጥ ሲቃጠል እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ያነባል፡፡ ከዛ ሰውየው “እንዴት?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ መንግሥት እንኳን ከአራት ዓመታት በላይ ሊቀጣኝ በማይችለው፣ እንደዛሬው ብዙ ሳልበስል ያውም አንዳንዱን ኃጢአት መሆኑን እንኳ ሳላውቅ ባደረኩት ነገር እንዴት እግዚአብሔር መጨረሻ በሌለው ቅጣት ለዘለዓለሙ ሊቀጣኝ ይችላል? እንዴት ዓይነት ጭካኔና ኢፍትሐዊነት ነው? በማለት ጠየቀ!”” አለና ጋዜጠኛው “ሁላችንም ይሄንን ጥያቄ መጠየቅ ስላለብን ነው ወደናንተ ያመጣሁት! እስኪ እናንተ ምን ይሰማቹሀል? ተወያዩበት! የዘለዓለም ቅጣት! ነገሩ አያበሳጭም? ምን ዓይነት ፍርድ ነው? የሰው ልጅ የማይቻል ፍጡር ነውና ገሃነም ውስጥ ቆልፌበት ልረፍ! ነው እንዴ ነገሩ?” አለና ዘፈን አስከተለ፡፡
እንዲህና ሌላም ዓይነት ስሕተቶች በተለይም ደግሞ ለብዙኃን መገናኛ ባለው ከፍተኛ ግምትና ክብር በብዙኃን መገናኛ የሚነገር ነገር ሁሉ እውነት በሚመስለው እንደኛ ላለ ማኅበረሰብ ሊያስከትል የሚችለው አሉታዊ ውጤት ሊገመት ከሚችለው በላይ ነው፡፡
ይሄ ጋዜጠኛ የተናገረው ነገር ሁሉ ሐሰትና ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጋር ሙሉ ለሙሉ የሚቃረን በመሆኑ “እንዴት ሚሊዮኖች (አእላፋት) በሚያዳምጡት ሬዲዮ (ነጋሪተ ወግ) ላይ ምንም የማታውቀውንና ትክክለኛ ያልሆነን የተሳሳተ መረጃ ሚዛናዊነትን ሳትጠብቅ አፍህ እንዳመጣልህ ትረጫለህ? ያዳመጠህን ሁሉ እያሳሳትክ እንደሆነ ይገባሀል ወይ?” ብየ የተሳሳተውንና ትክክለኛው ምን እንደሆነ፣ በማይጠበቅ ደረጃ አለመብሰሉንም ልነግረው የጣቢያውን የስቱዲዮ (የመከወኛ ክፍል) ስልክ (መናግር) ብቀጠቅጥ ብቀጠቅጥ ይጠራል የሚያነሣው ግን የለም፡፡ ከዚያ “ትክክለኛውን ነገር ለምን የተሳሳተ፣ ያልበሰለና ሰይጣናዊ መልዕክት ለተረጨበት ሕዝብ በማኅበራዊው የብዙኃን መገናኛ አላደርሰውም?” ብየ አሰብኩና ወደእናንተ አመጣሁት፡፡
የብዙኃን መገናኛው እንዴት መጫወቻ መቀለጃ ሆኗል መሰላቹህ! በተለይማ የባጡ የቆጡ የሚቀባጠርባቸው የመዝናኛ ዝግጅቶች! (አብዛኞቹ ማለቴ ነው) እነሱን “ምን ተሳሳቱ?” ብሎ ከመጠየቅ “ያልተሳሳቱት ምንድን ነው?” ብሎ መጠየቁ ይቀላል፡፡
የተቀመጡበት ወንበር ብስለት፣ እጅግ ኃላፊነትና ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑን ጨርሶ የማይረዱ (ሳይነገራቸው ቀርቶ አይመስለኝም የሚገባቸው ስላልሆኑ እንጅ) ፣ እዚያ ላይ ቁጭ ብለው የሚናገሩት እያንዳንዷ ነገር በባሕላችን በወጋችን በማንነታችን አዎንታዊ በሆኑ የወል አስተሳሰባችን ላይ ሁሉ አሉታዊ ውጤት የማያስከትል ስለመሆኑ መርምረው አረጋግጠው የመናገር ብቃት የሌላቸው፣ ምንም ስለ ማያውቁት ነገር ተጠያቂነት በሌለበት ስሜት እንዳሻቸው የሚቀባጥሩ፣ የሚያቀርቡት ነገር በባሕል በወግ በማንነት በታሪክ ወዘተረፈ. ላይ የቱንም ያህል አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያስከትል ቢሆንም እንኳ ገንዘብ እስካስገኘላቸው ጊዜ ድረስ ምንም ከማድረግ የማይመለሱ ወይም ከገንዘብ በስተቀር ምንም የማይታያቸው (Business oriented) ፣ በዜግነታቸው ሀገሪቱ ከእነሱ የምትጠብቅባቸው ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለ ከነመኖሩ እንኳን ጨርሶ የማይረዱ ወይም መወጣት በፍጹም የማይፈልጉ ወዘተረፈ. ናቸው፡፡
ይሄ እንግዲህ እንደ ወያኔ ዓይነት አገዛዝ ባለበት ሀገር የሚጠበቅ አደጋ ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ የጠቀስናቸው እሴቶች የሚሰሟቸውን የሚጠብቁትንና ብቃት ያላቸውን ዜጎች ሥርዓቱ (The system) ወደጎን ስለሚገፋቸው፣ ስለማይፈልጋቸውና ቦታ ስለማይሰጣቸው ለእነኝህ እሴቶቻችን ዴንታ የሌላቸው፣ ሁለነገራቸውን ገንዘብ የሚገዛቸው ኅሊና ቢስ የመንደር አፈጮሌዎች መፈንጫ ለመሆን እንገደዳለን ማለት ነው፡፡
በዚህ ምክንያት ታዲያ በሀገርና ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ጉዳትና ኪሳራ እንዲህ የዋዛ እንዳይመስላቹህ፡፡ ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት ወዲህ በኅብረተሰባችን ላይ በሰፊው ለተስፋፋው ኢግብረገባዊነት፣ የሞራል (የቅስም) ዝቅጠትና ሌሎች አሉታዊ ለውጦች፣ የማንነት ቀውስና ኪሳራዎች ሁሉ ምክንያቱ ሌላ ምንም ሳይሆን ይህ ችግር ነው፡፡
ነገር ለማሳጠር ያህል ጋዜጠኛ አንዷለም በሰይጣን እየተጋለበ የረጨውን የተሳሳተ፣ አሰናካይ፣ አሳሳች መልዕክት አርሜ ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ እግዚአብሔር የሰይጣን ደቀመዝሙሩ ጋዜጠኛ አንዱዓለም እንዳለው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለተሠራ ትንንሽ ኃጢአት “ይሄን ስላደረጋቹህ!” ብሎ ዘለዓለማዊ ቅጣት ወይም ገሃነም ውስጥ የሚጥል ጨካኝና አረመኔ አምላክ ሳይሆን የፈጸማቹህት ኃጢአት የቱንም ያህል ከባባድና እጅግ በርካታ እንኳን ቢሆን የሚምርና ዘለዓለማዊ መንግሥቱን የሚያወርስ፤ ለደግነቱ፣ ለቅንነቱ ወደር የሌለው ቸር አምላክ ነው፡፡ ከኛ የሚጠበቀው ንስሐ መግባት ብቻ ነው፡፡
እግዚአብሔር ማንንም “ለምን ኃጢአት ሠራህ?” ብሎ አይጠይቅም! የሰው ልጅን ደካማነትና የባለጋራችንን ብርታት ያውቃልና፣ ኃጢአት የሌለበት ሰው የለምና፡፡ እግዚአብሔር የሚጠይቀው ጥያቄ “ለምን ንስሐ አልገባህም?” ብሎ ነው፡፡ የሠራነው ኃጢአት የቱንም ያህል ከባድና ዘግናኝ ይሁን፤ ምንም ያህል ጊዜ ይደጋገም ይብዛ ንስሐ በመግባት ከተጠያቂነት ከተወቃሽ ተከሳሽነት ነጻና ጻድቅ መሆን እንችላለን፡፡ ከዚህ በላይ ቸርነት ደግነት ቅንነት ምን አለ? ከዚህም በላይ እግዚአብሔር እኮ ለእኛ ካለው ፍቅር ብዛት የተነሣ እንደጠፋን እንደረከስን እንዳንቀር አንድያ ልጁን አምላክ እግዚአብሔር ወልድን ተለዋረደ ሞት አሳልፎ የሰጠ ወደር የሌለው ቅን፣ ደግና ቸር አምላክ ነው፡፡ እጅግ ኃጢአተኞች በደለኞች እርኩሶች የነበርነው ንስሐ በመግባት ብቻ ንጹሕና ጻድቅ መሆን ከቻልን ይሄ የሚያሳየው የእግዚአብሔርን ጨካኝነት ነው? ከኃጢአተኝነት ንስሐ በመግባት ጻድቅ መሆን እየቻልን የሠራነው ኃጢአት እንደሚያስፈርድብን ተነግሮን እያወቅን ንስሐ ባለመግባትና በኃጢአት ላይ ኃጢአት በመደራረብ ሰውን ሳናፍር፣ እግዚአብሔርን ሳንፈራ ምድሪቱን ስናጎሳቁል ቆይተን ስንሞት ቢፈረድብን ተጠያቂው ማን ነው?
ለመሆኑ እግዚአብሔር ኃጢአት የተባሉ ነገሮችን “የሚያስኮንኑ ኃጢአቶች ናቸው!” ብሎ ለምን የደነገገ ይመስላቹሀል? በእኛ ላይ ቀንበር ለመጫን ነው የሚመስላቹህ? አትሳሳቱ አይደለም! የሰው ልጆችን ኑሮ ሰላማዊ፣ አስደሳችና ጤናማ ለማድረግ ነው፡፡ የሱ ፈቃድና ፍላጎት ይሄ ቢሆንም እኛ ግን ለእኛው ጥቅም አታድርጉ ተብለን ተከልክለንም እንኳ ቃሉን ባለመስማት ወደሰው ሚስት/ባል በመሔድ ወይም በመዘሞት፣ የሰው ገንዘብን በመስረቅ፣ በመስከር፣ በመጣላት፣ በሐሰት በመመስከር፣ በመመቅኘት፣ በማሟረት፣ ጣዖት በማምለክ፣ ለአባይ ጠንቋይ ለቃልቻ በመስገድ በመገዛት፣ ነፍስ በማጥፋት፣ ሱሰኛ በመሆን የመሳሰሉትን በመፈጸም ኑሯችንን ሰላም የጠፋበት፣ የሁከትና ጎስቋላ እናደርገዋለን፡፡ ታዲያ ማን ነው ተጠቃሚው? ማንስ ነው ተጠያቂው?
እስኪ ልቡናውን ይስጠን! ለንስሐ ሞትም ያብቃን! ከንስሐ ግን ማመን ይቀድማል!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

No comments:

Post a Comment