Thursday, February 9, 2017

ታሪክን ምርኮኛ የማድረግ ዘመቻ – ዶ/ር ነብዩ ጋቢሳ



ዶ/ር ሃይሌ ላሬቦ
ከሰሞኑ የፖለቲካችን የስበት ማእከል ታሪክ እና የታሪክ ባለሙያዎች ሆነዋል።ዶ/ር ሃይሌ ላሬቦ የተባሉ የታሪክ ምሁር ከኢሳት ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ በሶሻል ሚዲያው ከፍተኛ አዋራ ማስነሳቱ ሳያንስ፣ የተዳፈኑ የመሰሉ ጉዳዮችንም በመቀስቀስ ላይ ይገኛል።በመጀመሪያ የዶክተሩን ቃለምልልስ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በጽሞና ለመከታተል ሞክሬአለሁ።በዚህም ተጠያቂውን ዶ/ር ሃይለማርያም ላሬቦ ከሙያም  ሆነ ስነምግባር አንጻር የበቃ ችሎታቸውን ለመታዘብ ችያለሁ። ውዝግቡ ከተቀሰቀሰም በሁዋላ የኦሮሞ አክቲቪስት ነን ከሚሉ ሰዎች በተሰነዘረውን ክስ ላይ ተመስርቼ ቃለ-ምልልሱን በሂሳዊ አይን ለማየት ሞክሬአሁ።ህዝብ የተሰደበበት እና ወደ አንድ ሚዛን ያጋደለ አቀራረብ ፈልጌ ማግኘት ተቸግሬአለሁ።እንዳውም ዶ/ር ሃይሌ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አወዛጋቢ ቦታ ስለሚይዘው ግራኝ አህመድ በጎ የሆነ እይታ እንዳላቸው መታዘብ ይቻላል። ግራኝ አህመድን  በሚመለከት ያላቸው እይታ በአዲስ አበባ ዮኒቪርሲቲ የታርክ ትምህርት ክፍል እውቅ የታሪክ ተመራማሪ ከነበሩት ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ ጋር ተመሳሳይ እይታ እንዳላቸው ማወቅ ይቻላል። በዚህ መሰረት አክቲቪስቶች ነን የሚሉት ክስ መነሻ ሌላ መሆን አለበት በሚል አዲስ መላምት ጥረቴን ሌላ ምክንያት ቢኖርስ ወደሚል አቅጣጫ ለወጥሁት።
በዚህ ሂደት ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ የኦሮሞ አክቲቪሰት ነን የሚሉት አክራሪ ብሄረተኞች በዶ/ር ሃይሌ ላይ  ዛቻ እና ማስፈራሪያን ጨምሮ፣ አጓጉል ስሞችን እስከ መስከጠት የደረሰ ዘመቻ ውስጥ እንደነበሩ መረዳት ይቻላል። ከዛም አልፎ በተማሩበት የታሪክ ጥናት መስክ ያላቸውን ችሎታ በማጣጣል ፣የዶክትሬት ደረጃቸውን ሃሰተኝነት በመናኘት፣  ማንኛውም መድረክ እንዳይጋበዙ፣ ተደማጭነት እንዳያገኙ እንዲሁም ከሚያስተምሩበት ስራ እንዲባረሩ ያላደረጉት ጥረት የለም ማለት ይቻላል። የነፍጠኞች ተላላኪ ወኪል፣የኦሮሞ ደመኛ ጠላት ተደርገው በአደባባይ እንዲሳሉም ተደርጎዋል።ይህ አልበቃ ብሎ በተለያዩ መድረኮች ቀርበው ጥናታዊ ጽሁፍ እንዳያቀርቡ ቅስቀሳ ሲደረግ እንደነበረ በቅርብ ግዜ የምናስታውሰው ነው። ለዚህ አንድ ምሳሌ ብንጠቅስ ባለፈው ዓመት ቪዥን ኢትዮጵያ ከኢሳት ጋር ባዘጋጁት ኮንፍረንስ ዶክተሩ እንዳይጋበዙ በአዘጋጆቹ ላይ ጫና ሲደረግ ነበር።ሌላው ዶ/ር ሃይሌን የተመለከቱ ተለያዩ መዛግብትን በድረ-ገጽ በመበተን የማስተማር ችግር እንዳለባቸው እንዳውም ዱክትርነታቸው የሃሰት እንደሆነ ሲነዛ ነበር።ጉዳዩን በቅርብ የምንከታተል ዶ/ር ሃይሌ በኦክስፎርድ ዮኒቨርሲቲ ያሳተሙትን ጥናታዊ የሆነ መፅሃፍ ይፋ ሲደረግ የሚቀርብባቸው ክሶች መሰረተቢስ፣ በጥላቻ የተነሳሱ እንደሆኑ ለመታዘብ ችለናል።ይህ አልበቃ ብሎ፣ ዶክተሩ በሚያስተምሩበት ዪኒቨርሲቲ ላይ ጫና በማሳደር ከስራ እንዲባረሩ ለማድረግ ዘመቻ ተደርጎ እንደነበረ እናስታውሳለን። ሰሞኑንም ይህን አይነቱ ዘመቻ በድጋሚ ተጀምሮ ፊርማ የማሰባሰቡ ስራ እየተከናወነ ይገኛል። እዚህ ጋር ሁላችንም መጠየቅ ያለብን ጥያቄ ግን ለምን ዶክተር ሃይሌ ላሬቦ የስም ማጥፋት ዘመቻ ጥቃትና የጥላቻ ኢላማ ተደረጉ የሚለው ጥያቄ ነው።
ዶክተር ሃይሌ ላሬቦ ተመርጠው የዚህ ሁሉ የስም ማጥፋት እና ማሸማቀቅ የውርጅብኝ ዘመቻ የተከፈተባቸው በሶስት ምክንያቶች እንደሆነ ነው።አንደኛው በዘህ ወቅት የፖለቲከኞች ቁማር መጫወቻ በመሆን እየተበላሸ ያለውን የሃገራችን ታሪክ ሳይፈሩ እውነቱን ከሃሰቱ በመለየት የመናገር ድፍረት በማሳየታቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው የዶክተሩ የት መጣነት (የዘውግ ማንነት)ከደቡብ በመሆኑ ነው።ሶስተኛው ምሁሩ ከዚህ ቀደም የጎሳ ፖለቲካ ዝንባሌ ባላቸው የታሪክ ጸሃፊዮች የተደረሰውን የታሪክ ልብ ወለድ እርቃኑን በማስቀረት ያሳዩት ቆራጥነት ነው።
በአሁኑ ወቅት ጎሰኞች የልብ ልብ አግኝተው ታሪካችንን በማጣመም ብቻ ሳይወሰኑ፣ ትክክለኛ የሆነው የሃገራችን ታሪክ እንዳይነገር የተለያዩ ማሸማቀቂያዎችን በመጠቀም የታሪክ ባለሙያዎች የዳር ቆመው ተመልካች የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሮአል። የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም የፖለቲካ አጀንዳ ያነገቡ ግለሰቦች በታሪክ ላይ የለየለት ውንብድና በመፈጸም የተወላገደ ታሪክ ሲጻፍና ሲነገር እያየን ነው። በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ  የታሪክ አዋቂዎች ስድብን፣ ነቀፋን በመፍራት ብሎም በፖለቲካዎ ተአርሞ(political correctness) ተሸብበው እንዳላዩ ሆነው ማለፍን በመረጡበት ወቅት ነው እንግዲህ ዶ/ር ሃይሌ ወዳደባባይ በመውጣት ሙያቸው የሚጠብቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት እየሞከሩ ያሉት።
ሳይንሳዊ የጥናት ዘዴን በሚከተል አካዳሚያዊ  ምርምር ምንም ነገር ቢሆን ከመፈተጠሽ፣ከመመርመር፣ከመተችት እና  ነጻ አይደለም (immune ) ፡፡ በታሪክ ጥናት ዘርፍ ውስጥም ባለሙያው የምርምር ህግን ተከትሎ፣በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ማንኛውንም ነገር ማጠየቅና እውነተኝነቱን ማረጋገጥ መሰረታዊ ግዴታው ነው።ከዚህ ውጭ የታሪክ ባለሙያው በማህበራዊ መገናኛ ላይ በሚፈጠሩ የጫጫታ ማእበሎች በመርበትበት እና ሙያዊ ግዴታውን ከመወጣት ወደሁዋላ ማለት የለበትም።በዚህ በኩል በዲ/ርሃይሌ ላሬቦ ቃለመጠይቅ ላይ የተነሳውን የሰሞኑ እሰጥ-አገባ ስንመለከት፣የታሪክን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ጩህት በማንበርከክ ሃቁን ለማዳፈን የሚደረግ መውተርተር እንደሆነ መረዳት እንችላለን።በዶ/ር ሃይሌ በኩል የተያዘውም አቁዋም ይበል የሚያሰኝና አሁንም ሳይንሳዊ የሆነውን የታሪክ ጥናት ዘርፍ ፈለግ እስከተተለ ድረስ መቀጠል ያለበት ጥረት እንደሆነ ነው። በነገራችን ላይ በአካዳሚክ  እና  ሃሳብን በነጻነት ጸር የሆኑት፤ የዘመናችን አክራሪዎቹ ተግባት ያስገነዘበን ሌላ ነገር ቢኖር ከዚህ የበለጠ እርምጃ የመውሰድ አቅም ቢሆኖራቸው አሁን በስልጣን ላይ ካለው የህወሓት ቡድን የበለጠ ነገር ሊከሰት እንደሚችል አመላካች ነው።
ሁለተኛውና አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኞችን ከማስቆጣት አልፎ ወደ መረረ የስም ማጥፋት ዘመቻ የከተታችው ምክንያት የዶክተሩ የመጡበት አካባቢ ከደቡብ ኢትዮጵያ መሆኑ ነው።በእነዚህ አክራሪ ብሄረተኞች አመዳደብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰሜንና ደቡብ በሚባሉ ሁለት ዘውጎች (dichotomies ) የተከፈለ ሲሆን፣ሰሜነኛው  የአቢሲኒያ ዘውግ የለየለት ጠላት፣ጨቁዋኝ እና የቀድሞ ስርዓት ናፋቂ በሚል መለያ ሲጠሩት ኖረዋል። ከዚህ ውጪ ያለው የኦሮሞና ደቡብ ዘውግ ከሰሜነኞቹ አንጻር በተቃራኒ የቆሙ ብቻ ሳይሆኑ የጨቆና እና የብዝበዛ ሰለባ በመሆናቸው አጋር አድርገው ይመለከቷቸዋል። የዶክተር ኃይሌ ታሪክ ትንተና የበለጠ ቁጣን የጨመረው ይህን የሁለት ዘውግ አከፋፈል ዋጋ ቢስ ስለሚያደርገው ነው።እዚህ ላይ ክርክሩ ያለው በአመክንዮ ወይንም ሳይንሳዊ ፈለግን ተከትሎ የሚደረስበት አካዳሚያዊ ድምዳሜ ሳይሆን በአክራሪ ኦሮሞ ብሄረተኞች አይን ይሄኛው ምሁር ከዚህኛው ዘውግ ከመጣ ወገንተኝነት ማሳየት ያለበት ለእውነት ወይንም ሙያዊ ግዴታው ሳይሆን ለመጣበት ጎሳ ወይንም አካባቢ መሆን አለበት የሚለው የጠባብነት መነሻ ነው።ይህ አይነት ጠባብ አክራሪነት በአካዳሚው ዓለም ገብቶ የሚያደርሰው ጉዳት ለጠቅላላው የሃገራችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን በኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ላይ የሚደረጉ የወደፊት ምርምሮች/ጥናቶችን የተዓማኒነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነው።
አክራሪ የሆኑት የኦሮሞ ልሂቃን በዶክተር ሃይሌ ላሬቦ ላይ የመረረ አቁዋም እንዲይዙ ካደረጉ ምክንያቶች ሶስተኛው፣ ምሁሩ ከዚህ ቀደም የጎሳ ፖለቲካ ዝንባሌ ባላቸው የታሪክ ጸሃፊያን የተደረሰውን ልብ-ወለዳዊ ታሪካ ገላልጠው እርቃኑን በማስቀረታቸው ነው። እኒህ አክራሪዎች ዶክተሩን ጠምደው የያዙበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን ለምን እኛ የምንፈልገውን ታሪክ አልነገረንም ነው። በኦሮሞ ጥናት ዘርፍ ውስጥ አዘውትረው ከሚጠቅሱዋቸው ጸሃፊያን መካከል ሲሳይ ኢብሳ፣መኩሪያ ቡልቻ፣አሰፋ ጃለታ፣ እና ቦኒ ሆለኮምብ (ብቸኛዋ የውጭ ሰው) ስራዎች ብንመረምር የአካዳሚክሱን ዓለም ምርመር ስርዓትን ያልተከተለ፣ የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት ተብሎ ብጭቅጫቂ እውነቶችን ከበዙ ውሸት ጋር በማዳበል የተደረሱ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል።እንዳውም በታሪክ እና ስነ-ሰብ ጥናት አንቱ የተባሉ ምሁራን ከላይ በተዘረዘሩት ጸሃፊዎች ስራዎች ላይ ካቀረቡት ሂስ አንዱ ‘በምንም አይነት መለኪያ አካዳሚያዊ ደረጃን የማይመጥኑ’ እንደሆኑ ነው። እነዚህ ከታሪክነት ይልቅ ለፕሮፓጋንዳ ፋይዳ ታልመው የተጻፉ ድርሳናት ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፣በቂም በቀል እና የቁጭት ትረካዎች ላይ በማተኮር ታሪክ ሊኖራት የሚገባትን የመዳኘት ስልጣን እንዲንጋደድ በማድረግ የፖለቲካ መገልገያ እንድትሆን አድርገዋል።የዶክተር ሃይሌ ላሬቦ አደባባይ ወጥቶ የእነዚህን ሃሳውያን የታሪክ ትርክት ገልብጥቡን ያወጡት። የአክራሪ ብሄረተኞቹን ትርክት በተጨበጠ በታሪክ ማስረጃ ሲፈተን ለእውነት ሚዛን ላይ መቀመጥ እንደማይበቃ ዶ/ር ሃይሌ በትንተናቸው አረጋግጠዋል።አክራሪዎቹ የቆሙበትን የሃሰት ትርክት ከስር መሰረቱ በማናጋታቸው ነው የወከባ እና ማሸማቀቅ ሰለባ የሆኑት።
እንደ ሃገር በኢትዮጵያና በኢትዮጳያ ታሪክ ላይ ምህረት የለሽ ትችቶችን እንዲሁም ማጣጣሎችን እንደ ቋሚ ተግባራቸው  ይዘው የነበሩ እኒህ አክራሪ ብሄረተኞች አለን የሚሉትን የታሪክ ትርክት የሚያጠይቅ ባለሙያ ወደ አደባባይ ሲመጣ ዝም የማሰኘት በዘመቻ ሲጠመዱ ማየትን የመሰለ አሳሳቢ ነገር የለም። ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር የለችም፣ታሪኩዋን ደብታራዎች የጻፉት ነው፣ምኒሊክ ጥቁር አፍሪካዊ አይደለሁም ብሎአል፣አቢሲኒያ በ19ኛው ክፍለዘመን ባደረገችው ወረራ 9 ሚልዮን ኦሮሞዎች አልቀዋልን የመሳሰሉ የታሪክ ፍብረካዎችን እንድንቀበል ያልተደረገ ሙከራ አልነበረም። ይባሱኑ ባለሙያው  ታሪክን በተለየ ዓይን እንድናይ በማድረጉ ሃገር ይያዝልን ማለት፣አንድ ጸሃፊ እንዳለው አለን በሚሉት የታሪክ መሰረት የራስ መተማመን ችግር (cultural insecurity) እንደሚጎላቸው ያሳያል።
እንደ ወጉ ከሆነ በዶ/ር ሃይሌ ላሬቦ ትንታኔ ወይንም የታሪክ አቀራረብ አለመስማማኝነት ተገቢ ሲሆን፣ነገር ግን ከጭብጡ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ክሶች በመደርደር አቅጣጫ ለማስቀየር መሞከር እውቀትም ብልጠትም አይደለም።የቀረበውን የታሪክ ትርክት የሚቃወም ወገን አለኝ ከሚለው ማስረጃ እና የታሪክ አተናተን ጋር መቅረብ ሲቻል፣ጉዳዮን ህዝባችን ተሰደበ ተንቋሸሸ በሚሉ አጉዋጉል ምክንያቶች ወደሌላ መውሰድ አክራሪ ብሄረተኞቻችን ምን ያህል ሃገራችንን እና ህዝብን ወደ አደገኛ  መንገድ እየወሰዱአት እንዳለ ያመላክታል።ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ በሃገራችን የአካዳሚክ ምርመር ነጻነት እና ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነት የባሰ አደጋ ውስጥ እየገቡ እንዳለ ጠቋሚ ነው።ይህ ድርጊት ታሪክን ከማጣመም የከፋ ወንጀል ባሻገር፤የሚፈጥራቸው ሌሎች አስከፊ መዘዞችም አሉ። እነዚህ አክራሪ ብሄረተኞች የደረሱበት ነገርን የማደፍረስ እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ጭምር ሌላ አይነት የኢትዮጵያ ታርክ ትርክት ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ  ፋታ የለሽ  የተቀናጀ ዘመቻ መሰረታዊው ምክንያት የኢትዮጵያ ምሁራን – በተለይ ወጣቶች ቸልተኝነት እና በበቂ ሁኔታ የተቀናጀ እና ተከታታይነት ያለው ምላሽ የመስጠት ጥረት ባለመኖሩ ነው።

No comments:

Post a Comment