(BBN News) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ህዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ገቢ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ አየር መንገዱ ስድስት ቢሊየን ብር ትርፍ ቢያገኝም፣ ህዝባዊ ተቃውሞው በገቢው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በኢትዮጵያ የተከሰተው ህዝባዊ ዓመጽ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከባድ ተፅዕኖ ማሳረፉ እና ሊገኝ የታቀደውን ገቢ ማሳጣቱ ሲነገር ቆይቷል፡፡
ምንም እንኳን ባለፈው በጀት ዓመት ማለትም ከ2015 እስከ 2016 በነበረው ጊዜ ተቃውመ ካለመነሳቱ ጋር ተያይዞ በአየር መንገዱ ላይ የደረሰ የገቢ ተጽዕኖ ባይኖርም፣ በአዲሱ በጀት ዓመት ግን፣ ህዝባዊ ተቃውሞዉ በአየር መንገዱ ገቢ ላይ ጥላ ማጥላቱን አቶ ተወልደ አልሸሸጉም፡፡ ‹‹ከመንገደኛ ፍሰት ውስጥ 70 በመቶ በላይ መንገደኞቻችን ትራንዚት የሚያደርጉ (በአዲስ አበባ በኩል ወደ ሌላ አገር የሚሄዱ) በመሆኑ አለመረጋጋቱ ከፍተኛ ተፅዕኖ አላደረሰብንም፡፡›› ያሉት ስራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ሆኖም በተቃውሞ የተነሳ በአዲሱ በጀት ዓመት ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡ መንገደኞች ላይ የቁጥር መቀነስ ተመልክተናል›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል አየር መንገዱ በውጭ ምንዛሪ እጥረት መቸገሩን ስራ አስፈጻሚው የገለጹ ሲሆን፣ ችግሩ የተከሰተውም ከነዳጅ ዋጋ ጋር ተያይዞ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ነዳጅ አምራች አገሮች በገጠማቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት አየር መንገዶች በእነዚህ አገሮች ያከናወኑትን ሽያጭ ወደ ራሳቸው ማስተላለፍ እንዳልቻሉ የገለጹት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በዋነኛነት በናይጄሪያ፣ በአንጎላ፣ በሱዳንና በግብፅ በየአገሮቹ ገንዘብ የሸጠውን 220 ሚሊዮን ዶላር ወደ አገሩ ማስተላለፍ አልቻለም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተመሰረተ ሰባ ዓመት አስቆጥሯል፡፡
No comments:
Post a Comment