26ኛው ዙር ወጥቷል! ሀብታም ጋቢ ተከናንቧል! ገንዘብ በአገሩ ጠፍቷል!
(ዋዜማ ራዲዮ)
ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ!
ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ ነኝ፡፡ ምስጉን ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› ስለመሆኔ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባም ኩማም ያውቃሉ፡፡
ዉሎና አዳሬ ‹‹ብሔራዊ››፣ ጠባዬ የባሕታዊ፣ ‹‹ላየን ባር›› ቤቴ፣ ‹‹ቴሌ ባር›› ግዛቴ…፡፡
ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ…ሄሄሄ የዛሬ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው!!
እርስዎ ግን እንዴት ነዎት?
ቢዝነስ ጥሩ እንዳይደለ አይንገሩኝ ጌታዬ! አውቀዋለሁ፡፡ ሥራ ጠፋ አይበሉኝ፣ እረዳለሁ፡፡ እርስዎ ጋ ብቻ አይደለም! ሁሉም ጋ ነው፡፡ እውነት ለመናገር አስደንጋጭ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ነው ፊንፊኔን የገጠማት፡፡ ዜና ስለማይከታተሉ ነው እንጂ ይህ ነገር በተቀረው ዓለም አዲስ አይደለም፡፡ እንኳን ፊንፊኔን ግሪክም ይሄ ነገር ገጥሟት ያውቃል፡፡ እርስዎ ጋዜጣ ስለማያነቡ ይሆናል ያላወቁት፡፡ ይቅርታ ያርጉልኝና እርስዎ ገንዘብ እንጂ ዜና መቼ ይከታተሉና፤ ለዚያ ይሆናል ያልሰሙት፡፡
በብዙ አገር ኢኮኖሚ ላሽቆ ያውቃል፡፡ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በፊንፊኔም የኾነው ይኸው ነው፣ ሌላ አይደለም፡፡
ልንገርዎታ!
ለምሳሌ የካልዲሷ ወይዘሮ ፀደይ አስራት የአራት ኪሎ ቅርንጫፏን ዘግታለች፡፡ አብዛኛው ካልዲስ አፉን ከፍቶ ነው የሚዉለው፡፡ ሥራ የለማ! ሸዋ ዳቦዎች የኢሊያና ሆቴሉን ቢሎስ ኬክ ቤት ድርግም አርገው ዘግተዋል፡፡ ገበያ የለማ! አሁን ኬኩን ትተው ዳቦውን በጥሞና እየሸጡት ይገኛሉ፡፡ እውነቴን ነው!
ደሞ ልንገርዎ!
ይሄ ጌቱ ገለቴ ዱባይ ከኢሚሮች ጋ በዉስኪ ቢራጭ አይግረምዎ! የጌቱ ኮሜርሻል ተከራዮች በገበያ እጦት በአሁን ሰዓት በእንባ እየተራጩ ነው የሚገኙት፡፡ የመገናኛው ዘፍመሽ ላይ ዝር የሚል ወፍ ጠፍቷል፡፡ ደንበል እንዲሁ ጧት ይከፈታል፣ ማታ ይዘጋል፡፡ የመርካቶ ነጋዴዎች አይሱዙ ላይ እቃ የሚያስጭን ነጋዴ ቢጠፋባቸው ስልካቸው ላይ ጌም እያስጫኑ ነው፡፡ ሥራ የለማ! እያዛጉ እስክስታ ሆኗል እኮ ነገሩ፡፡
ከሁሉም ከሁሉም ባንኮች አንጀት ይበላሉ፡፡ ደንበኞቻቸው ጋር እየደወሉ ገንዘብ አስቀምጡ ይላሉ፡፡ በሌለ ገንዘብ፡፡ ጉም በኾነ ገንዘብ፡፡
ጌታዬ! ዛሬ እንኳን ያበደሩት ይቅርና ካርድ ያጎረሱት ኤቲኤም ማሽን ብር መስጠት አቁሞ የለም እንዴ!! በፊት በፊት No network ነበር የሚለው፡፡ አሁን አሁን No Money ማለት ጀምሯል፡፡
ፊንፊኔ እኮ ተቀዛቅዛ ተቀዛቅዛ የጎርደን በረዶ ኾናለች፡፡ ብር የገባበት አልታወቀም፡፡
የሚገርም ጊዜ ነው!! ሀብታሙ ከድሀው እኩል የሚያለቅስበት ጊዜ ላይ ደረሰናል፡፡
ለምሳሌ የኔ ደንበኞች በሙሉ ንብረት አላቸው፡፡ ብር ግን የላቸውም፡፡ ሁሉም ንብረታቸውን ወደ ብር እንድቀይርላቸው ይማጸኑኛል፡፡ ያልተረዱኝ ግን በአሁኑ ሰዓት በፊንፊኔ ሁሉም ገዢ ወደ ሻጭነት መቀየሩን ነው፡፡ አሃ! ሰው ሁሉ ሻጭ ከሆነ ገዢው ማን ሊሆን ይችላል?
ለምሳሌ ባልደራስ ሦስት መኝታ ኮንዶሚንየም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ከሸጥኩ ሦሰት ወር አልሞላኝም፡፡ አሁን በስምንት መቶ ሺ ጥንቡን ጥሏል፡፡ ለምሳሌ ሲኤምሲ አንድ ቅልብጭ ቪላ 6 ሚሊዮን ያወጣ ነበር፡፡ አሁን አምስት የሚቆጥር ጠፋ፡፡
አትላስ መደዳ አስፋልት የሚያዩ ባዶ ቦታዎች በሙሉ በ25 ሚሊዮን የቸበቸብኳቸው እኔ ገረመው ነኝ፡፡ ዛሬ በ20 ሚሊዮንም ዞር ብሎ የሚያያቸው ጠፍቷል፡፡ የአቶ የማነ ካፒታል ሆቴል ይሸጣል! የፊንፊኔ አብዛኛው ጅምር ፎቅ ይሸጣል፡፡ ማን ይግዛው!!
አያት ሪልስቴት ቤት ገዢ አጥቶ ልመና ገብቷል፡፡ እንዳውም በአሁኑ ሰዓት ያልተገነባ ሪልስቴት በነጻም ዉድ ነው እየተባለ ነው፡፡ የሚገርም ነገር እኮ ነው የኾነው!
በገጠር አምስት ሚሊዮን ወገን ድርቅ መታው ይባላል፡፡ የከተማውን ማን አየ!! ለሐብታም ረሐብ ማለት የሚላስ ዳቦ ማጣት እንዳይመስልዎ! የገበያ ድርቅ ከመታው ማንኛውም ሐብታም ይቆረፍዳል፤ ይቆራመዳል፣ ይጃጃል፣ ይፋጃል፡፡
በዚህ መሐል ነው እንግዲህ ኦቦ ድሪባ ኩባ ጨረታ ያወጡት፡፡ አልሰሙም ይሆናል ጌታዬ! 26ኛው ሊዝ የመሬት ጨረታ ወጥቷል እኮ! እና ምን ይጠበስ ነው ያሉኝ??
የደወልኩላቸው ደንበኞቼ ሁሉ እንዲያ ነው ያሉኝ፡፡ የሊዝ ጨረታ መዉጣቱን ስነግራቸው ጆሮዬ ላይ ስልክ የዘጉብኝ አሉ፡፡ አሃ ልክ ነዋ! አይፈረድባቸውም፡፡ አልተቀየምኳቸውም፡፡ በዚህ ሰዓት ገዢ መሆን የሚፈልግ ማን አለ!! እንኳን ቤት መሬቱ የባህር ትራንዚቱ ለገበያ ቀርቦ የለም እንዴ!!!!
ጌታዬ!!
በሳምንት ሦስት ጊዜ መታተም የጀመረው አዲስ ልሣን ጋዜጣ ማክሰኞ ለታ 176 ኪስ ቦታዎች ለገበያ መቅረባቸውን በፊት ገጹ ያበስራል፡፡ ለኔ ግን መርዶ ነው፡፡ ለደንበኞቼም እንዲሁ፡፡ በዚህ ሰዓት ማን ነው ገንዘቡን በትኖ መሬት የሚቀራመት፡፡
እኔ ግን 26ኛ ዙር ጨረታ ወጣ ቢሉኝ ጥያቄ አለኝ እልኩኝ፡፡ ለኦቦ ድሪባ!! የ25ኛው ዙር መቼ ተሸጠና፣ ለ24ኛ ዙር ማን ከፈለና፡፡ አዳሜ ይሄን ገንዘብ በጨረታ ፎርም ሞጅራ ሞጅራ ክፈል ስትባል አይደለም እንዴ ፈሷን ጥላ የጠፋችው!! ፎርም ላይ ብዙ ዜሮ መጻፍ ቀላል ነው፡፡ ቼክ ላይ ነው ከባድ፡፡
እርስዎ ግን እንዴት ነዎት ጌታዬ!!
ትዝ ይልዎ እንደሁ ባለፈው ጊዜ በአሜሪካን ግቢ ጉድ ተሰምቶ ነበር፡፡ ጣሊያን ወርቅ ቀብሮ የተሰወረ እስኪመስለን ድረስ ለቁራሽ መሬት ሚሊዮን ሲከሰከስ ነበር፡፡ ያ ለካሬ 355ሺ 500 ብር ሰጥቶ አገር ጉድ ሲያሰኝ የነበረው ጋርደን ሪልስቴት አሁን የገባበት አልታወቀም፡፡ እውነቴን ነው!! ለጨረታ ማስከበርያ ያስያዘው አራት መቶ ሺህ ብርም ቀልጧል፡፡ ቦታውም ለድጋሚ ጨረታ ቀርቧል፡፡
ጋርድን ሪልስቴት ብቻ መሰልዎ እንዴ እምጥ ይሁን ስምጥ የገባበት ያልታወቀ?? ኸረ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከርሱ ጎረቤት እንጅሎፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለ964 ካሬ ቦታ ለአንዲት ካሬ 311ሺህ 500 ብር አቅርቦ አሸንፎም ነበር፡፡ ዉሰድ ሲባል ግን ጠፋ፡፡ ለጨረታ ማስከበርያ ያስያዘው 3መቶ ሺህ ብር ቀልጧል፡፡ ቦታው ለድጋሚ ጨረታ ቀርቧል፡፡
እዛው ሰፈር አቶ ሙዘሚል መሐመድ አሕመድ ለ343 ካሬ ቁራሽ መሬት ያቀረቡት ዋጋ አነጋጋሪ ኾኖ ነበር፡፡ ቦታው አሜሪካ ግቢ የሚገኝ ቢኾንም አሜሪካን አገር የሚገኙት የአቶ ሙዘሚል ዘመዶች ሳይቀሩ ሰውየውን “አብደዋል ወይ!፣ እዚህ እኛ አገር እንኳ ለመሬት እንዲህ ውድ ብር አይቀርብም” ብለው ስለኮነኗቸው ያስያዙትን መቶ ሺ ብር ቀልጧል፡፡ ቦታውም ለድጋሚ ጨረታ ቀርቧል፡፡
ጌታዬ! ያ የእብደት ዘመን ያበቃ ይመስላል፡፡ አሁን ሌላ ታሪክ የምንሰማበት ወቅት ነው የሚኾነው፡፡
ከትናንት በስቲያ ከአስሩ ክፍለ ከተሞች ሰባቱ መሬት አቅርበዋል፣ በርከት ያለ መሬት ነው ታዲያ! በድምሩ 176 ቦታዎች ገበያ አልወጡም ብለው ነው?!
በንፋስ ስልክ ላፍቶ 18 ቦታዎች፣ በቦሌ ወረዳ 9 እና 10 አያትና ጎሩ እንዲሁም ቦሌ ለሚ አካባቢ የሚገኙ 94 ቦታዎች፣ በኮልፌ ወረዳ 7 እና ወረዳ 3 የሚገኙ 23 ቦታዎች፣ በየካ ወረዳ 1 እና ወረዳ 3 የሚገኙ ስፋታቸው 150 ካሬ የሆኑ ዘጠኝ ቦታዎች፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድና ወረዳ 10 የሚገኙ 13 ቦታዎች፣ በቂርቆስ አፍሪካ ኅብረትን የሚጎራበቱና ስፋታቸው 1300 ካሬ የሚኾኑ ሁለት ቦታዎች፣ በልደታ ወረዳ 10 የሚገኙ ስፋታቸው አንድ ሺ ካሬ የሚሆኑ 2 ቦታዎች፣ በአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ 4 እና ወረዳ 9 ገላን ኮንዶሚንየም አካባቢ የሚገኙ 13 ቦታዎች ለገበያ ቀርበዋል፡፡
መሬት እንዲህ እንዳሁኑ በርከት ብሎ እንደ ቲማቲም ለገበያ ሲቀርብ ይረክሳል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ቸር ወሬ ያሰማን!
ደጋግሜ እንደነገርክዎ እኔ ገረመው በፊንፊኔ መሬት ጥርሴን ነቅያለሁ፡፡ አሁን ግን ሥራ አጥቻለሁ፡፡ ሥራ ያጣ ቄስ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል፡፡ ሥራ ያጣ ደላላ ምን ያደርጋል?
ጌታዬ! በኔ በኩል ስንቅ መቋጠር ቢያቅተኝ ስንኝ እቋጥራለሁ፡፡ ለዚህ ክፉ ዘመን ብቀኝ ማን ምን ይለኛል!!
ንብረት ጥንቡል ጣለ፡፡
ሻጭም ጨርቁን ጣለ፡፡
ገንዘብ የት ነህ ቢሉት ጉም ኾኛለሁ አለ!
ገረመው ገረመው ለምን ትለኛለህ!
ገንዘብ ያልገረመው የት አይተህ ታውቃለህ፡፡
ደላላው ደላላው ለምን ትለኛለህ
ገንዘብ ያልደለለው ማን አይተህ ታውቃለህ!
ጌታዬ! እንደኔ የሚደለል ጠፍቶ የሰው ፊት ከማየት ይሰውርዎ!!!
ገረመው ግዛው ነኝ (ከላየን ባር)
No comments:
Post a Comment