Monday, February 6, 2017

ለዉይይት ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ የለበትም – #ግርማ_ካሳ

   


በኢሕአዴግ እና በተቃዋሚዎች መካከል ድርድሮች እንደተጀመሩ ሰምተናል። አንዳንድ ወገኖች በድርድሩ ላይ ጥያቄ ምልክት አላቸው። በድርድሩም ምንም አይነት ዉጤት እንደማይገኝ ነው እየነገሩን ያሉት፡፡ አንደኛ በድርድርና በዉይይት ችግሮችን ለመፍታት መሞከር የሰለጠነ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ፖለቲካ ነው። ሁለተኛ በድርድርና በዉይይት ችግሮችን ለመፍታት ካልተቻለ ችግሮችን ለመፍታት የሚቻልበት መንገድ በራሱ አጠያያቂ ነው። ወያኔን ስለማስወገድ ይነገራል። “ወያኔ መወገድ አለበት” ይባላል። ግን “ወያኔ መወገድ አለበት” ማለትና “ወያኔን ማስወገድ ሰማይና ምድር እንደሚራራቁ የተረዳን አይመስለኝም።
በሲሪያ ከስድስት አመታት በፊት ሕዝቡ የሚያደርገው ሰላማዊ ትግል ብዙ ጊዜ ሳይሰጠው በቶሎ ነው ወደ ትጥቅ ትግል የተለወጠው። ሲሪያ አሁን የደረሰችበት ደረጃ ደረሰች። የሕዝቡን ተቃዉሞ exploit በማድረግም አሸባሪዎች ተፈለፈሉ። ይኸው በመጨረሻ ከተላለቁ በኋላ ተቃዋሚዎች ወደ ጠረቤዛ ዙሪያ እየመጡ ነው። ችግሮች በዉይይት ለመፍታት እየሞከሩ ነው።
ታዲያ በኛስ አገር ዉይይት ለምን ይጠላል ? ለዉይይትስ ቅድመ ሁኔታ ለምን ይቀመጣል ? ለምን መወያየት መፈለግ እንደ ድክመት ይቆጠራል ? በተለይም በዉጭ ያሉ ሃይሎች ችግር እየፈጠሩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። እነዚህ ሃይላት ዉይይቱን የማይፈልጉት በርግጥ “ዉይይቱ ከጥቁሙ ጉዳቱ ይበለጣል፤ የተሻለ አማራጭ አለን፣ ይሄ …” በሚል ነው ? ወይስ እነርሱ በዉይይቱ ስላልተጋበዙ ነው ?
ከዚህ በፊት የጻፍኩት አንዲትን ጽሁፍ አሻሽዬው እንደገና ለማቅረብ ወደድኩ። ምን አልባትን በዉይይት ረገድ አንዳንድ ሐሳቦችን ሊሰጠን ይችላል ብዬ አስባለሁ።
======
የአሥራ ሰባት አመት ወጣት ነዉ። ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ በእጁ ይዟል። እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ፣ ንግግር አድርገዉ ወደ ጨረሱ አንድ የእድሜ ባለጸጋ ሰዉዬ ቀስ በቀስ ይጠጋል። ሳያስቡት የያዘዉን ሽጉጥ ወደ እርሳቸዉ ደቅኖ ይተኩሳል። ሰውየዉ ይወድቃሉ። አካባቢዉ ተረበሸ። ተናወጠ። አምቡላንስ ተጠርቶ በአፋጣኝ በስፍራዉ ደረሰ። የወደቁትን አባት በአምቡላንሱ የነበሩ የህክምና ባለሞያዎች አነሷቸዉ። የፍጥነት ጉዞ ወደ ሆስፒታል ጀመሩ። ሆስፒታል ሳይደርሱ በመንገድ ላይ የኝህ ሰዉ ሕይወት አለፈች።ይህ ወጣት ይጋል አሚር ይባላል። ተኩሶ የገደላቸዉም ሰዉ፣ የቀድሞ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ይሳቅ ራቢን ነበሩ።
ይሳቅ ራቢን እድሜ ዘመናቸዉን በሙሉ የጥይትና የመድፍ ድምጽ በመስማት ያሳለፉ ጦረኛ ወታደር ነበሩ። በፈረንጆች አቆጣጠር በ1941 ከታዋቂዉ ሞሼ ዳያን ጋር የፓልማክ ግብረኃይል አባል ሆነዉ፣ ያኔ በፈረሳንዮች ቅኝ ግዛት ስር በነበረችዉ በሊባኖስ የናዚ ጀርመን ደጋፊ የነበረዉ የፈረንሳይ ቪቺ መንግስት ወታደሮች ጋር ተዋግተዋል። በዚያ ጦርነት ጊዜ ነበር ሞሼ ዳያን አንድ አይናቸዉን ያጡት።
ከዚያ በኋላ ከአረቦች ጋር በተደረጉት ተከታታይ ጦርነቶች ትልቅ ጀግንነትና የውትድርና ብቃት ያሳዩ፣ በእሥራኤል ታሪክ አሉ ይባሉ ከነበሩት ታላቅ የጦር መሪዎች አንዱ ነበሩ። የእሥራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የጦሩ የኢታ ማጆር ሹም ሆነውም አገልግለዋል።
ይሳቅ ራቢን «እኔ ሰላም ሳላይ እድሜዬን ጨርሻለሁ። ለልጆቻችን ሰላም ማምጣት አለብን» በሚል እምነት፣ ድፍረት የተሞላበት የሰላም እርምጃ ወሰዱ። የእሥራኤል ጠላቶች ከሚባሉ ጋር መነጋገር ጀመሩ።
ኢሳቅ ራቢን ከመገደላቸዉ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተናገሩት፣ ለእኛ ለኢትዮጵያዉያንና ለመሪዎቻችን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ አስደናቂ አባባል ነበር ። «የሰላም መንገድ ከጦርነት ይሻላል። ይሄን የምለዉ እንደ አንድ ወታደር ነዉ። መከላከያ ሚኒስቴር ሆኜ የእስራኤል ወታደሮች ቤተሰቦች ስቃይ ይሰማኛል። ለነርሱ፣ ለልጆቻችን፣ ለልጅ ልጆቻችን ስንል መንግስታችን ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ማንኛዉንም ቀዳዳ፣ ማንኛዉንም እድል መጠቀም አለበት። ሰላም አንድ ጸሎት ብቻ አይደለም። ሰላም የጸሎታችን መጀመሪያ ነዉ» ነበር ያሉት።
የጦርነትን ፣ የጥላቻና የእልህ ፖለቲካ አደገኛነቱን ያወቁታልና፣ አብረዋቸዉ የነበሩ ጓደኞቻቸዉ ሲረግፉ፣ አካለ ስንኩል ሲሆን፣ ንብረት ሲወድም ፣ ሰዉ በሰዉ ላይ ሲጨክንና አዉሬ ሲሆን አይተዋልና፣ እርሳቸዉ የኖሩበትን በጦርነት የተበከለን አየር ለልጅ ልጆቻቸዉ ማዉረስ አልፈለጉም። እርሳቸዉ ይመኙትና ይናፍቁት የነበረዉን ሰላም፣ እርሳቸዉ ባያገኙትም እንኳን፣ የልጅ ልጆቻቸዉ እንዲያገኙ መደረግ ያለበትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸዉ ተገነዘቡ። «ለልጅ ልጆቻችን ስንል ሰላም እንዲመጣ የተገኘችዋን ቀዳዳ ሁሉ መጠቀም አለብን» በሚል ጽኑ አምነት፣ በጦርነት ያልሆነ፣ የወስጥና የልብ ጀግንነት ለማሳየት ተንቀሳቀሱ። የእሥራኤል ጠላት ከተባሉት ከነያሲር አራፋት ጋር መነጋገር ጀመሩ።
ብዙ ተቃዉሞ መጣባቸዉ። እነ ናታንያሁ ተነሱባቸዉ። ግትር ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ በጭንቅላት ሳይሆን በጠመንጃ የሚያምኑ፣ እነርሱ ብቻ ከሌላዉ እንደተሻሉ አድርገዉ በመቆጠር በትእቢት የተወጠሩ፣ ከነርሱ ዘር ዉጫ ለሌላዉ ግድ የማይሰጣቸዉ ሰዎች በርሳቸዉ ላይ ማንጎራጎር ጀመሩ።
ኢሳቅ ራቢን ግን ወደ ኋላ አላሉም። «የሰላም ጠላቶች አሉ። ሊጎዱን፣ የሰላሙን መንገድ ሊያጨናግፉን የሚፈልጉ። በድፍረት እናገራለሁ። ከፍልስጤማዉያን መካከል የወጣዉ፣ በፊት ጠላታችን የነበረዉ የፍልስጤም ነጻ አውጭ ግንባር አሁን የሰላም አጋራችን ሆኗል» ሲሉ ከቀድሞ ጠላቶቻቸዉ መካከል ወዳጆችን እንዳፈሩ ተናገሩ። ከያሲር አራፋት ጋር በአንድ ላይ ለሰላም ቆሙ። ኢሳቅ ራቢን በጦርነት ሊያጠፉት ያልቻሉትን የያሲር አራፋትን ቡድን በሰላም አሸነፉት።
ታዲያ ለዘመናት በጦር ሜዳ ሲዋጉ በጥይት ያልተመቱት እኝህ ታላቅ ሰዉ፣ በሰላሙ ሜዳ በቴላቪቭ ከተማ ጥይት አገኘቻቸዉ። ለሰላም ለፍቅር ለወንድማማችነት ሲሉ ወደቁ። እጅግ ታሪካዊ፣ ተወዳጅ የሰላም ሰዉ !!!!
የይሳቅ ራቢንን ታሪክ ያለምክንያት አላመጣሁትም። አንዳንዶችን ተቃዋሚዎችን መጨፍለቅ ጀግንነት ይመስለናል። አንዳንዶች ኃይልን የምንመዝነዉ በያዝነዉ ብረትና በዘረጋነዉ የሥለላ አዉታር ነዉ። መነጋገር፣ መወያየት፣ ፍቅርና መግባባት ፣ በጦርነትም ሆነ በጉልበት ከሚገኝ ጊዚያዊ መፍትሄ የበለጠ ዘለቄታ ያለዉ ጥቅም ሊያመጣ እንዲሚችል አናስብም። የሩቁን፣ እኛ ካለፍን በኋላ በልጆቻችንና በልጅ ልጆቻችን ዘመን ሊፈጠር የሚችለዉን፣ ለሁላችንም የሚበጀዉን አንመለከትም። ጊዚያዊ ጥቅማችንንና ስልጣናችን ላይ ብቻ በማተኮር ግትር ፖለቲካ እናራምዳለን።
እንደ ኢሳቅ ራቢን አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት (ከአቶ ኃይለማሪያም ጀርባ ያሉት) ከወጣትነታቸዉ ጀምሮ ጦርነትን ያዩ፣ በጦርነት የኖሩ ሰዎች ናቸዉ። በታሪክ ስለሚኖራቸዉ ቦታ፣ ስለ ልጆቻቸዉና የልጅ ልጆቻቸዉ ማሰባ አለባቸዉ እላለሁኝ። ጸረ-ሽብርተኝነትን ለመቋቋም ተብሎ የወጣዉ አዋጅ ፣ በዚህ አዋጅ መሰረትም፣ ለሰላማዊና ለሕጋዊ ትግል ጠንካራ አቋም ያላቸዉ እነ እስክንደር ነጋን አንዱዋለም አራጌ እንዲሁም ሌሎች በርካታ በሽብር ወንጀል ተከሰዉ ወደ ወህኒ መዉረዳቸዉ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተቃዋሚዎች ላይ በየወረዳዉና በየክልሉ የሚደርሰዉ ወከባ፣ የአንድነት ፓርቲ መታገድ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ … ኢሕአዴግን ከሕዝብ ጋር የሚያጣሉ፣ ጥላቻን እንዲሰፋ የሚያደርጉ፣ ዜጎች የበለጠ ወደ ከረረ አቋም እንዲሄዱ የሚገፋፉ እንጂ፣ የመግባባትንና የእርቅን መንፈስ የሚያመጡ አይደለም።
ተናዶ የኃይል እርምጃ መወሰድ፣ በበቀል መነሳሳት፣ ሰውን ማዋረድ፣ ሰዉን መስደብ፣ ሰዉን መክሰስ በጣም ቀላል ነዉ። በአይናችን ላይ ትልቅ ምሰሶ እያለ የሌላዉን ጉዳፍ ማየት፣ የተገነባዉን ማፍረስ፣ አገርን ከድህነት ወደ ድህነት ማውረድ፣ ጠላቶችን ማፍራት፣ ሕዝብን ከሕዝብ መከፋፈል፣ ወንድምን ከወንድም ማጣላት አስቸጋሪ አይደለም።ይሳቅ ራቢን እንዳደረጉት ጠላት የነበሩትን ወዳጅ ማድረግ፣ የፈረሰዉን መገንባት፣ አገርን ከድህነት ማውጣት፣ ችግሮችን በዉይይት መፍታት፣ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ የተበተኑትን መሰብሰብ፣ ትችትና ወቀሳን በትህትና ተቀብሎ ስድብና አሉባልታን ደግሞ ንቆ ነገሮችን በትእግስት ማሳለፍ ግን እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነዉ።
ስለሆነም ኢሕአዴጎች አሁንም የቀናዉን መንገድ እንዲይዙና ለእርቅና ለብሄራዊ መግባባት መዘጋጀታቸዉን ለማሳየት ተጨባጭ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲነሱ ጥሪ እንደወትሮው በድጋሜ አቀርባለሁ። እርግጥ ነው በመልክም አስተዳደር ዙሪያ ችግር እንዳለባቸው በግልጽ አምነዋል። ከምሁራን ጋር፣ ከተቃዋሚ ደርጅቶች ጋር ለመነጋገር የሞከሩበት ሁኔታም አለ። ሆኖም ንግግር ብቻ በራሱ ምንም አይደለም። ኢሕአዴግ በርግጥም በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለው በተግባር ማሳየት አለበት። ተግባር ተግባር፣ ተግባር ያስፈልጋል። ለምሳሌ፣ አንሳ ሱኪ በበርማ እንዳደረገችው፣ የሕሊና እስረኞችን በሙሉ መፍታት፤ ከተቃዋሚዎች ጋር የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ የሚሆንበትን ሁኔታ ቅንነት ባለው ሁኔታ መነጋገር እና እንደ ጸረ-ሽብርተኝነት ያሉ አፋኝ ሕጎችን መሰረዝ ወይንም ማሻሻል ያሉት አገዛዙ በቀላሉ ሊተገብራቸው የሚችላቸው ተግባራት ናቸው።
በአገራችን እርቅና ሰላም እንዲመጣ ማድረጉ የኢሕአዴግ ብቻ ሃላፊነት አይደለም። ኢሕአዴግን እንቃወማለን በምንልም ወገኖች በኩል መደረግ ያለበት ቁልፍ ጉዳዮች አሉ ብዬ አምናለሁ። ሰላም በአንድ በኩል ብቻ አይደለም። እኛ «ኢሕአዴጎች ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይደሉም» ብለን እንደምንከሳቸው ሁሉ እነርሱም በበኩላቸዉ «ስልጣን ብንለቅ አይለቁንም፣ በሰላም መኖር አንችልም» የሚል ፍርሃት ሊኖርባቸው ይችላል ብዬ አምናለሁ። በዚህም ምክንያት እርቅ ለመመስረት ፍላጎቱ ቢኖራቸዉም፣ ከፍራቻ የተነሳ፣ በሰላም ስልጣን ከለቀቅን መገደላችን ካልቀረ፣ እስከተቻለን ድረስ ስልጣናችንን ማቆየት አለብን የሚል ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። ይህ እንግዲህ እርቅ እንዳይመጣ ሁላችንም ወደ ባሰ ደረጃ እንዳንደርስ የሚያደርገን ነዉ።
እንግዲህ በዚህ ረገድ የተቃዋሚ ጎራዉ፣ የሰለጠነ፣ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ (ኢሕአዴጎችን ጨምሮ) የሚያቀራርብ፣ በበቀልና በጥላቻ ላይ ሳይሆን በፍቅርና በይቅርታ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዎች ማራመድ ይጠበቅበታል። አሁን አሉ የሚባሉት ተቃዋሚ ድርጅቶች ትልቅ የብስለት ችግር አለባቸው። መብስል ይኖርባቸዋል። ብሶት ብቻ ነው የሚያሰሙት እንጂ አማራጫ በማሰማት ለሕዝቡ ተስፋ ሲሆኑ አይታዩም። ያ መለወጥ አለበት።
ሁላችንም በአስተሳሰብ ታድሰን የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች እንደ ወንድማማቾች፣ በዘር፣ በሃይማኖት ሳንከፋፈል፣ በመመካከር፣ በመቀባበለና በመያያዝ መፍታት ካልቻል፣ በመካከላችን ያሉትን ልዩነቶች እያሰፋን እና በነገሮች እያከረርን ከመጣን፣ የሰው ልጅ መሰረታዊ የስብእና እና የዜግነት መብቱ ያለ ገደብ የሚከበርባትና ሕግ የበላይ የሆነባትን ኢትዮጵያ ካልገነባን እንደ አገር እና እንደ ሕዝብ እንጠፋለን። በፍቅር አገራችንን እንገባ። የአመለካከት ለዉጦች እናደርግ። በዋናነት መልእክቱ አራት ኪሎ ላሉ ባለስልጣናት ቢሆንም፣ ሌሎቻችንን ይመለከታል:

No comments:

Post a Comment