Monday, February 13, 2017

127 የአሜሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች፤ የትራምፕን የጉዞ ገደብ በመቃወም ክስ መስርተዋል

   


127 የአሜሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች፤ የትራምፕን የጉዞ ገደብ በመቃወም ክስ መስርተዋል
ከአሜሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች ግማሽ ያህሉ በስደተኞች የተቋቋሙ ናቸው

ጎግል፣ አፕል እና ማይክሮሶፍትን ጨምሮ 127 የአሜሪካ ታላላቅ ኩባንያዎች፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ያወጡት የስደተኞች የጉዞ ገደብ የስደተኞችን ህጎችና ህገ-መንግስቱን የሚጥስ ነው በሚል የተቃወሙት ሲሆን በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በጋራ ክስ መመስረታቸው ተዘግቧል፡፡
በአብዛኛው በቴክኖሎጂ መስክ ላይ የተሰማሩት እነዚህ ኩባንያዎች፣ በጋራ በመሰረቱት ክስ፤ ስደተኞች በአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ በመጠቆም፣ ትራምፕ ስደተኞች ለተወሰነ ጊዜ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከላቸው በአገሪቱ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ሊነሳ ይገባል በሚል በክሳቸው ማመልከታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከላቸው የአገሪቱ ኩባንያዎች የውጭ አገራት ምርጥ ባለሙያዎችን እንዳይቀጥሩና እንዳያሰሩ እክል ይፈጥራል ያሉት ኩባንያዎቹ፤ ተመልሰው የመግባታቸው ጉዳይ አስተማማኝ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ሰራተኞቻቸውን ወደ ሌሎች አገራት ለስብሰባና ለልምድ ልውውጥ ለመላክ እንደሚያስቸግራቸውም ገልጸዋል፡፡
ከአሜሪካ 500 ታላላቅ ኩባንያዎች መካከል 200 ያህሉ በሌሎች አገራት ስደተኞችና ከስደተኞች በተወለዱ ልጆች የተቋቋሙ መሆናቸውን ታዋቂው ፎርቹን መጽሄት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ማስታወቁን ያስታወሱት ኩባንያዎቹ፤” ይህም በንግድና ቢዝነሱ መስክ የጎላ ሚና የሚጫወቱትን ስደተኞች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ መከልከል ኢኮኖሚውን ማዳከምና አዳዲስ ኩባንያዎች እንዳይፈጠሩ እንቅፋት መፍጠር እንደሆነ ያመለክታል” ማለታቸውንም ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡

No comments:

Post a Comment