ሪፖርቱም ቃለጉባዬውም ኣልተፃፈም። ሰነፍ አገዛዝ የወለዳት የሚኒስትሩ ፀሀፊ አሉባልታ – ቆንጂት ስጦታው
=========================================================================
=========================================================================
[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነሽ?
- በጣም ስፈልግዎት ነበር፡፡
- ለምን?
- ሰሞኑን ምነው ቢሮ አልገቡም?
- ስብሰባዎች ነበሩብኛ፡፡
- ከዛሬ ነገ ይገባሉ እያልኩኝ ስጠብቅዎት ነበር፡፡
- ይኼን ያህል?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ገጥሞሽ ነው?
- በጣም ወሳኝ ጉዳይ፡፡
- እኮ ምን?
- አንድ የእኛ ጥበቃ ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነበር፡፡
- ኦኬ፡፡
- እዚህ እኛ ጋ ክበብ የምትሠራ ልጅ ነበረች፡፡
- እሺ፡፡
- ጥበቃውን አወቁት በጣም ረጅሙ ማለቴ ነው፡፡
- ያወቅኩት መሰለኝ፡፡
- ልጅቷንስ አወቋት?
- ኧረ አላወቅኳትም፡፡
- ለነገሩ እርስዎ ክበብ አይጠቀሙም፡፡
- አሁን ፖለቲካሽን ትተሽ ወደ ጉዳዩ፡፡
- እና ይኸውልዎት ሁለቱ ግንኙነት ይጀምራሉ፡፡
- አንድ መሥሪያ ቤት አይደል እንዴ የሚሠሩት ቢገናኙ ምን ችግር አለው?
- የሥራ ግንኙነት አይደለም የምልዎት?
- ታዲያ የጥቅም ግንኙነት ነው?
- ኧረ እንደሱም አይደለም፡፡
- ታዲያ ምን ዓይነት ግንኙነት ነው?
- ሁለቱም እፍ ይላሉ፡፡
- እ….
- ከዛም ልጅቷ ኦፕ ትላለች፡፡
- ምንድን ነው የምታወሪው?
- አልገባዎትም ክቡር ሚኒስትር?
- እፍ፣ ኦፕ እያልሽኝ ምን ይገባኛል?
- ልጅቷ ከጥበቃው ጋር በፍቅር አብዳ አረገዘች እያልኩዎት ነው፡፡
- እሺ፡፡
- እና ይኸው የሦስት ወር እርጉዝ ናት፡፡
- ይኸው ነው?
- ኧረ ሌላም አለ፡፡
- ምንድን ነው ሌላው?
- የእኛን አትክልተኛ ያውቁታል አይደል?
- አዎን፡፡
- እሱ ደግሞ ይኸው ከአንደኛው ሾፌር ጋር ከተጣላ ሰነባበተ፡፡
- በምን?
- አትክልተኛው ውኃ ሲያጠጣ መኪናውን ረጨበት፡፡
- እ…
- እና በዛ ተነጋግረው ይኸው ተኮራርፈዋል፡፡
- ሌላ አለሽ?
- ይኸው ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለመሆኑ ባለፈው የሰጠሁሽን ሪፖርት ጽፈሽዋል?
- አይ አልጻፍኩትም፡፡
- ለምን?
- አሁን አደርሰዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የመጨረሻ ስብሰባችን ቃለ ጉባዔስ ተጽፏል?
- እሷ ቀላል ናት ብዬ አልጀመርኳትም፡፡
- ከዛሬ ጀምሮ መመርያ ይወጣል፡፡
- የምን መመርያ?
- ማንኛውም ሠራተኛ ጊዜውን በዚህ እንዳያጠፋ የሚል፡፡
- በምን ክቡር ሚኒስትር?
- በአርቲ ቡርቲ!
- ሄሎ!
- ሄሎ ጋሼ፡፡
- ማን ልበል?
- አላወቅከኝም ጋሼ?
- አላወቅኩም ማን ልበል?
- የወንድምህ ልጅ ነኝ፡፡
- እንዴ ከአሜሪካ?
- አዎን ጋሼ፡፡
- ከየት ተገኘህ ዛሬ?
- ባለፈው ስደውልልህ አላነሳህልኝም፡፡
- ስብሰባ ላይ ሆኜ ይሆናላ፡፡
- እንዴት ነህ ጋሼ?
- ሰላም ነኝ፤ አንተ እንዴት ነህ?
- ምን ይኸው ይኼ ሰውዬ ጤና ነስቶናል፡፡
- ማን ነው እሱ?
- ትራምፕ ነዋ፡፡
- ምን አደረገ?
- ሰሞኑን ዜና አልተመለከትክም እንዴ?
- ምን ስብሰባ ስለሚበዛብኝ ቤት ስገባ በጣም ይደክመኛል፡፡
- ዓለምን እያመሳት አይደል እንዴ?
- ምን አድርጎ?
- ይኸው እያባረረ እኮ ነው፡፡
- ሙሰኞችን ነው?
- የሰባት አገር ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ ብሏል፡፡
- ኢትዮጵያ አለችበት እንዴ?
- ምነው ልትመጣ ነው እንዴ?
- አንድ ስብሰባ እዛ አለኝ፡፡
- በቃ እኔ ልቀድምህ እችላለሁ፡፡
- ማለት?
- እኔ ቀድሜ ኢትዮጵያ ልመጣ እችላለሁ፡፡
- ከሰባቱ ውስጥ እኛ አለንበት?
- ጎረቤቶቻችን ነው ያሉበት ግን…
- ግን ምን?
- እኛም ልንካተት እንችላለን፡፡
- እና ምን እያልከኝ ነው?
- ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እፈልጋለሁ፡፡
- ለምን?
- መቼም በአገሪቷ ዕድገት ተደምሜ እንዳልሆነ ታውቃለህ፡፡
- እና እዚህ ምን ትሠራለህ?
- እሱን እንድንማከር እኮ ነው አደዋወሌ፡፡
- ታዲያ ምን ልርዳህ?
- ይኸውልህ ጋሼ ሐዋሳ አንድ መሬት አለኝ፡፡
- እሺ፡፡
- እሷን ልሽጣትና አዲስ አበባ አንድ መሬት ልግዛ፡፡
- ኦኬ፡፡
- ስለዚህ አንተ መሬቱን አዘጋጅ፡፡
- እ…
- ከዚያ አሪፍ ሕንፃ መሥራት ነው፡፡
- እሺ፡፡
- እና ከሚስትህ ጋር ፓርትነር ሆነን እንሠራለን፡፡
- ጥሩ ሐሳብ ይመስላል፡፡
- ከዚያ እያከራየን መኖር ነው፡፡
- ልንሰበስብ?
- ምን?
- ኪራይ!
- ሰሞኑን ምነው ጠፋህ?
- ስብሰባ በዝቶብኝ ነው፡፡
- አንድ ነገር ላማክርህ ስፈልግህ ነበር፡፡
- ምንድን ነው?
- ሰሞኑን አንድ ነጋዴ ጓደኛዬን አግኝቻት ነበር፡፡
- እሺ፡፡
- አንድ ሥራ እንድሠራ ነግራኛለች፡፡
- የምን ሥራ?
- ሥራው በጣም አትራፊ ነው ብላኛለች፡፡
- ምንድን ነው እሱ?
- ሰሞኑን ዱባይ ሴል ወጥቷል፡፡
- እሺ፡፡
- በቃ ዕቃ ጥንቡን ጥሏል፡፡
- ምን ዓይነት ዕቃ?
- ሁሉም ዓይነት፡፡
- እሺ፡፡
- በቃ ከዛ በኮንቴይነር አስጭነህ እዚህ መቸብቸብ ነው፡፡
- አይ አንቺ?
- ምነው?
- ሁሉ ነገር ለአንቺ ቀላል ነው አይደል?
- ምን ከባድ ነገር አለ ብለህ ነው?
- ገንዘቡ ከየት ይመጣል?
- ገንዘቡንማ ለእኔ ተይው ብላኛለች፡፡
- ገንዘቡ ቢገኝ ዶላሩ ከየት ይመጣል?
- አንድ የማይገባኝ ነገር አለ፡፡
- ምንድን ነው የማይገባሽ?
- በየጊዜው ከባንክ ፕሬዚዳንቶች ጋር እራት በላሁ ምናምን ትለኝ አይደል እንዴ?
- እ…
- ለዚህ ካልጠቀሙህ ከርስህን መሙላት ብቻ ምን ይጠቅማል፡፡
- አንቺ ሴትዮ፡፡
- ለማንኛውም አሁን የምሄድበት ቦታ አለ፣ በኋላ እናወራለን፡፡
- የት ልትሄጂ ነው?
- ለካ ይኼ ስብሰባ አለ፡፡
- የምን ስብሰባ?
- የመሪዎቹ ስብሰባ ነዋ፡፡
- እዛ ነው እንዴ የምትሄጂው?
- ኧረ መንገድ ይዘጋል ብዬ ነው፡፡
- እኔ ፓስ አሰጥሻለሁ፡፡
- ምን ዓይነት ፓስ?
- VIP የሚለውን ነዋ፡፡
- እኔ የምፈልገው ያኛውን ነው፡፡
- የትኛውን?
- VVIP!
- አንተ ልጅ መቼ ነው የምትሄደው?
- የት ዳዲ?
- አሜሪካ ነዋ፡፡
- ኧረ አልሄድም፡፡
- ለምን ሲባል?
- ይኼ ትራምፕ የሚባል ሰውዬ የሚሠራውን እያየህ?
- አንተ እኮ ልትማር ነው የምትሄደው?
- ቢሆንም ሪስክ መውሰድ አልፈልግም፡፡
- ታዲያ አውሮፓ ዩኒቨርሲቲ ይፈለግልህ?
- እዛም መሄድ አልፈልግም፡፡
- ቻይና ይሻልሃል ታዲያ?
- እኔ እኮ ካድሬ አይደለሁም፡፡
- ምን?
- ቻይና የሚላኩት ካድሬዎች አይደሉም እንዴ?
- እና እዚሁ ትማራለህ?
- ሥራ ብጀምር ይሻላል፡፡
- የምን ሥራ?
- አንተ ሚኒስትር ነህ አይደል ዳዲ?
- ብሆንስ?
- ለመንግሥት ቅርብ ሰው ነህ፡፡
- እሺ፡፡
- እንደምንም ብለህ ማሽን ግዛልኝ፡፡
- የምን ማሽን?
- የኮንስትራክሽን ማሽን፡፡
- እሺ፡፡
- ከዛ ማሽኔን የመንግሥት ፕሮጀክት ጋ ታስገባልኛለህ፡፡
- እ…
- ቀስ ብለህ ደግሞ በባንክ ብድር ተጨማሪ ማሽኖችን ትገዛልኛለህ፡፡
- እ…
- ከዛ እግሬን ሰቅዬ መብላት ነው፡፡
- ወይ ጉድ፡፡
- ምንም አታስብ ዳዲ፡፡
- ስማ መማር አለብህ፡፡
- ዳዲ የእኔ ፍላጎት ሌላ ነገር መሆን ነው፡፡
- ምን መሆን ነው?
- ልማታዊ ባለሀብት!
No comments:
Post a Comment