Friday, February 17, 2017

ህወሓት ኤርትራን ለማስቆረስ ለምን ጎመዠ? – ጋዜጠኛ ፍቃዱ በርታ




የዛሬ ሁለት ዓመት የካቲት 2007 ዓ/ም፣ አራት ኪሎ ከሚገኑት ካፉዎች በአንዱ  በቀጠሮ ከተገናኘን ከአንድ ወጃጄ ጋር ማኪያቶ ይዘን ወግ ጀምረናል፡፡የመገናኘታችን መንስሄ  የህወሐት 40ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ሰበብ ሆኖን፤ የድርጅቱን ታሪክ በሰፊው የሚዳስስ  ተከታታይ ጽሑፍ  በምሰራበት ፍቱን መጽሔት ላይ ለመሰራት በወጣነው ዕቅድ መሰረት፣ ከመሸጫ መደብሮች ያጠናቸውን ስለህወሓት የሚያወሱ መጽሐፍትን  ከወዳጆቻችንን እየተዋስን በማሰባሰብ ላይ ስለነበር ከዚህ ወዳጄ ጋር የተገናኘነው ያገኘልኝን መጽሐፍ ሊሰጠኝ ነበር ፡፡
በተጋጋለው የሃሳብ ልውውጣችን ጣልቃ፤የህወሓት 40ኛ ዓመት አስመልክቶ መቀሌ ላይ ሰለተካሔደው የአከባበር ስነስርአት ጉዳይ አንስተን ወግ ጀመርን፤‹‹ በመቀሌው ዝግጅት ላይ የሱዳኑ ፣የሶማሊያው፣የጅቡቲው፣የውጋንዳው፣የሩዋንዳው፤ ከምስራቅ አፍሪካ መሪዎች ማን የቀረ አለ? ሁሉም ተገኝተዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር፣የአውሮፓ ህብረት፣የቻይና እና የደቡብ ኮሪያ ተወካዮች ሁሉ ነበሩ፡፡ ሁኔታቸውን  ካስተዋልከው፣ እያከበሩ ያሉት የድርጅት ሳይሆን የሉዋላዊ አገር በዓል ነው የሚመስለው፡፡ሕዝቡንም በዙያ መልክ እያለማመዱት ነው፤›› አለኝ ወዳጄ በስጨት እያለ፡፡
‹‹ ይህ ሁሉ  ሽርጉድ ትግራይን የመገንጠል ዕቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ መንገድ መጀመራቸውን ለማሳየት  ይመስልሃል?›› አስከትዬ ጠየቅኩት፤
‹‹ አዝማሚያቸው እንደዚያ ነው፤››
‹‹ በስንት ዓመት ሊያሳኩት የሚችሉ ይመስልሃል?››
‹‹ በዚህ አካሔዳቸው ከቀጠሉ በ15 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚያሳኩት ይመስለኛል፤››
ያደቆነ ሰይጣን ሳያቄስ አይቀርም እንደሚባለው፤ የህወሓት የ40 ዓመታት  ትግራይን ከአገርዋ የመለየት ውጥን መሆኑ ነው፤ለመሆኑ ህወሓት እና እኛ እንዴት ለዚህ ተደራረስን?
በኤርትራ ተወላጁ ኢትዮጵያዊ ሀገር ወዳድ ምሑር በፕ/ር ተስፋፅዮን መድኀንዬ የተጻፈው ÇEritrea: Dynamics of a national questionÈ፤ የተሰኘ ባለ 346 ገጾች መጽሐፍ በ1979 ዓ.ም. ለንባብ በቃ፤ የመጽሐፉ ጠቅላላ መልዕክት ሽፋኑ ላይ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡አፈሙዙን  ቁልቁል ከዘቀዘቀው ክላሺንኮቭ  ጋር የተገጠመው ሳንጃ  ከፊል አካል  መሬቱን ሰርስሮ ገብቶ ከጎኑ ከበቀለ  አበባው ከፈካ ችግኝ ጋር ከገመድ ተያይዞ ይታያል፡፡መጽሐፉ ኢትዮጵያ  ከኤርትራ አማጺያን ጋር መካከል 27 ዓመታት ላስቆጠረው  የእርስ በእርስ ጦርነት ምክኒያት  የአገር ሀብት፣ ለቀጠፈው የሰው ልጅ  ሕይወት፣እንዲሁም  የአገር ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ  ለሚሳስባቸው ዜጎች እንደ ፕ/ር ተስፋፅዮን አይነቱን ለአአገር ተቆርቋሪ ዜጋ  ማግኘት እንደ ትልቅ  ፀጋ የሚቆጠር አጋጣሚ ነበር፡፡
ፕ/ር ተስፋፅዮን  በመጽሐፋቸው ከእርስ በርስ ጦርነቱ የደቀነቀውን አደጋ በጥልቀት ከመዳሰሳቸው በተጨማሪ የችግሩ ዘላቂ መፍትሔ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረግ አውዳሚ ጦርነት ሳይሆን  የኢትዮጵያ መንግስት እና ሻዕቢያ በጠረጴዛ ዙሪያ በሚያደርጉት ድርድር መሆኑን ያመላክታል፡፡እንደ ተስፋፅዮን እምነት ሻዕቢያ እያካሄደው የነበረው ጦርነት ኢምፔሪያሊስቶች ኢትዮጵያን ላማዳከም የጠነሰሱት ሴራ ውጤት መሆኑን ያስረግጣል፡፡ ከችግሩ መውጫ መንገድም ፣ ንጉሡ ኃይለ ስላሴ ያፈረሱትን እ.ኤ.አ. የ1953ቱ የኤርትራ ሕገ መንግሥት እና በ1952ቱ ኤርትራ በተመድ የጸደቀላትን የፌዴሬሽን መብት ወደቦታው በመመለስ  መሆኑን  ለከመንግስቱ ኃይለ ማሪያም መንግሥት ምክር ለግሰዋል፤ Ç… Ethiopian leaders should seriously consider ‘ Federation’ as the practical solution of Eritrean problem at the moment. They should reconsider their views on the nature and real purpose of Ethio-Eritrean ‘Federation’ effected in 1952È(p.292).
ለኤርትራ አማጽያን ወደ በረሃ  መትመም ሰበብ  ከተመድ ጋር የተገባው  የኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር የመቀላቀልቃ የስምምነት ውል ተጥሶ፤ የኃይል ውህደት በመፈጸሙ ምክኒያት የመጣ  መዘዝ ነበር፡፡ ምሑሩ ለቀድሞ ለኢትዮጵያ መንግስት  ያቀረቡት ፌዴሬሽኑ ተመልሶ ኤርትራም በኢትዮጵያ ትላ ስር ትኑር፣የኢትዮጵያ እንድነትም ከተደቀነበት አደጋ ይዳን፤የአገሩ አንድነትና ሰላም  ተጠብቆ መኖር ግድ ለሚለው ማንኛውም  ዜጋ ልብን በሲቃ የሚሞላ የምስራች ነበር፡፡
በወቅቱ ለፕ/ሩ አሳብ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በሻእቢያ በኩል የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ ይኑር አይኑር የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ፈጣን እና አስደንጋጭ ምላሽ ይዞ ብቅ ያለ ሌላ አካል ነበር፡፡
በንዴትና ቁጣ የተንጨረጨረው ጽሑፍ ተቃርኖ የሚጀምረው ገና ከሽፋኑ የተስፋ ፅዮንን መጽሐፍ ሽፋን ቁልቁል በመገልጥ  ነው፡፡ ርእሱምን  ብረት ህዝቢ ኤርትራ ቁልቁል አፉ አይድፋአን (የኤርትራ ሕዝብ ጠመንጃ አይዘቀዘቅም) የሚል ሲሆን፤የጽሑፉም ባለቤት የትግራዩ ነጻ አውጪ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡
አቶ መለስ በጽሑፋቸው ፣ የተስፋ ፅዮንን ኤርትራዊነት ጥርጣሬ ውስጥ ከማስገባት እና በመዘርጠጥ ሳይገቱ ፤ አንድ ሰው እውነተኛ ኤርትራዊ መሆን ከፈለገ ማሟላት አለበት  የሚሉትን ዝርዝር ህገ ደንብ እንደሚከተለው ይተነትናሉ፤ 1.የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው ብሎ  የሚያምን ፣ 2.የኤርትራ ጥያቄ ብቸኛ መፍትሔ ፌዴሬሽን ወይም ኮንፌዴሬሽን  ሳይሆን መገነጠከል ብቻ መሆኑን ፤3.የኤርትራ የመገንጠል ጥያቄ በመርህ ሳይሆን በገቢር ደረጃ እንዲከበር ተቀብሎ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መኖር በሚለው አሳብ ፈጥሞ የማይስማማ ፣4.ሙሉ ለሙሉ ካልሆነ በቀር የኤርትራ መሬት ወይም ጥቅም አሳልፎ በመስጠት ወይም ለኢትዮጵያ በመተው የሚደረግ (የሚመጣ ነጻነት)… የማያወግዝ …ወዘተ  (ከአገር በስተጃርባ ከገጽ 129-130) ከኤርትራ ከተወለዱ እናት እና አባት መገኘቱ ብቻውን ኤርትራዊት  ለመሆን ብቁ እንደማያደርጉት በድርሳነ መለስ ጽሑፋቸው ይደነግጋሉ፡፡እንደ ተስፋፅዮንም  እምነት የሻዕቢያ ጦርነት ኢምፔሪያሊስቶች ኢትዮጵያን ለማዳከም የጠነሰሱት ሴራ ከሆነ የኢትዮጵያ መዳከም እንደ ኢምፔሪያሊስቶቹ ጮቤ የሚያስረግጠው ሕወሐት የሚባል ድርጅት  እንዳለ አለመግለጻቸው ሳይጸጽታቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡
የህወሓት ለኤርትራ መገንጠል የነበረው እንደ እሳት የሚንቀለቀል ፍቅር ከመጠን ያለፈ እንደነበር ‹‹ በጸጸት››  የሚያስታውሱት ስለመሆኑ አንጋፋው ታጋይ አቶ ገብሩ አስራት እንዲህ ያቀምጡታል፤‹‹የኢትዮጵያን እንዲሁም የብሔሬን ጥቅም አስጠብቃለሁ ብሎ የቆመው ህወሓት ፣በኤርትራ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ፡ የሚጠቅማችሁ ነጻነት ነው ብሎ መከራከሩ ተገቢ እልነበረም፡፡ከራሳቸው ከኤርትራውያን አንድነት ይጠቅመናል የሚል ሐሳብ ሲሰነዘር፡እኛ ጭራሽ ስለአንድነት መወራት የለበትም ብለን፣ ያዙን ልቀቁን ማለታችን ፣ መለስ ብዬ ሳስበው ይጸጽተኛል›› (ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፣ከ98-101)፡፡ በእርግጥ የአቶ ገብሩ ጸጽት ከልብ ከሆነ ድርጅታቸው  ኤርትራን ለማስገንጠል  የፈለገበት ትክክለኛ ምክንያት  ምን እንደነበር ሊያጋሩን በተገባ ነበር፡፡
ሕወሓት  የኤርትራን ለማስገንጠል  ላሳደረው  መሰሪ ፍላጎት፤ የተስፋ ፅዮን መጽሐፍ በማብጠልጠል ብቻ አላበቃም፤ለምሳሌ በ 1979 ዓ/ም ድርጅቱ አቋሙን ባንጸባረቀበት ‹‹የኤርትራ ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት?;›› የተባለው መጽሐፍ የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት  በመሆኑ የኤርትራ ህዝብ ለነጻነት የሚያደርገው ትግል ትከክለኛ እና ፍትሐዊ መሆኑን በማስቀመጥ ፤እግረ መንገዱን ሻዕቢያ ከኤርትራ ነጻነት ውጭ ሌሎች አማራጮችን እንዳይፈልግ አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ተጠቅሞበታል፡፡ በሌላ በኩል  የ1981ዱ የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ወቅት፤ ሻእቢያ  ከኩዴታው አድራጊ ጀነራሎች ጋር ለድርድር በተቀመጠበት ሲቀመጥ፤ ኤርትራን ከማስገንጠል ውጪ ባሉት ሁኔታዎች እንደ ማንኝውም ኢትዮጵያዊ ድርጅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ  ስምምነት ላይ ደርሶ ለተግባሪነቱም  የገባውን የተኩስ አቁን ውል ተግባራዊ በማድረግ ለስምምነቱ የገባውን ግዴታ ተወጥቶ ነበር፡፡ ህወሓት በበኩሉ የጀራሎቹን የሰላም ስምምነት ጥሪ ውድቅ ከማድረጉም በተጨማሪ የሻዕቢያ  መስማማት የኤርትራን ሕዝብ የነጻነት ትግል ለሽያጭ ከማቅረብ ጋር አነጻጽሮ የውግዘት መግለጫ እስከ ማውጣት ደርሶ ነበር፡፡ (አባቴ ያቺን ሰዓት፤መጽሐፍ) ፡፡
የኤርትራ መገንጠል  ህወሓትን  ለምን  አስጎመጀው?
በመንግሥት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የታሪክ መምህር የሆኑት አቶ መስፍን ዳኛቸው (ስማቸው የተቀየረ)  ህወሓት ኤርትራን በተመለከተ ያራምድ የነበረው አቋም ሲያብራሩ፤‹‹ ህወሓት ለኤርትራ የተለየ ስስ ልብ ኖሮት አያውቅም፤ወይም የሻእቢያ ተላላመኪም ተንበርካኪም ሆኖ አይደለም፤ ይልቅስ ሚናውን የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ ሲያስመስል የነበረው ሆን ብሎ ለዘዴው ነው፡፡ወያኔ የኤርትራ መገንጠል ያስጎመዠው የነበረው፤ ከተደበቀችበት ጉድጓድ ውስጥ ብቅ ስትልለት ቀጨም ለማድረግ  በከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት አድፎጦ አይጥዋን እንደሚጠባበቅ የተራበ ድመት ነበር፤››
እንደ ታሪክ ተመራማሪው እምነት ፣ህወሓት  የኤርትራ  ሕዝብ ከሻእቢያ ከነጻነት ውጪ ምንም እንዳይቀበል በፕሮፖጋንዳ በማደንዘዝ፤ ሻእቢያን እጁን ጠምዝዞ ወዶም ይሁን በተጽእኖ ፣አውቆም ይሁን ሳያውቅ ህወሓት ባዘጋጀለት ወጥመድ ሰተት ብሎ ገብቶለታል፡፡አቶ መስፍን ለዚህ ሁሉ ምክኒያት ነው የሚሉትን ሲያስቀምጡ፤ ‹‹ ኤርትራና ኢሳያስ ያሉባት ኢትዮጵያ ለወያኔ ምቾት ይነሳዋል፤ ሻእቢያ እና ኢሳያስ አፎርቂ ያቀፈች ኢትዮጵያ ለወያኔ  ያፍነዋል፤ይጠበዋል፤ ጭንቅ ጥብብ ያስኘዋል፤›› ለምን ብትሉ፤‹‹ ኢሳያስና ኤርትራ  ካሉ  ኢትዮጵያ ለወያኔ የምታለብ ላም መሆን እንደማትችል ህወሓት አውቆታል፡፡ኤርትራን የተቀበለች ኢትዮጵያ የህወሓት መፈኝጫ ልትሆን እንደማትችል እነመለስ ዜናዊ አልጠፋቸውም፡፡ለዚህ ነው ለህወሓት እና ለመለስ የስልጣን ጥም ሲባል ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ  መሔድ የነበረባት፤››
የሕግና የፖለቲካ ምሑሩ አቶ ደረጄ አበበ (የሳቸውም ስም ተቀይሮዋል) በአቶ መስፍን ትንታኔ መስማማታቸውን ገልጸው፣እንደ እሳቸው እምነት የወያኔ አሻጥር ከዚያም በላይ አልፎ ይሄዳል፤‹‹ የሕወሓት አድርባይነትና ደባ በዚህ የሚበቃ አይደለም፡፡ እንደ ወያኔ ላለ መሰሪ ቡድን የስልጣን ጥም ችጋር ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዋላዊነትና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ መውደቅ ኢምንት ጉዳይ ነው፡፡እንደ ህወሓት ፍላጎት ኤርትራ ትሂድ እንጂ ካዚያ በኋላ የኢትዮጵያን ግዛት ተቆጣጥሮ ሥልጣንም ሃብትም ማካበት ቀላል ነው፡፡  ያም አልበቃ ብሎዋቸው፣ በሕገ መንግስቱ ውስጥ አንቀጽ 39ኝን ያስገቡት ለጌጥ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሰቀቀን እያባነኑ ለመግዛት፤ ሕዝቡ ከእንቅልፉ ነቅቶ ችግር የሚፈጥር ከሆነ  ፣ወይም ግራ ተጋብቶ ሲዘናጋ ወይም በቃን ብለው ሲያስቡ  ትግራይን ይዞ መሔድ ይቻላል ብለው ተማምነው ነው፡፡አሳዛኙ ነገር እነሱ የትግራይ ሪፐንሊክን መገንባት የሚያልሙት ቀሪውን አገር በማፍረስ መሆኑ ነው፤ ››
ከእንግዲህ የኤርትራ ሕዝብ ኢትዮጵያ ጋር መዋሃድ  ቢፈልግ እንኳን ህወሓት እያለ በቀላሉ ያሳካል ብለው አቶ ደረጄ  አያምኑም፤ይልቅስ፣ ‹‹ ሕወሓት በሥልጣን ማማ ላይ ላስቀመጣቸው እና የሕወሓትን ሥርወ-መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ኪሳራ እውን እንዲሆን ላደረገላቸው፣ ሽምጥ እየጋለቡት ለዚህ ላደረሳቸው የሥልጣን ፈረሳቸው ሻእቢያ ‹‹ዕድሜህን ያርዝመው›› ማለታቸው አይቀርም፤››
ከአራት ኪሎው ወዳጄና ከሁለቱ ምሑራን ጋር  ተገናኝተን ይህን ውይይት ካደረግን ሁለት ዓመት ሞላን፡፡ ከዚያ በኃላ ብዙ ነገሮች ተቀያይረዋል፤ ህወሓትም ኢትዮጵያም  የዛሬ ሁለት አመት  እንደነበሩት አይደሉም፤ሶስቱ ሰዎች፤የአራት ኪሎው ወዳጄና ሁለቱ ምሑራን ዛሬ በህወሓትና በአገራችን ላይ የሚኖራቸውይ  እሳቤ  ከያኔው የተለወጠ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክኒያቱም፣ ዛሬ ቢያንስ ቢያንስ  የህወሓት ጎረቤቶቹ ፣የቴዎድሮስ ልጆች ጎንደሬዎቹ ከህወሓት በስተደቡብ ሆነው እሳት ጨብጠው ቆመዋል…፡፡

No comments:

Post a Comment