Monday, February 13, 2017

ባንዶች፤ የዐማራ ተጋድሎ የጎበዝ አለቆችና የመስዋት በግ የሆነው ገበሬ

(ሙሉቀን ተስፋው)
ባንዳነት (ከጠላት ጋር ማበር) የተጀመረው በቀይ ባሕር አካባቢ በሚኖሩ ትግሬዎች ቢሆንም በጊዜና በመጠን እየተለያየ በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ነበረ፤ አለ፤ ወደፊትም ይኖራል። የማኅበረሰብ ተፈጥሮ ጥሬ ብስል ተጎራሰም ነው፤ ለሕዝብ የሚያስብ፣ ራሱን የሚወድ፣ ለገንዘብ የተገዛ፣ በጥቅም የማይደለል… ዓይነት ሰዎች በየትኛውም ሕዝብ ውስጥ አሉ።
ለምሳሌ የራስ አበበ አረጋይን እና ቤተሰቡን ታሪክ ማየት ይቻላል፤ ራስ አበበ አረጋይ ታላቅ ስመ ጥር አርበኛ ነበር፤ የሚያሳዝነው ግን አባቱ እልም ያለ ባንዳ ሆኖ ከልጁ ጋር በተለያየ ግንባር መሰለፉ ነው። የአንድ ቤተሰብ አባላት ውስጥ ባንዳና አርበኛ መፈጠራቸው ለዚያውም አባት ባንዳ ልጅ አርበኛ ሲሆኑ መመለክት እጅግ ይገርማል። ይህን ጉዳይ ያለ ነገር አላነሳሁትም።
የዐማራ የጎበዝ አለቆች ጋር ስንነጋገር ያደረሱኝ መረጃ እጅግ አስገርሞኛል። ለማስተማሪያነት ይሆናል ይፋ አድርገው ስላሉኝም ነው ይህን መጻፌ።
ምትኩ ገላው የተባለ ወጣት የዐማራ አርበኞችን ከወንድሙ ጋር ከተቀላቀለ ቆይቷል። በጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ‹‹ቤተሰብ ጋር ደርሼ መመለስ አለብኝ›› የሚል ሐሳብ ያነሳል፤ ፈቃድ ተከለከለ፤ አደጋ ይደርስብሃል ተባለ። ተማጽእኖው ቀላል አልነበረም። ይሁን ተባለና ሔደ።
የዐማራ ታጋዮች በነጋታው ጥር 27 ቀን በደባርቅ ወረዳ ቆላው አካባቢ ይሔዱ እንደነበር ያውቃል። ሆኖም ምትኩ ገላው ወንድሙን ጨምሮ ብዙ ጓደኞቹ የዐማራ ሕዝብን ስቃይ እንቅልፍ ነስቷቸው ከወያኔ ጋር መቆራረጣቸውን እያወቀ ‹‹ባንድነት›› ባሕሪው ይሆናል ብለው አላሳቡትም ነበር።
የጎበዝ አለቆች ሔዱ፤ አቶ ምትኩ በቀጣዩ ቀን 450 እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ የወያኔ ወታደሮችን ይዞ ከተፍ አለ፤ ፍጥነቱ ከብርሃንም ይልቃል። የዐማራ ታጋዮች ከነፍሳቸው ይልቅ በልጁ ባንዳነት ሐዘን እጅግ ተጎዱ። ግን አርበኝነት የዘራቸው ነው፤ ነፍጥ አተኳኮስ፤ ከበባን መስበር ብላቴ ወይም ጦላይ የጦር ትምህርት ቤት አልተማሩም፤ እድሜ ለአርማጭሆ ጫካዎች። ሙሉ በሙሉ መንገዶች ሁሉ ተዘግተዋል። በጀርባቸው ያለው ላጥ ያለ ገደል ብቻ ነው። ገደሉን ለመውረድ እንደ ሰሜን ጭላዳዎች ልምምድ ያስፈልጋል።
ጀግኖቹ ግን አንድም ሰው ሳይጎዳ ከበባውን ሰብረው ሔዱ። ባንዳው አፈረ፤ አረመኔዎቹ የወያኔ ወታደሮች አንድ በእርሻ ቦታ ላይ የነበረ ምንም ስለጉዳዩ ዕውቀት እንኳን የሌለውን ዐማራ ገበሬ በቀትር ተኩሰው ገደሉት። በሚያርሰው መሬት ትልም ላይ የምስኪኑ ገበሬ ደም ፈሰሰበት። ገበሬው የመስዋት በግ ሆነ።
ሌላም ጊዜ እንዲህ ያለ ባንዳ ገጥሟቸዋል። አቶ አሳየኸኝ ተቀባ ይባላል። በታኅሳስ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ከድቶ ገብቶ የወንድሞቻችን ሕይወት አስቀጥፏል። አቶ አሳየኸኝና አቶ ምትኩ አሁን ከወያኔዎች ጋር ናቸው፤ በባንዳነት የተገኘ ሀብትና ክብር የጠዋት ጤዛ እንደሆነ ደካማው አእምሯቸው ገና አልተገለጸለትም።
የዐማራ ሕዝብ ትግልማ ያለምንም ጥርጥር በቆራጥ ጀግኖቻችን ያሸንፋል!!

No comments:

Post a Comment