Friday, February 24, 2017

የትረምፕ የውጭ ፖሊሲ – ሰሎሞን አባተ (VOA)


 2  464  466
ሰሎሞን አባተ
ከሩሲያ ጋር አብረው ሊሠሩ የሚችሉባቸውን አካባቢዎች መፈለግ፤ በኢራንና በቻይና ላይ ኾምጠጥ ያለ አቋም በመያዝ ለእሥራኤል መሪ ለቤንጃንሚን ኔታንያሁ ጠንካራ ድጋፍ በመሥጠት በሃገራቸው የውጭ ፖሊሲ ላይ ለውጦችን እንደሚያመጡ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ቃል ሲገቡ ነበር፡፡
እነሆ የዘመቻ ወቅት አብቅቶ የምርጫ ውጤት ለይቶ “ፕሬዚዳንት ትረምፕ” እየተባሉ ሲጠሩ ልክ አንድ ወራቸውን ከትናንት በስተያ ደፈኑ፡፡
አሁን የትረምፕ አስተዳደር የዕይታውን ጥራት እንደገና እየፈተሸ፤ እንደገና እያነጣጠረና የዒላማውንም ምንነት እየለየ ነው፡፡
ቃል መኀላቸውን ከፈፀሙ በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ባደረጉት ንግግር ከእንግዲህ ወዲያ የሃገራቸው የውጭ ፖሊሲ የሚመራው በአንድ መርህ ብቻ መሆኑን አጠንክረው አውጀዋል፡፡
“ከዛሬ አንስቶ መመሪያችን አሜሪካ ትቅደም ብቻ ነው፤ አሜሪካ ትቅደም፡፡ በንግድ፣ በግብሮች፣ በኢሚግሬሽን፣ በውጭ ጉዳዮች በምንወስደው በያንዳንዱ ውሣኔ!” ብለዋል ትረምፕ፡፡
ፕሬዚዳንቱ በመጀመሪያው የሥራ ወራቸው ለአሥሮች ዓመታት ፀንተው በቆዩ የተለመዱ አሠራሮችና በዓለምአቀፍ ግንኙነቶች ላይ ለውጦችን ማድረግ ጀምረዋል፡፡
ትረምፕ በቅርቡ የእሥራዔልን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁን ዋይት ሃውስ ውስጥ ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ ይህ የሁለቱ መሪዎች ስብሰባና ውይይት በቀደሙት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን የሻከረውን የዩናይትድ ስቴትስ – እሥራዔል ግንኙነት መሻሻል አዲስ ዘመን ያሳያል ተብሏል፡፡
ትረምፕ ለመንበረ-ርዕሰ-ብሔር ዘአሜሪካ ይወዳደሩ በነበረ ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስን ኤምባሲ ከቴል አቪብ ወደ ኢየሩሣሌም እንደሚያዞሩ ቃል ሲገቡ ነበር፡፡ ኔታንያሁ በኃይል በተያዙ የዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ አካባቢዎች እያካሄደች ያለችውን የሠፈራ ግንባታም የመደገፍ አዝማሚያ ነበር የሚስተዋልባቸው፤ ቢያንስ ሲቃወሙት አልተሰሙም፡፡
አሁን ግን የያኔው ትረምፕ አይደሉም፡፡ አሁን ፕሬዚዳንት ትረምፕ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ትረምፕ ያንን በእሥራዔል የአሜሪካን ኤምባሲ አድራሻ የማዞር ሃሣባቸውን ዛሬ ቀዝቀዝ አድርገውታል፡፡ ኔታንያሁ ደግሞ ይህንን የሠፈራ ግንባታ የሚባል ነገራቸውን ገታ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የእሥራዔልና የፍልስጥዔምን ግጭቶች ለማስቆም ይረዳል ስትል ዩናይትድ ስቴትስ ለረዥም ጊዜ ይዛው ለቆየችው የሁለት መንግሥታት ምሥረታ መፍትኄም ትረምፕ ቀልባቸውን የሰጡ መስለዋል፡፡
“የሁለት መንግሥታት ምሥረታንም፤ የአንድ መንግሥት መፍትኄንም እያስተዋልኩ ነው፤ ሁለቱም ወገኖች የሚወድዱትን እኔም እወድደዋለሁ” ብለዋል ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጋር ሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፡፡
ኢራን ኒኩሌር የጦር መሣሪያ እንዳትሠራ ለማድረግ የሚዝቱት ትረምፕ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ በአንድ ወገን በቴሕራንና በሌላ ደግሞ በስድስቱ የዓለም ኃያላን መካከል የተፈረመውን ስምምነት አብዝተው ሲነቅፉ ይሰማሉ፡፡ “በዕውኑ መጥፎ ስምምነት” እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡
ኢራን በቅርቡ ላካሄደቻቸው የሚሳይል ሙከራዎች ትረምፕ አዳዲስ ማዕቀቦችን ጥለውባታል፡፡ “ኢራን ኒኩሌር የጦር መሣሪያ መቼም ቢሆን ጨርሶ እንዳትሠራ ለማድረግ ሌሎችም እርምጃዎችን እወስዳለሁ፡፡ ምቼም ቢሆን ኒኩሌር የጦር መሣሪያ እንዳትሠራ እያልኩ ነው” ብለዋል፡፡
ሌላው ትረምፕ የሚነሱበት ጉዳይ ሩሲያ ነች፡፡ ምንም እንኳ በሞስኮና በቴሕራን መካከል እጅግ የጠበቀ ግንኙነት እንዳለ ቢታወቅም፤ ምንም እንኳ ባለፈው የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ውስጥ እጆቿን ጣልቃ አስገብታለች ተብላ ብትከሰስም፤ ከሩሲያ ጋር እኮ የተሟሟቀ ግንኙነት ቢኖረን አይከፋም ባይ ናቸው፡፡ ይህንን ሃሣባቸውንም በተደጋጋሚ ሲገልፁ ይሰማሉ፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንታቸው ማይክ ፔንስ ግን ባለፈው ሣምንት ማብቂያ ላይ ይህ የትረምፕ ሃሣብ ለሚያሰጋቸው የአውሮፓ አጋሮቻቸው የፅናት ማረጋገጫዎችን አጠንክረው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
“በፕሬዚዳንት ትረምፕ አመራር ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያን በተጠያቂነት መያዟን የምትቀጥል ቢሆንም ፕሬዚዳንቱ በሚያምኑበት ሁኔታ በጋራ ልንሠራ የምንችልባቸውን አዳዲስ መንገዶችም እንፈልጋለን” ብለዋል ምክትል ፕሬዚዳንት ፔንስ፡፡
ቻይና የገንዘቧን የምንዛሪ አቅም እንዳሻት በማጠማዘዝ ታጭበረብራለች ሲሉ በምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት የሚያብጠለጥሏትን ቻይናን በበጎ እምብዛም ሲያነሱ ተሰምተው አይታወቁም ነበር፡፡ “በጨዋታ ሕግ ተመርተው አያውቁም፤ አሁን መጀመር ያለባቸው ጊዜ እንደሆነ አውቃለሁ” ብለዋል፡፡
ከቻይና በሚገቡ ሸቀጦች ላይ አዳዲስ ታሪፎችን እንደሚጭኑና ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ጋር ያሏትን የንግድ ፖሊሲዎች እንደሚለውጡ ሲዝቱ ተሰምተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንቱ የዋይት ሃውስ ሥራቸውን ከጀመሩ አንስቶ አስተዳደራቸው በእነዚያ ጉዳዮች ላይ ብዙም ሲናገር አይሰማም፡፡ ይልቅ ትኩረቱን ወደ አካባቢያዊ የፖለቲካ ትንቅንቆችና ንትርኮች አዙሯል፡፡
በአንድ በኩል በርግጥ ታይዋንን በሚመለከት ትረምፕ የቆየውን የአሜሪካ የ“አንድ
ቻይና” ፖሊሲ እንደሚደግፉና እንደሚያራምዱ አረጋግጠዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ቻይና በደቡብ ቻይና ባሕር ላይ አለኝ የምትለውን የግዛት ባለቤትነት ጉዳይ ዋሺንግተን ጥያቄ ውስጥ ማስገባቷን ቀጥላለች፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል የጦር ጄቶች ተሸካሚና አጥቂ ጓድ መደበኛ የውጊያ ልምምዱን እዚያው ደቡብ ቻይና ባሕር ውስጥ ሰሞኑን ጀምሯል፡፡
ይህ ልምምድ እየተካሄደ ያለው ቻይና በአካባቢው ላይ አለኝ በምትለው ሉዓላዊ ይዞታዋ ላይ ጣልቃ እንዳይገባባት እያስጠነቀቀች ባለችበት ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡
“በትረምፕ አስተዳደር ውስጥ በቻይና ላይ በተለይ የደቡብ ቻይና ባሕርን በሚመለከት ጠንከር የማለት ፍላጎት እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ይሁን እንጂ ግልፅ ፖሊሲ ስለመኖሩ ከመግለጫዎቹ በውል የሚታወቅ ነገር የለም” ብለዋል የስትራተጂያዊና የዓለምአቀፍ ጥናቶች ማዕከል ባልደረባዋ ቦኒ ግሌሰር፡፡
አዲሱ የትረምፕ አስተዳደር መሪው ላይ ከተቀመጠ እነሆ አንድ ወር ተጠቀቀ፡፡ ዶናልድ ትረምፕ የ“አሜሪካ ትቅደም” ፖሊሲያቸውን ምንነት ይበልጥ እያጠሩ በሄዱ መጠን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ባሏቸው ግንኑነቶች ላይ ይበልጥ የመመቻቸት አዝማሚያ እየያዙ የሚሄዱ ይመስላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment