Tuesday, February 21, 2017

ፕ/ር በየነ ምን እያሉ ነው ? ? ? ተስፋው የተንጠለጠለው ኢህአዴግ ላይ ነው


 

ፕ/ር በየነ ምን እያሉ ነው ? ? ?
ካለፉት የተለየና የተሻለ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ም/ ጠ/ሚ/ሩ ኢህአዴግን ወክለው በመክፈቻው ላይ መገኘታቸው ተስፋ እንዲሰንቁ መነሻ እንደሆናቸው ገልጸዋል፡፡
እኔ ፕሮፌሰሩ ተስፋ በመሰነቃቸው ችግር የለብኝም፡፡ ‹ በጎውን ማሰብ ከበጎ ያደርሳል › ከሚል ቀና አስተሳሰብ የመነጨ ነው ቢሉ የተሻለ ነበር፡፡ ግን ተስፋ እንዲሰንቁ ስላበቃቸው ያቀረቡት ምክንያት ፕሮፌሰሩ ምን እያሉን ነው የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡ ጥቂቶችን እንመልከት፡፡
ፕ/ር በየነ ከዚህ በፊት ‹አሁን ከነገሩን የተስፋ መነሻ›› በበለጡ መድረኮች ራሳቸው ተሳትፈዋል፣ በጭንቅ ጊዜ /በክፉ ቀን/ ህወኃት/ኢህአዴግ ስለተቃዋሚዎች ያላቸውን በጎ ነገሮች እና ጭንቁ/ ክፉው ቀን ሲያልፍ የሚሉትንና ያደረጉትን ያውቃሉ ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች ጋር በጠቅላይ ሚ/ር ደረጃ የተደረገውንና የሆነውን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እንመልከታቸው፡፡
1ኛ / በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጠ/ሚ/ሩ ስለቃውሞ ጎራው በአደባባይ የሰጡት ቃለ ውዳሴና እንዳበቃ ሲደረግ የነበረው፤
2ኛ/ በ1977 ምርጫ ወቅት በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት /ዲፕሎማቶች–አሜሪካ ቆንሲል እና አውሮፓ ኅብረት/ የወቅቱ ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ ቅንጅትና ኅብረት በጋራ የጠሩት የተቃውሞ እርምጃን ይሰርዙት እንጂ ‹ከሰማይ በታች ባለ በማንኛውም ጉዳይ እንነጋገራለን › ባሉበት ኅብረቱን ወክለው ተደራዳሪው እርሳቸው ነበሩ፤በድርድር በተገኘው ውጤት መሰረት ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ተቃውሞው መሰረዙን ‹ ያበሰሩን › አንዱ እርሳቸው ነበሩ፡፡ ከተቃውሞው መሰረዝ በኋላ የሆነውን ያውቃሉ፡፡
3ኛ/እርሳቸው የተሳተፉበት በተወካዮች ምክር ቤት አባል ፓርቲዎች መካከል የተደረጉ ድርድሮች፤ የተደረሰባቸው ስምምነቶችና ተግባራዊነታቸው፤
4ኛ/ የቀድሞው ሦስት ፓርቲዎች ጋር ያረቀቁት የሥነምግባር ደንብ (አዋጅ የሆነው) ከአርቃቂዎቹና ቀዳሚ ፈራሚዎቹ መኢአድ ከጋራ ምክር ቤት ለመውጣት የተገደደበት እውነታ፤
5ኛ/ በኢህአዴግ ፈቃድ ስለተቋቋመውና ‹መድረክ› የሥነ ምግባር ደንቡን አልፍምም በማለት ለማያሳተፍበት የ ‹‹ ፓርቲዎች የጋራ የፖለቲካ መድረክ›› የተለየ ውጤት ያለማምጣት ሲናገሩ እንደነበር፤ የማናውቃቸው የጓር ድርድሮች የመኖር ዕድል እንደተጠበቀ ሆኖ- ሁላችንም የምናውቀው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
በእነዚህ ሁሉ በውይይቱ የተደረሰባቸው ስምምነቶች፣ የተፈረሙ ውሎች … እና በተግባር የተፈጸመውን እያወቁ፣ አሁን ድርድር እየተደረገ ነው በሚባልበት ጊዜ የብዙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተለይ ደግሞ እርሳቸው ጠንካራ የሰላማዊ ታጋይ ስለመሆናቸው የሚመሰክሩላቸውን ምክትላቸውን አስረው ባሉበት እንደምን የም/ጠ/ሚሩ መገኘትን ከወትሮው የተለየ ተስፋ እንዳሰነቃቸው አልገባኝም ፡፡ የተስፋው መገለጫ ግራ አጋባኝ ፣ የአስተያየቱ ጊዜ ፈጠነብኝ፡፡
በተያያዘ ሌላ ጥያቄ የጫረብኝ ጉዳይ አለ፡፡ ስለድርድሩ ስድስት ፓርቲዎች በጋራ መግለጫ ሲሰጡ እርሳቸው የሚመሩት ‹መድረክ› ስለምን አብሮ እንዳልቆመ አለማስረዳታቸው ነው፡፡ ይህን ሳያስረዱ በተናጠል አቋም ይዞ በሚደረግ ‹ድርድር› እንዴት ተስፋ ይሰነቃል፤ አሁንም ተስፋው የተንጠለጠለው ኢህአዴግ ላይ ነው ማለት አይሆንም ትላላችሁ? ለዚህ ጥያቀዬ መነሻ የሆነኝን የተከበሩ አቶ ቡልቻ ከአራት ዓመት በፊት/ አዲስ ገጽ -ታህሳስ 2005/ የመድረክና አንድነትን ውዝግብ በሚመለከት ‹ ስለመድረክ › የተናገሩትን ልጥቀስ ፡፡ ‹‹ሳናፍር እውነቱን እንነጋገር ካልን ብቻችንን አጥቂዎቻችንን መመከት አልቻልንም፡፡ይህን ስል በፖለቲካ ሙግት፣ በገንዘብና ዓለምአቀፍ ደረጃ የፖለቲካ ድጋፍ ማግነትን አስመልክቶ እንጂ በጦር ኃይል ማለቴ አይደለም፡፡ ….የእርሰስ በርስ ጦርነት በፍልስፍናዬ የተወገዘ ነው፡፡ ›› ዛሬስ መድረክ አከዚያን ጊዜ የተሻለ የፖለቲካ ሙግት የማድረግ አቅም ላይ ነውን ? የሚለውን ሳስብ ብቸኝነቱ የተናጠል ጉዞው ቢያሳስበኝ ነው፡፡ ከዚህ ጋር መነሳት ያለበት ከ‹ቀለብተኞቹና የኢህአዴግ ስሪቶች ውጪ› ያሉት ወይም ነን የሚሉት የተቃውሞ ጎራው በኅብረት ያለመቆም ጉዳይ ነው፣ ቢያንስ ስለድርድሩ የጋራ አቋም ለመውሰድና በአንድ ድምጽ ለመደራደር እንደምን ወይም ለምን ተሳናቸው ?፡፡ ዛሬም እዚያው ናቸው ፣ ተነጣጥለው ውጤት ይጠብቃሉ ማለት ነው? ከጊዜ ጋር መልስ የሚያገኝ ቢሆንም እኔ ግን አይታየኝም፡፡ እየሆነ ያለው ነገር የተቃዋሚ ጎራው አመራሮችን በህዝብ ትዝብት ላይ የሚጥላቸው፣ የህዝብ ተኣማኒነትን አሳጥቶ እነርሱ የሰነቁትን ተስፋ ህዝብ እንዳይጋራና ከጎናቸው እንዳይቆም የሚያደርግ ነው፡፡
የመከራ ቀናችን እንዲያጥር፣ ዘላቂ መፍትሄ እንድንቀዳጅ፣ ማስተዋሉን ፣ በጎውን በልቡናችን ያሳድረው፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡ 13/06/09.

No comments:

Post a Comment