Monday, February 13, 2017

ዳንኤል ሺበሹ/አናኒያ ሶሪና ኤሊያስ ገብሩ ይናገራሉ (ስንታየሁ ቸኮል እንደዘገበው)




ፍጹም ድፍረት የሀገር ፍቅር የትግል ፍላጎት ተመልክቼ ተመለስኩ! የማይደክሙ የነጻነት እግሮች ወደ ቦሌ ክ/ከ/ ፖሊስ መምሪያ ዛሬም አቀናሁ። ምክንያቱ ደግሞ እንደተለመደው በሕግ አልበኝነት የእስር ቤት በር የተዘጋባቸው ጓደኞቼ ጋዜጠኛ አናኒያ ሶሪ -ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጓድ ዳንኤል ሺበሺ ለመጠየቅ ነበር፡፡ ቦታው ላይ ከደረስኩ ከጥቂት መጠበቅ በኃላ ተገናኘን የሞቀ ፈገግታ በሰላምታ ተለዋውጠን ስናበቃ በወቅታዊ ጉዳይ ትንሽ ማውጋት ጀመርን። ምንም የማይደክሙ አንደበቶች ያወራሉ። በአንባገነኖች እስር ቤት ውስጥም ሆነው ዛሬም እጃቸውን ኣጣምረው ድጋፋቸውን በኣደባባይ ይገልጻሉ ፡፡ እነዚህ ልበ ሙሉዎች ስለውጫዊ ትግል መጠናከር ኣጥብቀው ይመክራሉ፡፡
“ሁለት ኣመት በእስር ላይ ቆየሁ። መልሰው አሰሩኝ ለነጻነት የምከፍለው ዋጋ ነው” ይላል ዳንኤል ሺበሺ
ጋዜጠኛ ኣናኒያ ሶሪ- ከሞላ ጎደል እንዲህ አለ….
“አስቸካይ ጊዜ ኣዋጅ ጥቂት የስርዓቱ ተጠቃሚዎች ከወጀቡ ለመጠበቅ ሲባል ሀገሪቱን በወታደር የጥርነፋ እዝ ለማስገባት የታለመ እንጂ የሀገሬ ሕዝብ ከማንም በላይ ሰላም ወዳድ ነው፡፡ -ሕግ አውጪ ኣካል 100% በሞላው ም/ቤት ከሀገር አኳያ ሳይሆን ከህወሓት ድርጅታዊ ጥቅም ኣንጻር እየተመዘነ ሕግ ያወጣል። መልሶ የፍርድ ቤት ስልጣን ወስዶ ሽብርተኛ በማለት ራሱ ይወስናል፡፡ ሰሞኑን የኣሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሰባት አገር ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ያወጡት መመሪያ በፌዴራል ፍ/ቤት ውድቅ ተደረገ! በሌላ በኩል የኬንያ መንግስት የስደተኞች መጠለያ (ዳዳብ) ሊዘጋው ያሳለፈውን ውሳኔ የሀገሪቱ ፍርዱ ቤት ሰብዓዊነት የጎደለው ትህዛዝ አገደ፡፡ የሰው ልጅ በሚኖርበት ሀገር ማንም ከስርዓት በላይ እንደልቡ አይዘልም፡፡ በዚህ ሀገር አንድ ጀነራል ተነስቶ ሕግ ያወጣል።እኛም እንደምንታሰር እያወቅን የምንታገለው ለዚህ ነው፡፡ ”
ሌላው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ .. በእዚህ እስር ቤት ሆኜ የማስተላልፈው ቢኖር ” ይህ ትግል የአንድ አካባቢ ትግል አይደለም ” ይህ ትግል በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጀርባ የተደቀነ አደጋ ነው፡፡ ከሌሎችም ኣካባቢ የመጡ በርካታ ሰዎች እዚህ ታስረው ይገኛሉ። ሁለም የሚያስበው አንድ አይነት ቋንቋ ነው። ከዚህ ጨቋኝ ስርዓት መገላገል በእስር ያለው እንዲህ እያሰበ ሌላው በንትርክና አጉል ጭቅጭቅ ጊዜውን ሊያጠፋ አይገባም ወደፊት ማየት ብቻ ፡፡

No comments:

Post a Comment