Monday, February 13, 2017

ዲሞክራሲ ሰፍኗል ተብለናል፡፡ መሬት ወርደን እናረጋግጥ! ፍትህ ሰፍኗል ተብለናል፡፡ መሬት ወርደን እናረጋግጥ!

   


ዲሞክራሲ ሰፍኗል ተብለናል፡፡ መሬት ወርደን እናረጋግጥ! ፍትህ ሰፍኗል ተብለናል፡፡ መሬት ወርደን እናረጋግጥ! (Justice delayed Justice
denied የዘገየ ፍትህ እንደሌለ ይቆራል – ዕውነት ነው?)
የሕግ የበላይነት አለ ተብለናል፡፡ “ፍትህ የተዘጋጀ ዳቦ አይደለም” የሚለው አባባል ነው ተግባራዊ? ታች ወርደን እናረጋግጥ! ማንም የበላይ
የበታቹን እንዳሻው አይበድልም? እናጣራ!
“ዳሩ ዳኛ የለም ልተወው ግዴለም” እያልን አንዘልቀውም፡፡ ወርደን እንየው!
ትምህርት፤ በወላጅ፤ በመምህርና በተማሪ ሶስት – ማዕዘን (Triangular) ግንኙነት እያማረ ነው ተብለናል፡፡ እስቲ መሬት ወርደን እንየው፡፡
ጤና፤ በየጣቢያዎቹ ለህዝቡ በሚያመች ዘዴ ተሰልቶ ዝግጁ ሆኗል ተብለናል፡፡ መዳኒት አለ? የበቃ ህክምና አለ? ጤና ኬላ በቂ ነው? እስቲ
ጦጢት እንዳለችው፤ ይዋጥልን እንደሆን ወርደን እንየው! የመንገድ ሥራ ተሳክቶ ተጠናቋል፤ ተብለናል፡፡ ዘላቂ ናቸው አይደሉም? ወርደን
እናጣራ! አገራችን ሰላም ሆናለች፤ ተብለናል፡፡ ወደ ሰሜን፣ ወደ ምሥራቅ፣ ወደ ደቡብ ምዕራብ ወርደን እንታዘብ፡፡ መሬት የያዘውን አይለቅምና
ወርደን እንየው፡፡ በሀቅ እንዘግበው!
ሀብት፤ በፍትሐዊ መልክ ይከፋፈላል ተብለናል፡፡ እኩልነት ቤት – ደጁን ሞልቶታል ተብሏል፡፡ እስቲ ወርደን ኢወገናዊ መሬት መኖሩን አይተን
እንርካ! የትራፊክ አደጋ ቀንሷል እንባላለን፡፡ መሻሻል አለመሻሻሉን፣ ትራፊክ ሜዳው ላይ ወርደን እንየው! የመልካም አስተዳደር ችግር ነበር
ተብለናል፡፡ ዛሬስ? ወርደን ማየት ነው!
አገራችን የአሸባሪዎች ኮሪደር ናት ተብለናል፡፡ ዕውነት የሽብር ድልድይ ነን? ወርደን ማየት የአባት ነው! የአገራችን ፌደራሊዝም እና ክልላዊ
መስተዳድሮች አካሄድ የተቀናጀና የሰመረ ግንኙነት ያለው ነው ተብለናል፡፡ ወርደን እንየው! ባቄላ፣ በቆሎ ወይስ ተልባ? እናጣራ፡፡ እንናበባለን?
በፓርቲ አባላት መካከል ልባዊ መግባባት፣ ወቅታዊ መናበብ አለ? ተቃዋሚዎች ከአሉታዊ ፅንፍ ወጥተዋል ወይ? ወርደን እንየው!
መንግሥት በግል ሚዲያዎች ላይ ያለው ዕምነት ምን ይመስላል? ዛሬም “በሬ ወለደ ይላሉ” ነው? ዛሬም “የሌሎች አፍ ናቸው” ነው? ዛሬም
“ፀረ-መንግሥት” ናቸው ነው? ዛሬም መታሰራቸው ልክ ነው? ዛሬም የሚታኑና የማይታመኑ ሚዲያዎች አሉ? ወርደን እንያቸው!
በአገራችን ሙስና ጉዳይ የማንስማማበት ምክንያት ያለ አይመስልም፡፡ ይሰረቃል፡፡ ይዘረፋል፡፡ ችግሩ ግን የማይደፈሩ ሰራቂዎችና ዘራፊዎች አሉ
የሉም? ነው፡፡ ጥያቄው ግልፅ ነው!፡፡ ስለዚህ ወርደን እንየው!
ከሁሉም በላይ ደግሞ ከውጪ ያለውን አጋር ወይም ሐሳዊ ወዳጅ መንግስት የምናምነው ምን ያህል ነው? ሴትዮዋ ጓሮ ለሚጠብቃትና
እያስነጠሰ ምልክት ለሚሰጣት ውሽማዋ፣ የባሏን ቤት ውስጥ መኖር ለመንገር፣
“አንት የጓሮ ድመት፣ ምንም ብታነጥስ ዛሬ በዓል (ባል) ነውና፣ ቅጠልም አልበጥስ” እንዳለችው ያንን እየደጋገምን የምንጓዝበት ዲፕሎማሲ
ያስኬደናል ወይ?
ከገዛ ህዝባችን መግባባትና መስማማት እንጂ ከሌሎች በምናገኘው ገቢ (fund) ወይም ድጎማ መተማመን ብዙ አያራምደንም፡፡ የሚያዛልቀን
የህዝብ ሀብት ነው! መቼም ቢሆን ነባርም መፃኢም ህልውናችን የሚወሰነው በህዝባችን ፍቅር ነው!
“አገባሽ ያለ ላያገባሽ
ከባልሽ፣ ሆድ አትባባሽ”
የሚለውን ተረት ሳንታክት ማሰብ ለሀገር ልማትና ዕድገት መሰረት ይሆነናል! አንርሳው!

No comments:

Post a Comment