Monday, February 6, 2017

የጅቡቲ መንግሥት መጠናከርና የፍሪድ መዳከም



የኢትዮጵያውያን አድማ እየተካሄደ ባለበት በዚያ ወቅት በጅቡቲ መንግሥት በኩል አቅምን የማጠናከር ስራ እየተሰራ ነበር። እንደሚታወቀው የወቅቱ የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ጨምሮ አብዛኛወቹ ባለስልጣኖች የኢሳ ጎሳ አባላት ነበሩ። ኢሳወች ሶማሊኛ ተናጋሪ ሕዝቦች ናቸው። በዚህም ምክንያት ጅቡቲ ነጻነቷን ከመቀዳጀቷ በፊት ከሶማሊያ ጋር ለመቀላቀል ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል። በኬንያ፣ በኢትዮጵያና በጅቡቲ የሚኖሩትን ሶማሌወች የያዘች ታላቋን ሶማሊያ ለመፍጠር የተደረገው ሙከራ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ብርቱ ትግልና ጅቡቲ ነጻ ሀገር ሆና ዕውቅና በማግኘቷ ምክንያት ከሽፏል። ያም ሆኖ ሶማሊያውያን ጅቡቲን እንደሀገራቸው አካል አድርገው ስለሚያዩዋት በዚያ አካባቢ ለሚከሰት ማንኛውም ነገር ቀድመው ለመድረስ አያመነቱም።
የቀዝቃዛው ጦርነት እንዳበቃ የሶማሊያ ስትራቴጅካዊ ጠቃሚነት አከተመ። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ የኃያላን ድጋፍ ተነፈጋት። ይህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ መንግሥት ይደገፉ ለነበሩ የሶማሊያ አማጺያን ምቹ ሁኔታ ፈጠረ። በጥር 1983 ዓ.ም የዚያድባሬ (ሲያድ ባሬ) መንግሥት የአማጽያኑን ጥቃት መመከት አቅቶት ፕሬዚደንቱ ዋና ከተማዋን ለቀው ጌዲዮ ወደሚባለው የሀገሪቱ ደቡባዊ ክልል አፈገፈጉ። ትንፋሻቸውን አሰባስበው ከአዲሱ ቤዛቸው ተወርውረው በኃይል ተገፍተው የተነጠቁትን ስልጣናቸውን ለማስመለስ ሁለት ያህል ሙከራወችን ያደረጉ ቢሆንም ሙከራቸው በጀኔራል መሀመድ ፋራህ አይዲድ በሚመራው ኃይል ከሽፎ የጌዲዮን ሪጂን በአማጽያን ቁጥጥር ስር የመዋል ስጋት ሲያንዣብባት ወደ ኬንያ ሸሹ። የፕሬዚደንት ዚያድባሬን ሀገር ጥሎ መሸሽ ተከትሎ ሶማሊያ በፍጥነት ወደቀውስ ውስጥ ገባች። ሀገሪቱን በበላይነት የምመራው እኔ ነኝ በሚል በታጣቂወች መሀል ይደረግ የነበረው ሽኩቻ አድጐ ወደ ለየለት ጦርነት አመራ። ታጣቂወች በየጎሣወቻቸው በመደገፋቸው ጦርነቱ መልኩን ቀይሮ በጎሣወች መሀል የሚደረግ የእርስ በርስ ጦርነት ሆነ። ከሁሉም ወገን ጥቃት የተከፈተበት የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር የደርግ ሠራዊት ዕጣ ደርሶት ሁሉም እግሩ ወደየአመራው ተሰደደ። የተወሰኑት በየጎሳቸው የሚደገፉ አማጺ ቡድኖችን ተቀላቅለው የርስ በርስ ጦርነቱን አፋፋሙት።
ወደጅቡቲ ተሰደው የመጡት የቀድሞው የሶማሊያ ወታደሮች የጠበቃቸው መልካም አቀባበል ነበር። እናንተም እኛም ሶማሌወች ነን ተብለው እንደሀገሪቱ ዜጎች መብታቸው ተከብሮላቸው በሙያቸው እንዲያገለግሉ ሲጋበዙ ያለምንም ማመንታት ግብዣውን ተቀብለው የጅቡቲን ወታደራዊ ኃይል ተቀላቀሉ። ፍሪድ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ ነበር። በዚህ በኩል አሉ የሚባሉትን ከባድ መሣሪያወች የሚተኩሱትን ጨምሮ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በውጊያው ላለመሳተፍ አምጸዋል። በዚያ በኩል የመንግሥቱ ጦር ተሰደው በመጡ የሶማሊያ ወታደሮች እየተጠናከረ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያውያኑ አምስትና ስድስት እየሆኑ መጥፋት ጀመሩ።
የፍሪድ ሠራዊት መፈታት
ሻምበል የሱፍ ከግምባር ጠፍተው የተመለሱትን የሀገሩን ልጆች በአፋር ወታደሮች አሳዶ በመያዝ የለበሱትን አስወልቆ እንደገረፋቸው ተሰማ። በዚህ የተበሳጨው በሙልሁሌ ግምባር መሽጐ የነበረው ኢትዮጵያዊ ኃይል በሚተኩሱበት ላይ ለመተኮስ ቆርጦ ይዞታውን ለቆ ወደራንዳ ተንቀሳቀሰ። የአፋር ወታደሮች ከግምባር ላይ ብቻቸውን ለመቆየት ወይም ወደኋላ እየተመለሱ ባሉት በኢትዮጵያውያኑ ላይ ለመተኮስ ባለመፍቀድ የመሸጉበትን መሬት ለቀው ኢትዮጵያውያኑን ተከትለው አፈገፈጉ። ሁኔታውን በቅርበት ሲከታተል የነበረው የጅቡቲ ተዋጊ ኃይል በበኩሉ ይህን ክፍተት ተጠቅሞ በፍሪድ ወታደሮች ተይዞ የነበረውን አካባቢ በእጁ አስገባ። ኢትዮጵያውያኑ እየተጠባበቁ ወደኋላ መመለስ መቀጠላቸውን የተመለከቱት ሻምበሎችና የአፋር ባለስልጣኖች ለማረጋጋት ብዙ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ጊዜው ግን ረፍዶ ነበር። ኢትዮጵያውያኑ አቡሌራንዳን አልፈው ወደራንዳ የሚወስደውን መንገድ ሲይዙ የጅቡቲ ወታደሮች ከኋላ በቀረው የአፋር ተዋጊ ኃይል ላይ በከባድ መሣሪያ የተደገፈ ውጊያ ከፈቱ። የፍሪድ ተዋጊወች ለመከላከልና መልሶ ለማጥቃት ፍላጎቱ አልነበራቸውም። ሁሉም ማለት ይቻላል ከሚተኮስበት ጥይት ለማምለጥ ስርአት በሌለው መልኩ ተበታትኖ መሸሹን ቀጠለ። ራንዳ ይኖሩ የነበሩት የፍሪድ የበላይ ኃላፊወች ተበታትኖ እየሸሸ ያለውን ወታደር አግደው እንደገና ለማሰባሰብ ብርቱ ጥረት አድርገዋል። ይሁን እንጅ የወታደራዊ አዛዦችን ትዕዛዝ ለማክበር የፈለገ አልነበረም ማለት ይቻላል።
ከወደራንዳ የሚናፈሰው ወሬ የዶራን ኗሪ ክፉኛ ረብሾታል። የፍሪድ ተዋጊወች ተሸንፈው እየሸሹ እንደሆነ ሲወራ የሰሙ አንዳንድ ሰዎች ቀደም ብለው ጓዛቸውን ሸክፈው ወደኢትዮጵያ ሄደዋል። ቀሪው በጭንቀት የሚሆነውን እየጠበቀ ሳለ የጀብሀታና የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደዶራ መግባት ጀመሩ። በሁኔታው ተስፋ የቆረጠው አብዛኛው የዶራ ኗሪ መያዝ የቻለውን ይዞ ወደኢትዮጵያ መሸሽ ያዘ።የሚመጣውን ለመቀበል ቆርጠው እዚያው ዶራ የቀሩ ጥቂቶች ናቸው። በዚያች የወከባ ወቅት ዶራ የምንኖር ኢትዮጵያውያን መገናኘት ሳንችል ቀርተን ተጠፋፋን። ከግምባር የሚመጡትን የኢትዮጵያ ወታደሮች እንጠብቅ ወይስ ከሚሸሸው ጋር አብረን እንሽሽ በሚል ከባለቤቴና አብራን ከምትኖረዋ ሶፊያ ጋር እየተወያየን እያለን መቶ ዓለቃ መኮንን እና ጥቂት ኢትዮጵያዊያን BM የሚተኩሰውን መኪና ይዘው ከተፍ አሉ። ከኢትዮጵያውያኑ ጋር ሰላምታ ተሰጣጥተን ስናበቃ ሻንጣችንን በመኪናው ላይ ጭነን ወደቡያ ተጓዝን። ቡያ ስንደርስ የገበያ ቀን ይመስል ብዙ ሰው ከሜዳ ላይ ፈስሷል። እነመኮንን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ቀድመው የመጡት እኔና ባለቤቴን ቡያ ለማድረስ ስለነበር ቡያ እንደደረስን ተሰናብተውን ወደኋላ ተመለሱ።
ዐዕምሮየ መስራት ያቆመ ያህል ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅ ብየ ፈዝዥ ባለሁበት በዚያን ጊዜ የጀብሀታ ለአፋር ኃላፊው አይቶኝ ወደእኔ መጣ። ሰውየው አጭር ቀጭን ወደቀይነት ያደላ ራሰ-በራ ሰው ነው። ከሰውየው ጋር ሰላምታ ተሰጣጥተን ጥቂት አወራን። የውይይታችን ፍሬ ሀሳብ ኢትዮጵያውያኑን ወታደሮች አሰባስቤ ወደኢትዮጵያ የአፋር ክልል ገብተን ከእነርሱ ጋር በጋራ ስለመንቀሳቀስ ነበር። ሀሳቡን ያቀረበልኝ እርሱ ነው። ለችግሬ ፍቱን መፍትሄ ያገኘልኝ ያህል ደስ ብሎኝ አቅፌ ልስመው ምንም አልቀረኝም። ሥራየን ትቼ ከሀገሬ ተሰድጀ ለአንድ ዓመት ያህል በበረሀ የተቃጠልሁት ምንም ውጤት ለሌለው ነገር መሆኑ እጅግ ሲያበሳጨኝ የቆየ ጉዳይ ነው። አንድም የረባ ነገር ሳላደርግ ባለቤቴን ጭምር በዚያ በረሀ አሰቃይቸ ወደሀገሬ መመለስ ቀርቶ ማሰብ ብቻውን ማንም ሊረዳው ከሚችል በላይ የውስጥ ህመም ይፈጥርብኝ ነበር። ይህ ሰው ያቀረበልኝ ሀሳብ ቢያንስ ዓላማ ያለው ሥራ እንድሰራ፣ ሞቴም ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርግ ነው ብየ ስላመንሁ ያለማመንታት እሽ ብየ ተቀበልሁት።
አሁን አንድ ነገር ማድረግ ይኖርብኛል፤ ባለቤቴን አግባብቸ ከሶፊያ ጋር ወደማንዳ እንድትሄድ ማድረግ። ወደቤተሰቦቿ ተመልሳ የራሷን ኑሮ መኖር አለባት። ለአንድ ዓመት ያህል የከፈለችው መስዋዕትነት ለፍቅር የተከፈለ መስዋዕትነት ነው። ላደረገችልኝ ሁሉ ፈጣሪ አለሁሽ ይበላት። እኔ ከሀገሬ የወጣሁት ወያኔን ከሚፋለሙ ኃይሎች ጋር ተሰልፌ የዜግነት ድርሻየን ልወጣ ነው፤ ለሀገር ሉአላዊነትና ለሕዝብ አንድነት ጸር የሆነውን ወያኔን ተፋልሜ የክብር ሞት ልሞት ነው። እሷ ተከትላኝ በረሀ ድረስ የመጣችው ወያኔን በጦርነት አሸንፈን አዲስ ስርአት እንመሰርታለን ብላ አምና ሳይሆን ከእኔ ላለመለየት ስትል ብቻ ነበር። በቃ! ከእንግዲህ በኋላ በእኔ የተነሳ ምንም አይነት መከራ ልትቀበል አይገባም። “ማንዳ ከደረሰች በኋላ አማራጭ ስታጣ ወደቤተሰቦቿ ትመለሳለች” ስል አሰብሁ።
ችግሩ ግን ከእኔ ተለይታ ከሶፊያ ጋር እንድትሄድ ለማሳመን ምን ማድረግ አለብኝ የሚለው ነበር። አውጥቸ አውርጀ አንድ መፍትሄ ብልጭ አለልኝ።  መፍትሄ ይሆናል ያልሁትን ነገር ለባለቤቴ ስነግራት እንደፈራሁት በንዴት ትንጨረጨር ያዘች። እኔ በአካል እንድለያት ቀርቶ ስለመለየት እንኳ እንድታስብ አልፈለገችም። “እንድታሰር ትፈልጊያለሽ?” ስል ዐይን ዐይኗን እያየሁ ጠየቅኋት። “ዝም ብለህ ምክንያት አትፍጠር። ምን አደረግህና ነው የምትታሰር፣ ማንም አያስርህም” አለችኝ እምባ እየተናነቃት። “ይኸውልሽ – – -” አልሁ ለማስረዳት እየተመቻቸሁ። “- – – የፍሪድ ወታደር መበተኑን የኢትዮጵያ መንግሥት ያውቃል። ስለዚህ ወደኢትዮጵያ የሚገባውን ወታደር ለመቆጣጠር የድንበር ቁጥጥር ያደርጋል። እናንተ ሴቶች ስለሆናችሁ ማንም አይጠይቃችሁም። ቢጠይቋችሁ እንኳ ለስራ ፍለጋ ወደጅቡቲ እንደገባችሁ መናገር ትችላላችሁ። እኛን ግን እንዲህ በቀላሉ የሚለቁን አይሆንም። በቁጥጥር ስር አውለውን ማጣራት ከጀመሩ አለቀልኝ ማለት ነው። እናንተ ቀድማችሁ ሂዱና ማደሪያ አመቻቹ፤ እኔ ጨለማን ተገን አድርጌ ወደማታ አካባቢ ከወታደሮች ጋር እመጣለሁ። ማንዳ በጣም ትንሽ ከተማ ስለሆነች ፈልጌ አላጣችሁም” ብየ በብዙ ድካም እሽ እንድትለኝ አግባባኋት። ከዚያም ወደማንዳ የሚሄዱ ግመል የሚጭኑ አፋሮችን ፈልገን ለሻንጣ መጫኛ 60 ብር ከፍየ ከእነርሱ ጋር እንዲሄዱ አደረግሁ። የትምህርት ማስረጃየና ልብሶቼ ከሻንጣው ውስጥ ናቸው። ባለቤቴ ወደጅቡቲ በረሀ ስትመጣ ይዛ ከመጣችው ገንዘብ ውስጥ የተረፈውን 700 ብርም ሰጥቻታለሁ። ከእኔ ጋር የቀረ ነገር ቢኖር አሮጌ ፍሻሌ ሽጉጥ፣ የለበስሁት ልብስና የሰነቅሁት ተስፋ ብቻ ነበር።
የመከነ ተስፋ
ባለቤቴንና ሶፊያን ሸኝቸ ስመለስ የጀብሀታ ለአፋር (የቀይ ባሕር ዳርቻወች አፋር) መሪው እየጠበቀኝ አገኘሁት። ኃላፊው ከሚገለገልባት ነጭ ፒካፕ ቶዮታ ላይ ሦስት የጀብሀታ ወታደሮች ቦምብ ታጥቀው ጠበንጃቸውን ይዘው ተቀምጠዋል። አፋሮቹ በፍየል ሞራ የወዛ የተንዠረገገ ፍሪዝ ጸጉር ያላቸው ናቸው። ከሾፌሩ ኋላ ባሉት ወንበሮች ላይ እኔና ኃላፊው ጐን ለጐን ቁጭ ብለን መጓዝ እንደጀመርን ፍርሀት ቢጤ ተሰምቶኝ የሚያጠራጥር ነገር ቢከሰት ለመተኮስ ተዘጋጅቸ ቆቅ ሆኜ ተቀመጥሁ። ፍርሀቴ የመነጨው ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት የፍሪድ ትግል እንዲከሽፍ አስተዋጽዖ አድርገሀል ብለው ከመንገድ አስወርደው ሊረሽኑኝ ይችላሉ ከሚል ጥርጣሬ ነበር። ምን ላድርግ! አፋሮች እኮ የተለያዩ ናቸው ሲባሉ አንድ ሆነው የሚገኙ ናቸው። እንዲህ አይነቱ ጥርጣሬ የመጣብኝ እኒያን ከጀርባ ላይ የተጫኑ የአፋር ወታደሮችን አይቼ ስለነሱ ማሰብ ከጀመርሁ በኋላ ነበር። አንድ ጊዜ አቁሙልኝ ብየ ለመውረድ ፈልጌ የነበረ ቢሆንም መቁረጥ ግን አልቻልሁም። ዶራ ላይ ስንደርስ በጣም ብዙ ወታደሮችን አየን። ወደከተማው ሳንገባ ወደበልሆ የሚወስደውን መንገድ ይዘን ጉዟችንን ቀጠልን።
በልሆ የደረስነው አመሻሽ ላይ ነበር። ካደርንበት ቤት በስተደቡብ በኩል ከገደል ውስጥ የተጠራቀመ ውሀ አለ ብሎ ይዞኝ የሄደ ማን እንደሆነ አላስታውስም። ከውሀው ውስጥ ገብተን ቆሻሻችንን በቆሻሻ ውሀ ታጥበን ትንሽ ቀዝቀዝ ብለን ወደማረፊያችን ተመለስን። ያን ቀን እኔና የጀበሀታው አፋር ያደርነው ጎን ለጎን ነበር።
በልሆ ለሦስት ቀናት ያህል ቆይተናል። እዚያ በቆየሁባቸው ቀናት እዚያ የደረሱትን ኢትዮጵያውያን ለማሰባሰብ ብዙ ጥረት አድርጌአለሁ። ይሁን እንጅ ሊሰማኝ የፈለገ አንድም ሰው አልነበረም። ሁሉም የሚያስቡት ወደኢትዮጵያ እንደገቡ ጠበንጃቸውን ሸጠው የኮንትሮባንድ ንግድ ስለመነገድ ነበር። ተደራጅተን ወደኢትዮጵያ ገብተን ከአፋሮች ጋር ሆነን እንንቀሳቀስ የሚለውን ነገር የምናገርም፣ የራሴን ድምጽ መልሸ የምሰማውም እኔ ብቻ ነበርሁ። ለነገሩ አይፈረድባቸውም፣ በአላማ የተሰባሰቡ ስላልሆኑ።
እኒያ ሻምበሎች የት እንደገቡ ማወቅ አልቻልሁም፤ ከመቶ ዓለቃ መኮንን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተለያየነውም ቡያ አድርሰውኝ ስንሰነባበት ነበር። በአራተኛው ቀን BM ተኳሹ መኪና መጣ። በውስጡ ሾፌሩና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያቋረጠ ነው የተባለው ወጣት ብቻ ነበሩ። ያ ቀን የጅቡቲ መንግሥት ሠራዊት በልሆን ለመያዝ በላካሰል በኩል እየገሰገሰ ነው የሚል መረጃ ስለተሰማ ሁሉም ወደኢትዮጵያ ለመሸሽ እየተዘጋጀ ያለበት ቀን ነበር። አጋጣሚውን ተጠቅሜ ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ ጋር ለመጓዝ ከመኪናው ላይ ወጣሁ። ኢትዮጵያና ጅቡቲ ድንበር አካባቢ ስንደርስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥበቃ እያደረገ ነው የሚል ወሬ በመሰማቱ እንደገና ወደኋላ ተመልሰን ከመንገድ ወጣ ብሎ አልፎ አልፎ ቁጥቋጦ ከሚታይበት ረባዳ መሬት እረፍት አደረግን። ሙቀቱ አይጣል ነው። ከመኪናው ውስጥ መቀመጡ የባሰ ያስጨንቃል። የተቋጠረ ውሀ ብናገኝ ብለን አካባቢውን ስናስስ ከጎድጓዳ መሬት ላይ መልኩን የቀየረ ውሀ አገኘን። መልኩን መቀየር ብቻ ሳይሆን ጥሩ ያልሆነ ሽታም ነበረው። የቻልነውን ያህል ጠጥተን ልብሳችንን አውልቀን ተለቃልቀንበት ትንሽ ቀዝቀዝ አልን። ችግሩ ግን ከውሀው ወጥተን ብዙ ሳንቆይ እንደገና በውሀ መነከር መፈለጋችን ነው።
መኪናው ወደቆመበት ስንመለስ የሆኑ ሰዎች ከሾፌሩ ጋር ቆመው አየን። ዐይኔን ማመን አቃተኝ። ሦስቱ አፋሮች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ የእኔዋ ባለቤትና ሶፊያ ነበሩ። ባለቤቴ እንዳየችኝ እየሮጠች መጥታ ተጠምጥማ ይዛኝ እዬዬ ማለት ያዘች። “ተይው አታልቅሽ!” ብሎ አባብሎ ለማረጋጋት ቀላል አልነበረም። በባለቤቴ ሁኔታ የተደናገጡትና ያዘኑት አፋሮች “ከእንግዲህ በኋላ እዚህ መቆየቱ አይጠቅምህም። አብረሀት ወደሀገርህ ብትመለስ ነው የሚሻለው። ከመኪናው ውስጥ ግቡና እናድርሳችሁ” አሉኝ። አብረውኝ የነበሩት ሁለቱ ኢትዮጵያውያንም “እባክህ ሂድ፣ አታስለቅሳት! ከእንግዲህ በኋላ እዚህ ቆይተህ የምትለውጠው ምንም ነገር የለም” ብለው ገፋፉኝ። ለነገሩ ራሴን ለጉዳት ከማጋለጥ በስተቀር የምለውጠው ምንም ነገር እንደሌለ እኔም ብሆን ቀደም ብየ ተረድቸ ነበር። ባለቤቴ ወደኢትዮጵያ አብሬያት ለመመለስ መስማማቴን ነግሪያት እንኳ “እሪ!” ማለቷን ልታቆም አልቻለችም። ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን ጋር ተቃቅፈን ከተሰነባበትን በኋላ ከአፋሮች መኪና ስገባ ልቅሶዋን አቁማ እምባዋን ትጠራርግ ያዘች።
ወደሀገር ቤት መልስና ፍጻሜው
ወደጅቡቲ የመጣሁት ከአንድ አመት በፊት በ1984 ዓ.ም በሐምሌ ወር የመጀመሪያወቹ ቀናት ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ በ1985 ዓ.ም በሐምሌ ወር የመጀመሪያወቹ ቀናት ደግሞ አብረውኝ የነበሩትን ሁለቱን ኢትዮጵያውያን ተሰናብቸ አፋሮች በያዟት መኪና ከባለቤቴና ከአሊ በረጎይታ አስጥየ አብራን ከኖረችው ሶፍያ ጋር ተሳፍረን ወደኢትዮጵያ ተጓዝን። ከኤሊዳር ወደ አሰብ ከሚወስደው ዋና ጎዳና ላይ ስንደርስ አብረውን የነበሩት አፋሮች “በሉ ኤሊዳር ቅርብ ስለሆነ ወደዚያ ሂዱ” ብለው ከመኪናው አውርደውን አመስግነንና ተሰናብተናቸው እነርሱ ወደማንዳ ሲያቀኑ እኛ ግራችንን ይዘን ወደኤሊዳር አመራን።
በመንገድ ላይ እያለን ከእኔ ጋር ቡያ ላይ ከተለያየን በኋላ ስለሆነው ነገር አጫወቱኝ። ማንዳ እንደደረሱ ዶራ ከሚያውቋት አፋር ቤት ለማረፍ ሄደው ኖሯል። አፋሯን እኔም በአካል አውቃታለሁ፣ ያለከለከች ወፍራም ሆና ጠይም ናት። ሴትዮዋ ከቤቷ ሊያርፉ የሄዱትን ሰዎች ማየት የማትፈልግ ክፉ ሆና ነበር ያገኟት። የሚሄዱበት የቸገራቸው የዶራ ሰዎች እናውቃታለን ብለው ለአንድ ቀን እንድታስጠጋቸው ቢጠይቋት አውሬ ሆናባቸው ነበር። እንዲህ ያለ ነገር ከአፋር ባህል ያፈነገጠ ነው። እንደምንም ተለማምጠው ለአንድ ቀን አዳር ከተፈቀደላቸው ሰዎች መሀል ባለቤቴና ሶፍያ ነበሩበት። በበነጋታው ከጅቡቲ የሚመጡትን ሰዎች እየፈለጉ ስለእኔ ማጠያየቅ ይይዛሉ። ከመሀል አንድ እኔን የሚያውቅ ሰው ከአፋሮች ጋር በመኪና ወደበልሆ እንደሄድሁ ይነግራቸዋል። ይሁን እንጅ ባለቤቴ የሰማችውን ማመን አቅቷት እኔን ይመጣል ብላ እስከበነጋታው አመሻሽ ድረስ ጠብቃ ሳልመጣ ስቀር ሶፊያ ከምታውቃቸው ኤሊዳር ከሚኖሩ ሰዎች ቤት ዕቃቸውን ለማስቀመጥ ወደዚያው አመሩ። ከሶፊያ ዘመዶች ጋር አንድ ቀን አድረው በበነጋታው እኔን ፍለጋ በእግር ወደበልሆ መጓዝ ጀመሩ። የያዙት ነገር ቢኖር ብስኩት ነበር። በመንገድ ከሚያገኟቸው አፋሮች የሚጠጣ ውሀ እየለመኑ ብዙ ከተጓዙ በኋላ ቀኑ ሲመሽ ከመንገድ ወጣ ብለው ከሜዳው ላይ ተኝተው አድረዋል። በበነጋታው ጠዋት ተነስተው መንገዳቸውን ሲቀጥሉ ባለመኪናወቹ አፋሮች ያገኟቸዋል። ከአፋሮች መሀል አንዱ የእኔን ባለቤት ለይቶ አውቋት ስለነበር አብዱልቃድር ባራ “የአብዱልቃድር ሚስት” ብሎ ተጣርቶ እኔ ካለሁበት ድረስ ይዟቸው መጣ።
ኤሊዳር የሚኖሩት የሶፍያ ዘመድ በአካባቢው የሚታወቁት ሁሴን ጋላው በሚል መጠሪያ ነው። አቶ ሁሴንና ባለቤታቸው በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ጠብ እርግፍ ብለው አስተናግደውናል። መልካም ማድረግ መጀመሪያ ለራስ ህሊና ቀጥሎ ደግሞ መልካም ለተደረገለት ሰው ይጠቅማል፤ በቸገረ ጊዜም ውለታ ውሎልኛል የሚል ሰው ሊደርስልን ይችላል። ሶፊያ ‘ውለታችሁ አለብኝ’ በሚል ሚስቴን ተከትላ እኔን ፍለጋ፣ ያለመሪ፣ በዚያ በረሀ ተንከራተተች። እነርሱ ባይደርሱልኝ ኖሮ በምንተፍረት ምን አይነት የሞኝ ውሳኔ ልወስን እንደምችል እግዜር ይወቅ! ከአስተናገጆቻችን ጋር ለስንት ያህል ቀናት እንደቆየን ትዝ አይለኝም። ራሴን እንደሽፍታ ቆጥሬ፣ የእኔን እዚያ መኖር የመንግሥት ደህንነቶች ካወቁ ሊይዙኝ ይችላሉ ብየ እሰጋ ስለነበር ወደከተማ ለመውጣት ድፍረቱ አልነበረኝም።
ወደመሀል ሀገር ስንጓዝ በመንገድ ላይ ፍተሻ ሊኖር ስለሚችል ሽጉጥ መያዜ ጥሩ አይሆንም። ባለቤቴ ወደማንዳ ሄዳ ዶራ በምታውቃቸው ሰዎች ድጋፍ መሸጥ እንደምትችል ስትነግረኝ ይሁን ብየ ተስማማሁ። በዚች ዓለም ላይ የማምነው እሷን ብቻ ነው። አሜሪካኖች ለያንዳንዱ ሰው ጠባቂ መልአክ አለው ብለው እንደሚያምኑ የት ላይ እንደሆነ ባላውቅም ተጽፎ አንብቤአለሁ ወይም ሲወራ ሰምቻለሁ። እግዚአብሄር የሰጠኝ የእኔ ጠባቂ መልአክ ባለቤቴ ሳትሆን አትቀርም። ብዙ ጊዜ ላደርጋቸው ታግየ ያልቻልኋቸው ነገሮች በእርሷ አማካኝነት ተሳክተውልኝ ያውቃሉ። ትቀየመኛለች ወይም ትጣላኛለች ሳልል ያሻኝን ተናግሬ የፈለገኝን ነገር አድርጌ ነው የኖርሁት። እርሷም ብትሆን በእኔ ላይ ቅሬታ ይዛ መዋል ማደር አይሆንላትም። እኔ አጥፍቸም ቢሆን ሰላም ለመፍጠር ስትል ብቻ እሷ ይቅርታ ትጠይቀኛለች። ከእኔ የምትደብቀው ምንም ነገር የላትም። እርሷ አብራኝ ስትሆን ሞገስ አገኛለሁ፤ ጎደሎየ ሁሉ ይሞላል። እናቴ ሳትቀር ባለቤቴ ከጎኔ መኖሯን ስትሰማ ሰላም ታገኛለች። የባለቤቴና የእናቴ ግንኙነት የአማትና የምራት ሳይሆን የጥሩ እናትና የጥሩ ልጅ ነው። ባለቤቴ እናቴን “እማማ” ብላ አንቱ እንድትላት ያደረግሁት እኔ ነኝ። እና አንዳንድ ቀን ብልጭ ሲልባት “እማማን አንቱ እንድል ያደረግኸኝ አንተ ነህ። ከዚህ በኋላ ተመልሸ አንች ለማለት ይከብዳል። አንቱ ስላቸው ያራቅኋቸው ስለሚመስለኝ ደስታ አይሰጠኝም” ትለኛለች። ስለባለቤቴ የተናገርሁት ውሸት ይመስላል አይደል? ግን ዕውነት ነው፤ የቀነስሁት ቢኖር እንጅ የጨመርሁት ሀባ ነገር የለም። በስምምነታችን መሰረት ወደማንዳ ሄዳ ሽጉጡን በ500 ብር ሸጣው ተመለሰች።
በመጨረሻ ወደአዲስ አበባ የሚሄድ የጭነት መኪና ተገኝቶልን ሶፊያንና አስተናጋጆቻችንን በፍቅር ተሰነባበትን። አዳይቱ ከምትባል ከተማ ሻይ ቡና ብለን አዳራችንን አዋሽ አርባ አደረግን። በበነጋታው ጠዋት ተነስተን ቀሪውን የአዲስ አበባ መንገድ ጀመርን። እንደጠረጠርነው አዋሽ አርባ፣ አዋሽ፣ ናዝሬትና ቃሊቲ ላይ ፍተሻው አይጣል የሚያሰኝ ነበር። ወለንጭቲ ስንደርስ የተሻገርናት ትንሽዬ ወንዝ ከቀናት በፊት ጢብ ብላ ሞልታ ብዙ ጥፋት እንዳጠፋች ሾፌሩ ሲያጫውተን ብዙም አልገረመኝም። ቢያንስ ዶራ እያለሁ ህይወት የሌለው በጎርፍ የተፈጠረ ወንዝ መኪና እንደገለበጠ አይቻለሁ። ትንሽ አይናቅም፤ ትልቅም አይፈራም።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቶ ዓሊ መኪ በኢትዮጵያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው ለጅቡቲ መንግሥት ተላልፈው እንደተሰጡ ተወራ። ቆይቶ ደግሞ በሞሀመድ አዶይታ የሚመራ ከፍሪድ የተገነጠለ አንጃ ከመንግሥት ጋር ስምምነት አድርጎ ሁለት የሚኒስትርነት ቦታወችን እንደተቀበለ ሰማሁ። የእኔ ህልምና የጅቡቲ አፋሮች ትግልም በዚህ መልኩ ተቋጨ።
ተፈጸመ

No comments:

Post a Comment