Wednesday, February 22, 2017

ሰላም፡ አንድነት፡ ተስፋ (ሰማያዊ) በግሬስ አባተ

   


thsmown0lm

ሰማያዊን አስመልክቶ ፓርቲው እንደፈረሰ እንዲሁም አዲሶቹ ተመራጮች ላይ በተለይም አዲሱን ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ላይ አሮጌው ፍረጃ እየወረደ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተቃውሞ ጎራው ጉዳይ ላይ ደጋግሜ እንዳልኩት ፈረጃ ስልጡኑን ቁጭ ብሎ የመነጋገር እድልን የሚዘጋ አሮጌ መንገድ ነው፡፡ ይህም የተቃውሞ ጎራውን አንካሳ ሲያረግ የኖረ ነው፡፡ ላንዳንዶች ፓርቲ የግለሰቦች ንብረት ይመስላቸዋል፡፡ ለዚህ ነው ግለሰቦቹ ሲሄዱ የሚፈርስ እነሱ እስካሉ የሚቆም የሚመስላቸው፡፡ ለምሳሌ ኢ/ር ይልቃል የነበረውን ችግር ለመፍታት እድሉ በእጁ ነበር፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተሳትፎ መሟገት ይችል ነበር፡፡ በእጁ የነበሩትን መድረኮች ከመጠቀም ይልቅ ዳር ዳር ሲል ቆይቶ በመጨረሻ አማራጭ ያደረገው አሮጌውን መንገድ ነው፡፡ በግለሰቡ ፍቅር የወደቁ ተከታዮቹም ከዛ የተሻለ ነገር ማድረግ አልቻሉም፡፡

በጣም የሚገርመው በማንኛውም ተቋማት ውስጥ በመሪነት ላይ ያሉ ሰዎች ጥሩ ነገር ሲሰራ መመስገናቸው ያለ በተቃራኒው ሲሆን ደግሞ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ ያለ ቢሆንም በኢትዮጵያ የተቃውሞ ጎራ ውስጥ ግን ለሚሰሩ ስህተቶች ሌሎችን ‹‹ወያኔ›› ማለት እራስን ከስህተት ነፃ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህን ሳይመረምሩ አሁንም ላለፉት ሁለት አስርታት በተሄደበት መንገድ ለመሄድ መጣደፍ ሌሎች ሁለት አስርታትን ቁጭ ብሎ ከመቁጠር የዘለለ ነገር አያመጣም፡፡ ለግለሰቦች ከማልቀስ በዘለለ ፓርቲዎች የለውጥ እንቅስቃሴውን መሸከም የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ ከማገዝ ይልቅ የሥነ-ሥርዓት ኮሚቴው ላይ እንደሆነው የበላይ አመራሮችን የመጠየቅ አቅም መፍጠሩ ከማስመስገን ይልቅ የአሮጌው ፖለቲካ ሰለባ ነው ያደረገው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ተቋማዊ ቅርፅ ያለው የለውጥ ሀይል እንደሚፈጠር ግራ ያጋባል፡፡

ሌላው አንድነት ላይ የሆነውን በማንሳት የሰማያዊም ተመሳሳይ እንደሆነ ለመግለፅ የሚሞከረው ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት እራስን ከስህተት ነፃ ለማድረግ እንዲሁም ካፈርኩ አይመልሰኝ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ አንድነት ውስጥ ከተፈጠረው ችግር ጀምሮ አባላት ከፅህፈት ቤታቸው በፖሊስ ሃይል እንዲወጡ ተደርጎ ለአቶ ትዕግስቱ አይነት መካሪ አልባ ሰው ፓርቲው እስኪሰጥ አብሮት የነበረው ከፍ ካለው የፓርቲው መዋቅር አንድ ግለሰብ ብቻ ነው፤ አባል የነበሩት በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ ሌሎች ከየት እንደመጡ እንኳን አይታወቅም፡፡ በሰማያዊ ውስጥ በብቸኝነት በሚመስል መልኩ አቶ የሺዋስ ላይ ፍረጃ የሚያካሂዱት እንደ አቶ ትዕግስቱ ከምርጫ ቦርድ ሰማያዊን በችሮታ ያገኘ ለማስመሰል ነው፡፡ ለዚህ ነው በጠቅላላ ጉባኤ ስለተሳተፉ ግለሰቦች፣ስለብሔራዊ ምክር ቤት አባላት፣እንዲሁም አሁን ስላሉት ስራ አስፈፃሚ አባላት ትንፍሽ ሲሉ የማይሰማው፡፡ ይህ የአሮጌው ፖለቲካ ሌላው ምሳሌ ነው፡፡

ከላይ እንዳልኩት ይህ አሮጌ ፖለቲካ ውዥንብር በመፍጠሩ ሰማያዊን አንካሳ ሊያደረግ እንደሚሞክር ግልፅ ነው፡፡ አሁን ያለው አመራር ለዚህ ጆሮ ሳይሰጥ ቆፍጠን ብሎ ጥሩ የሚባሉትን በማጎልበት ያለፉትን ህፀፆች በመመርመር ለምሳሌ በውስጠ ዲሞክራሲ እና በተቋማዊነት ላይ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ባጠቃላይ የተቃውሞ ፖለቲካውን የአሮጌው ፖለቲካ መፈንጫ ከመሆን ለመታደግ መስራት የሁሉም የለውጥ ሀይል ድርሻ ነው፡

No comments:

Post a Comment