Monday, February 13, 2017

የሪፖርተርን ርእስ አንቀጽ ወድጄዋለሁ #ግርማ_ካሳ


   

edi1752
በተቃዋሚዎችና በአገዛዙ መካከል ይደረጋል በተባለው ድርድር ዙሪያ ሪፖርተር ጋዜጣ ግሩም ርእስ አንቀጽ አውጥቷል። ይሄን ርእስ አቀንጽ እኔ ልጽፈው የምችለው ሙሉ ለሙሉ የምጋራው ርእስ አንቀጽ ነው።
“ውይይትም ሆነ ድርድር ለማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ወገኖች ያለፉትን ቂምና ቁርሾዎች ወደ ጎን በማድረግና ለአገርና ለሕዝብ ምንም ጥቅም እንደሌላቸው ከልብ በማመን፣ አዲሱን ጉዞ በሠለጠነ መንገድ ላይ ቢጀምሩ ጥቅሙ ለአገር ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ ሁሉም የአገሪቱ ፓርቲዎች በእኩልነትና በነፃነት እንዲፎካከሩ ማድረግ የወቅቱ ዓቢይ ጥያቄ ነው፡፡ ከፖለቲካ ፍጆታነት የማይዘሉ አጓጉል ድርጊቶችን በማስወገድ የዜጎችን አንገት ሲያስደፋ የኖረውን አስከፊ የፖለቲካ ባህል መለወጥ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ድርድሩም ሆነ ውይይቱ በቀና መንፈስ እንዲጀመር ሲፈለግ በቅድመ ሁኔታዎች እያመካኙ ምክንያት መደርደር ሊቆም ይገባል፡፡ ድርድሩም ሆነ ውይይቱ ለሰጥቶ መቀበል መርህ ክፍት ከሆነ ቀዳሚው ጉዳይ የአገርና የሕዝብ ጥቅም ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁጠርኛ መሆን ግዴታ ነው፡፡”
ይላል ሪፖርተር በረስ አንቀጹ።
በሪፖርተር ላይ የሰፈሩትን ጠቃሚ ሐሳቦች ማንም አገሩን የሚወድ የቀና አስተሳሰብ ያለው ሰው በሙሉ የሚደግፈው ነው የሚል እምነት ነው ያለኝ። ሆኖም ግን አንድ በትልቁ ሊሰመርበት የሚገባ ነገር አለ። እርሱም ይሄ በሪፖርተር እንዲኖር የተፈለገው መንፈስ እንዳይኖር እንቅፋት የሆነው ራሱ ገዢው ፓርቲ መሆኑ ነው።
አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች ( በዉጭ ያሉትን አይመለከተም፤ እኔ ዉጭ ያሉት እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ አላያቸዉም፤ለምን እዳያስፖኢራ ሆኖ፣ ከህዝቡ ርቆ ፣ ድጋፍ ከመስጠት ዉጭ የሚደረግ ትግል ስለሌለ) በአገዛዙ ላይ ቁርሾ የላቸዉም። በሕወሃት የፖለቲካ ዉሳኔ የታገደው እነ አቶ ግርማ ሰይፉ አመራር የነበሩበት የአንድነት ፓርቲ በአገዛዙ ላይ ቁርሾ አልነበረውም። አብዛኛው አመራሩ አገዛዙ የዘረጋቸውን የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ፍላጎት የነበራቸው፣ የአባይን ቦንድ የገዙና ገንዘብ ያዋጡ ናቸው። አቶ ግርማ ሰይፉ ከነ አባ ዱላ ጋር በመሆንም በአባይ ግደብ ዙሪያ ሁሉ ግብጽ ድረስ በመሄድ አጋርነትን ያሳዩ ናቸው። ሆኖም አገዛዙ ሞደሬት፣ ዘመናዊ የተባሉ ድርጅቶችን ሁሉ ነው በኃይል የጨፈለቀው። የሚገድለው፣የሚያስረው፣ ጽ/ቤት የሚያዘጋው፣ የተለያዩ ሕጎች እያወጣ የሚያሽብረው፣ ከሥራ የሚያባረርው፣ ከቤት የሚያፈናቅለው አገዛዙ ራሱ ነው። ሌላውን እንደጠላት እያየ ለማጥቃትና ለመንቀሳቀስ የሞከረው ራሱ አገዛዙ ነው። እንጂ አገር ቤት ያሉ በሰላም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ኢሕአዴግን እንደ ጠላት የቆጠሩበት ሁኔታ የለም።
ስለዚህ ሪፖርተር ያሰፈረው ሐሳብ ተግባራዊ እንዲሆን፣ የሰለጠነ ፖለቲካ፣ ሰላም በአገራችን እንዲሰፍን በዋናነት መለወጥ ያለበት አገዛዙ ራሱ ነው። አገዛዙ ተቃዋሚዎችን እንደ ጠላት ማየት ማቆም አለበት። በመድበለ ፓርቲ የሚያምን ከሆነ፣ የተጨበጡ ተግባራት መፈጸም አለበት። ለድርድር መተማመን እና መቀባበል ያስፈለጋል። ይህ መተማመን እንዲኖር፣ የታሰሩ የተቃዋሚ እስረኞችን በሙሉ መፈታት አለበት። አንዱዋለም አራጌን፣ ዮናታን ተስፋዬን፣ ተስፋዬ ታሪኩን፣ ዶር መራራ ጉዲናም፣ ኮሎኔል ደመቀ ዘዉዱ የመሳሰሉትን አስሮ ለድርድር መቅረቡ ሂደቱን ከወዲሁ እንዲበላሽ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን መተማመንን የሚያመጣ አይደለም። ብዙዎች ካለፉት ታሪኮች በመነሳት “ወያኔን ማመን ቀብሮ ነው። ወያኔ አይታመንም” የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው። በአንድ በኩል ትክክል ናቸው። ሆኖም ግን የአሁኑ ሁኔታ ከዚህ በፊት ከነበረው በእጅጉ የተለየ በመሆኑ፣ እንዳልፈው የይስሙላ ብቻ ድራም ላያደርጉ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ። እንግዲህ አገዛዙ በርግጥ እንደከዚህ በፊቱ አስመሳይ አለመሆኑን በተጨባጭና በተግባራ ማሳየት አለበት።
እንደ አየለ ጫሚሶ ቡድን ያሉ ግብስብ ቡድኖችን እንተዋቸዉና ተቀባይነት ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች (በተለይም መኢአድ፣ ሰማያዊ፣ መድረክ እንዲሁም ኢዴፓ) የተጨበጠ ነገር በሂደት ካላዩ ፣ ምንም እንኳን አሁን ቅድመ ሁኔታ ባያስቀመጡም፣ ሂደቱን አቋርጠው መወጣታቸው የማይቀር ነው።
ደግሜ እላለሁ፣ ገዢው ፓርቲ ይሄንን እድል ማበላሸት የለበትም። ይሄ የሰላም ድርድር በሕዝብ ተአማኒነት እንዲኖረው የሚያደርግ ሥራ በቶሎ መስራት አለበት። ደግሜ እላለሁ ይሄ ስራ መጀመርም ያለበት የተቃዋሚ መሪዎችን ሁሉ በመፍታት ነው።

No comments:

Post a Comment