አቃቤ ህግ በእነ ንግስት ይርጋ ላይ ያለውን የክስ መቃወሚያ አስተያየት አላቀረበም (የካቲት 7, 2007)
*በቀን ለአንድ ሰአት ብቻ ነው ከቤተሰብ እንድገናኝ የሚፈቀድልኝ።
ከተመዘገቡ ቤተሰቦች ውጪ አልጎበኝም። -ተከሳሽ ንግስት ይርጋ
የዛሬ የካቲት 7, 2007 ቀጠሮ የነበረው ተከሳሾች በቀረበባቸው ክሰ ላይ ባስገቡት መቃወሚያ ላይ አቃቤ ህግ ያለውን አስተያየት እንዲያቀርብ ነበር። ሆኖም አቃቤ ህግ በስራ መደራረብ ምክንያት መልሱን ማድረስ እንዳልቻለ ተናግሮ ተጨማሪ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል። የተከሳሽ ጠበቆች የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ እና አለልኝ ምህረቱ፤ አቃቤ ህግ ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ እና ተገቢ እንዳልሆነ፣ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት እንደነበረ እንዲሁም በስነስርአት ህጉ የመቃወሚያ ምላሽ ለመስጠት የተሰጠው ጊዜ አንድ ሳምንት መሆኑንን በመጥቀስ ተጨማሪ ቀጠሮ ሳይጠበቅ አቃቤ ህግ ምላሽ እንዳልተሰጠ ተቆጥሮ የመቃወሚያው ብይን እንዲሰራላቸው ጠይቀዋል።
አቃቤ ህግ በነ ንግሰት ይርጋም ሆነ ሌሎች በእለቱ በችሎቱ የሚታዩ መዝገቦች ላይም አቃቤ ህጎች ስልጠና ላይ ስላሉ በጥቂት አቃቤ ህጎች ብቻ ስራ እየተሰራ እንዳለ እና የስራ መደራረቡም ከዛ የመጣ እንደሆነ ተናግሯል።
ዳኞችም የሁለቱን ክርክር ከሰሙ በኋላ ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት የቢኖራቸውም የሁለቱንም ወገን አስተያየት መቀበል ተገቢ እንደሆነ ተናግረው፤ አቃቤ ህግ ያቀረበው ምክንያት ሁል ጊዜም ባይሆን አልፎ አልፎ የሚከሰት ነገር እንደሆነ ጠቅሰው ምክንያቱን አሳማኝ ነው ብለው አቃቤ ህግ በቀጣይ ቀጠሮ በመቃወሚያው ላይ ያለውን አስተያየት እንዲያቀርብ ጥብቅ ትእዛዝ ሰጥተዋል።
5ኛ ተከሳሽ የሆነው በላይነህ አለምነህ፤ ቤተሰቦቹ ከባህርዳር አዲስ አበባ ድረስ መጥተው በችሎት እንደሚገኙ ጠቅሶ ነገ በጠዋት ወደ ባህርዳር ስለሚመለሱ እና ከሰአት ደግሞ ማረሚያ ቤት ከቤተሰብ ስለማያገናኝ በችሎት እንዲገናኙ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።
1ኛ ተከሳሽ ንግስት ይርጋ፤ ካስመዘገበችው ቤተሰብ ውጪ እሷን ለመጠየቅ ቤተሰቦቿ እንደተቸገሩ አና የምትጠየቀውም በቀን ለአንድ ሰአት ያክል ብቻ መሆኑን (ከ6 እስከ 7 ሰአት) የተናገረች ሲሆን ለአብነት ያክልም ከጎንደር ከሳምንት በፊት የመጣ በችሎቱ የተገኘ ወንድሟ ሳምንቱን ሙሉ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ቢመላለስ እሷን ለማግኘት እንዳልተፈቀደለት ተናግራለች። ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስትገባ “የሚጠይቁሽ ቤተሰቦች አስመዝግቢ” ስትባል በቅርብ (አዲስ አበባ) ያሉ እና ተመላልሰው የሚጠይቋትን ብቻ እንዳስመዘገበች፤ ከጎንደር ያሉ ቤተሰቦቿን ግን ማን ይምጣ ማን አይምጣ ስለማታቅ ለማስመዝገብ በመቸገሯ ሳታስመዘገብ እንደቀረች በመገለፅ ተጨማሪ የሚጠይቋት ቤተሰቦቿን ለመጨመረም እንደተቸገረች ተናግራለች።
ዳኞች የሁለቱንም ተከሳሾች አቤቱታ ከሰሙ በኋላ በማረሚያ ቤት አሰራር እንደማይገቡ በመናገር ከቤተሰብ መገናኘት ከተከለከሉ ግን አቤቱታቸውን መቀበል እንደሚችሉ ገልፀው ያቀረቡት አቤቱታ እነሱን የሚመለከት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ቀጣይ ቀጠሮ ለየካቲት 15, 2007 ተይዟል።
ይህ ዘገባ የተገኘው ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት ነው::
No comments:
Post a Comment