Monday, February 13, 2017

አድማሱ “ዛፍ” በቆረጠበት ጊዜ – (የዩኒቨርሲቲው ሥነ ውበታዊ ክስመት



አድማሱ “ዛፍ” በቆረጠበት ጊዜ – (የዩኒቨርሲቲው ሥነ ውበታዊ ክስመት)
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
“እና – እንደኔና እንዳንቺው የውበት ዐይኑ የታወረ፣
እግረ ኅሊናው የከረረ፤
ባሕረ ሐሳቡን ያልታደለ፣
የውበት ዐይኑ የሰለለ፣
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ አበባ እኮ አይደለም አለ፡፡
ያልታደለ፤…” (“እሳት ወይ አበባ”)
“እና – እንደኔና እንዳንቺው የውበት ዐይኑ የታወረ፣
እግረ ኅሊናው የከረረ፤
ባሕረ ሐሳቡን ያልታደለ፣
የውበት ዐይኑ የሰለለ፣
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ አበባ እኮ አይደለም አለ፡፡
ያልታደለ፤…”    (“እሳት ወይ አበባ”)
መግቢያ
ታኅሣሥ 29 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. በዓለ ገና፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ዕድገትና ደረጃን በሚመለከት በጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት በሚያስተምር ግለሰብ ዋና የመረጃ ሰጪነት፣ ዘጋቢ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተላልፎ ነበር፤ የፕሮግራሙ አቀራረብም፣ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬን ማዕከል ያደረገ ነበር፡፡ እንዲኽ ዓይነት ይዘት ያለውን የዶክመንተሪ አቀራረብ፣ አሜሪካኖች* “Charm offensive” ይሉታል፡፡
ይህን ሲሉ፣ ኾን ተብሎና ታቅዶ፣ የራስን የማንነት ውበትና በጎነት አጉልቶ በማውጣት የሚቀርብ ድርጊትን መግለጻቸው ነው፡፡ ይህንኑ የራስ መልክአ ውዳሴ ወደ አማርኛ ስንተረጉመው፣ “አጀብ እዩልኝ” ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ዶክመንተሪው በዋናነት፣ የዩኒቨርሲቲውን ጉዳይ ያነሣ ቢመስልም፣ ዐቢይ ትኩረቱ ግን፣ ፕሬዝዳንቱን እንዲኹም የሥራ አፈጻጸማቸውን አጉልቶ ለማውጣት ያለመ ነው፡፡ ኾኖም፣ እውነታው* በመልክአ ውዳሴው ከቀረበው የዩኒቨርሲቲው ኹኔታ እንዲኹም፣ ከፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ ገጸ ሰብእና ጋር ሲነጻጸር ፈጽሞ የተራራቀ ነው፡፡
ይህን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ የወዲያው ሰበብ የኾነኝ፣ ይህንኑ የእውነታ መራራቅና መጣረስ ለማሳየት በማሰብ ነው፡፡ ኹለተኛውና ዋነኛው የጽሑፌ መንሥኤ ግን፤ በፕሬዝዳንት አድማሱ እና በቦርዱ ሊቀ መንበር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ይኹንታ ሰጪነት፣ በዩኒቨርሲቲው ቅጽር የተካሔደው የዛፍ ምንጠራ ድርጊትና የሕንፃ ግንባታ አስከትሎት ጉዳይ ነው፡፡
ይህ መጣጥፍ፣ የኹለት ክፍሎችን ቅንብር የያዘ ነው፡፡ አንደኛው* የዩኒቨርሲቲውን ዛፍ ምንጠራ እና የዕውቅ ሥነ ውበታዊ መገለጫውን መገፈፍ በየአንጻሩ ማሳየት ሲኾን፤ ኹለተኛው ደግሞ፣ ዛፍ ምንጠራው፣ የዩኒቨርሲቲውን መካነ አእምሯዊ ተልእኮ ለማሳካት ሳይኾን፣ የፕሬዝዳንቱንና ፈቃድ የሰጡትን ሹመኞች ፍላጎትና ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት መኾኑን በጥቂቱ ማሳየት ነው፡፡
ኢንዱስትሪ እና ዩኒቨርስቲ
የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪውና በኢትዮጵያ ጉዳዮች በርካታ ጥናቶችን ያሳተሙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፣ ከኅልፈታቸው ጥቂት ዓመታት ቀደም ብለው* “Powers of the Mind: The Renovation of Liberal Learning in America” በሚል ርእስ፣ ስለ ዩኒቨርሲቲ ፍልስፍና መጽሐፍ አሳትመው ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪን፣ ስለ ዩኒቨርሲቲ ምንነት በርካታ ጥልቅ ሐሳቦችን የገለጹ ቢኾንም፤ ከዚኽ መጣጥፍ ዋና ይዘትና መንፈስ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውን አንዱን አገላለጻቸውን ብቻ ወስደናል፡፡
ፕሮፌሰር ሌቪን፣ “ዩኒቨርሲቲ፣ በኢንዱስትሪ የውጤታማነት መለኪያ መስፈርት ሊመዘን አይገባም፤” ይላሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አገላለጽ፣ ዩኒቨርሲቲ በኢንዱስትሪ መለኪያ የማይመዘንበት ምክንያት* በይዘት፣ በዓላማም ኾነ በውጤት ከኢንዱስትሪ የተለየ በመኾኑ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ዩኒቨርሲቲ እንደ ኢንዱስትሪ ገበያ የሚፈልገውን ብቻ ፈብርኮ የሚያቀርብ ሳይኾን፣ ተማሪዎች፣ ለጥናትና ምርምር የተኮተኮተ አእምሯዊ ማሕቀፍ እንዲኖራቸው ለማስቻል የተደበረ የዕውቀት ኀሠሣ ማዕከል በመኾኑ ነው፡፡
ይህን መሠረታዊ የዩኒቨርሲቲ እና የኢንዱስትሪ ባሕርያዊ ልዩነት በውል ባለመገንዘብ፤ የወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ፤ መድረክ ባገኙባቸው አጋጣሚዎችና ከላይ በጠቀስነው “የአጀብ እዩልኝ” ዶክመንተሪያቸው ሳይቀር፤ ስለሚመሩት ዩኒቨርሲቲ ሲገልጹ፣ ደጋግመው የሚጠቀሙባቸው ዕዝሎችና ቅጽሎች፡- ‹አደረጃጀት›፣ ‹ሽፋን›፣ ‹ቅበላ›፣ ‹ቁጥር›፣ ‹ግንባታ›፣ ‹የኃይል ትስስር›፣ ‹ፕሮጀክት›፣ ‹አንድ ለአምስት› … ወዘተ. ናቸው፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት ቅጽሎችና ሐረጎች፤ የኢንዱስትሪ የምርታማነትና የውጤት ደረጃ አመልካች መለኪያዎች፤ የአንድ ፋብሪካ የምርት ቁጥጥር ሓላፊ ወይም የሕንፃ ግንባታ ተቆጣጣሪ “ካቦ”፣ በሚያቀርበው ሪፖርት የሚጠቀማቸው ቃላት እንጂ፣ “ⷈሉ አመክሩ ወዘሠናየ አጽንዑ”(ኹሉን መርምሩ መልካሙንም አጽንታችኹ ያዙ) የሚለውን ታላቅ ኃይለ ቃል ይዞ የተነሣን፣ የማእምራን መዲና የኾነ ዩኒቨርሲቲን መንፈስ የሚወክል ወይም የሚመጥን አይደለም፡፡
“አድማሱ ዛፍ የመነጠረበት ዘመን”
የዚኽን ንኡስ ርእስ ሐሳብ የወሰድኹት፣ በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ታዋቂ ከኾነና በስፋት ከሚነገር ታሪክ ወስዶ፣ አንድ ወዳጄ በአንድ ወቅት ያጫወተኝን ትረካ መሠረት አድርጌ ነው፡፡ ትረካው በአጭሩ ሲቀርብ እንደሚከተለው ነው፡፡
ልዑል ራስ ኃይሉ እና ዐፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በራስ ካሳ ሥር ታስረው በነበሩት በልጅ ኢያሱ ከእስር ቤት ማምለጥ፤ ራስ ኃይሉ፣ “ተሻርከው አስመልጠዋል” በሚል ምክንያት የከረረ ጠብ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ልዑል ራስ ኃይሉም ከጎጃም አገረ ገዥነት ተሽረው በእስርና በግዞት ይሰደዳሉ፡፡ በምትካቸውም፣ ከንቲባ ማተቤ ደረሶ ደብረ ማርቆስን ተሾሙ፡፡ ይህን የሥልጣን ሽግግር አገሬው ስላልወደደው፣ የራስ ኃይሉን ልጅ ፊታውራሪ አድማሱ ኃይሉን ይዞ ተቃውሞ ቀሰቀሰ። በጊዜውም በደብረ ማርቆስ ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት ውስጥ በግብር የተሰበሰበና የራስ ኃይሉም የግል ንብረት የነበረ ሀብት፤ “የሸዋ ሹመኞች መጥተው ሊወስዱት ነው፤” ተብሎ ስለተወራ፤ እነፊታውራሪ አድማሱ፤ “ይህ ንብረት ሸዋ ከሚሻገር ጎጃሜ ይውሰደው!” በማለት፤ ግምጃ ቤቱን ከፍተው በሕዝብ አስመዘበሩት፡፡ ይህም ድርጊት እስከ ዛሬ በጎጃም፣ “አድማሱ ያፈረሰው ጊዜ” ተብሎ ሲወሳ ይኖራል፡፡
ወደ ጥንተ ነገራችን ስንመለስ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አድማሱ ጸጋዬ፣ “ለዩኒቨርሲቲው ማስፋፊያ ሕንፃ መገንባት አስፈላጊ ነው፤” በሚል መነሻ፣ የቅጽረ ግቢው ግርማ ሞገስ ኾኖ በዓለም የሚታወቀውን ዐጸድ በማስመንጠር፣ የማይበጅ አፍራሽ ተግባር ፈጽመዋል፡፡
የኹለቱም “አድማሱ”ዎች ድርጊት፣ በጥቅሉ “የአፍራሽ” ቅጽል ተሰጥቶት ቢገለጽም፤ የመጀመሪያው አድማሱ የተነሡበት መንፈስ፣ ለጎጃም ሕዝብ ወገንተኝነት የቆመ ሲኾን፤ ይህም ድርጊታቸው በጊዜው በሕግ ቢያስጠይቃቸውም፣ ከሞራል አንጻር ሲታይ ግን የሚያስኰንናቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ የኹለተኛው አድማሱ አፍራሽነት ግን፤ በሕግም ኾነ በሞራል መስፈርት ያስጠይቃቸዋል፡፡ ይኸውም፣ ከዩኒቨርሲቲው ቅጽር ሥነ ውበት አንጻር የሚያስጠይቅ ስሕተት ተፈጽሟል፤ የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡
የመጀመሪያው አድማሱ አፍራሽነት፣ ስሕተት ከተባለ መግፍኤው፣ ለሕዝብ ከመቆም ሲኾን፤ የኹለተኛው አድማሱ የአፍራሽነት ድርጊት ግላዊና መለካዊ (ሥልጣን ሰገድ) ከመኾን የመነጨ ነው፤ ማለት እንችላለን። በመኾኑም፣ የቀዳሚው አድማሱ ድርጊት፣ አንድ ማኅበረሰባዊ ተረክ ኾኖ እንደቆየን ኹሉ፣ የዩኒቨርስቲው አድማሱ የደን ምንጣሮ አፍራሽነትም ለትውልድ ሲነገር ይኖራል፡፡
የደን ምንጣሮው፡- ከሥነ ሕይወት፣ ከሥነ ውበት እና ከፎክሎር አተያዮች አንጻር፤
ሀ/ሥነ ሕይወት
የዛፍን ምንነትና ኹለንተናዊ ጥቅም አስመልክተው፣ ወ/ሮ ዕሌኒ መኩሪያ የተባሉ ዕውቅ ጋዜጠኛ፤ “ዛፎች ለሕይወት” በሚል ርእስ በ2005 ዓ.ም. መጽሐፍ አዘጋጅተው ነበር፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ስለ ዛፍ እና ሥነ ሕይወት* ማብራሪያዎች፣ ፎቶግራፎች፣ ግጥሞችና መጣጥፎች ተካተውበታል፡፡ የእኒኽ ዓይነት መጻሕፍት ዓላማ፤ ዛፍ እንዳይመነጠርና ለዛፍ ክብካቤ እንዲደረግ አበክሮ ማሳሰብ በመኾኑ፤ ስለ ሥነ ሕይወት እና ሥነ ምኅዳር ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ኾኖ አግኝቼዋለኹ። ይህን በመሰለ ጥረት፣ ለማኅበረሰቡ የዛፍን ጥቅም በወል ለማስጨበጥና ለማስተማር በሚሞከርበት ጊዜ፤ ዩኒቨርሲቲው፣ ሲኾን፣ ከነወ/ሮ ዕሌኒ መኩሪያ ጋር በአስተማሪነት ይሰለፋል ብለን ስናስብ፤ በተቃራኒው የዛፍ ጭፍጨፋ ተግባር ላይ ተሰልፎ መገኘቱ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡
የወቅቱ የዩኒቨርሲቲው አመራር እና አስተዳደር፣ ዩኒቨርሲቲው ለመጪው ትውልድ የሚያገለግል ዐጸድ መትከልና አኹን ያሉትንም መከባከብ ሲገባው፤ ራሱ ያልተከለውንና ከዘመናት በፊት የነበረውን ደን መመንጠሩ፣ ዩኒቨርሲቲው፣ ስለ አካባቢ ጥበቃ አስፈላጊነት ለማኅበረሰቡ ለማስተማር የነበረውን የዕውቀትና የሞራል ልዕልና እንዲያጣ ምክንያት ኾኗል፡፡
እንዲኽ ያለው ብዝኃ ሕይወትን የመጠበቅና የመከባከብ ሓላፊነት፤ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለው ተቋም ይቅርና በዜግነት ደረጃ እንኳን ግለሰብ ሊፈጽመው እንደሚገባ፤ በአንድ ወቅት ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ፣ የደን ምንጠራን በመቃወም ካሳዩት አርኣያነት የምንረዳው ነው፡፡
ከጥቂት ዐሥርት ዓመታት በፊት፣ በፈረንሳይ ለጋሲዮንና በቤላ መካከል በሚገኝ በአንድ በደን በተሸፈነ ይዞታ ላይ ምንጣሮ ሊካሔድ አስተዳደራዊ ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡ በተጠቀሰው አካባቢ ያለው ደን፣ ከአዲስ አበባ ምሥረታ ኹለትና ሦስት ምእተ ዓመታት ቀድሞ የነበረና ሀገር በቀል ዕፀዋትን የያዘ ነው፡፡ ደጃዝማች ዘውዴ፣ በእነዚኽ ዕፀዋት ላይ የተላለፈው የምንጣሮ ውሳኔ እጅግ የተሳሳተ መኾኑን ለመግለጽ፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ አስተባብረው ተቃውሟቸውን በማቅረብ  ምንጣሮውን ማስቀረት መቻላቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ከደጃዝማቹ አርኣያነት ያለው ዜግነታዊ ተግባርና እነወ/ሮ ዕሌኒ ካሳተሙት የደን ኹኔታን ከሚያሳይ መጽሐፍ መንፈስ፣ በብዙ መልኩ፣ ለተፈጥሮ በተለይም ለደን ክብካቤ መቆም እንደሚገባን እንረዳለን፡፡ በአንጻሩ፣ የዩኒቨርሲቲው ድርጊት አሳዛኝ ከመኾን አልፎ መንግሥታዊ ይኹንታ ላለማግኘቱ ማረጋገጫ የለንም። በመኾኑም፣ ስሕተቱ፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር ብቻ ሳይኾን፣ መንግሥትን ወክሎ የተቀመጠው የቦርዱም ሓላፊነት ያለበት ጭምር እንደኾነ ልብ ይሏል፡፡
ለ/ሥነ ውበት
አንድ ሰው* ስለ ጥበብ፣ ስለ ተፈጥሮ፣ ስለ ውበት… ወዘተ. መረዳት የሚችለው፣ ለተፈጥሮ የሚማልል ንቁና ሥሡ ስሜት ሲኖረው ነው፡፡ ይህ ስሜት ደግሞ፣ በተፈጥሮ የሚገኝ ብቻ ሳይኾን፣ ከትምህርት እና ከአድናቆት ጋር በተያያዘ ስሜታችን ሲኮተኮትና ሲሠለጥን የሚገኝ ነው፡፡ ግለሰቡ ውስጣዊ ጉጉት ካለው በእነዚኽ ጉዳዮች ይደነቃል፤ ይደመማል፤ ይማረካል፤ ይማራል፤ ይቆረቆራል፡፡ ነገር ግን፣ ግለሰቡ፣ የሥነ ውበት መማረክ ከሌለው፣ ውስጡ በሥነ ውበት ስእነት(ኢከሃሊነት) የተሞላ ሕጹጽ ነው፤ ማለት ነው፡፡
ይህን ለመግለጽ፣ አንዳንድ ሠዓሊዎች ግድግዳ ላይ የተሰቀለን ሥነ ጥበባዊ ሥራ አይተው፣ “ከፊል ቦታ ላይ ‘dead spot’ ስላለው መስተካከል አለበት” የሚል ሞያዊ አገላለጽ ይጠቀማሉ፤ ቀለም አንሶታል፤ ሕይወት አልባ ነው፤ ለዛ የለውም፤ ደብዝዟል፤… ወዘተ. ማለታቸው ነው፡፡ ይህን ብሂል ወደ ሰው ስናመጣው፣ ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ፣ ሥነ ውበትን ለማድነቅ የሚያስችላቸው የስሜት ሕዋሳቸው በድኗል ወይም አልተኮተኮተም ማለት ነው፡፡ በመኾኑም፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትና ይኹንታ የሰጡት የቦርድ ሹመኞች፤ ከሥነ ውበት ክሂል አንጻር ርምጃቸውን ስናየው፣ የሥነ ውበት አድናቆት ስእነት(ኢከሃሊነት) ሰለባ መኾናቸውን በግልጽ እንረዳለን።
ታላቁ ባለቅኔና ጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ በ“እሳት ወይ አበባ” ግጥሙ ላይ፣ ስለ ክሂለ ቢስነት (dead spot) ከተቀኘው ጥቂት ስንኞችን እንጥቀስ፤
“እና – እንደኔና እንዳንቺው የውበት ዐይኑ የታወረ፣
እግረ ኅሊናው የከረረ፤
ባሕረ ሐሳቡን ያልታደለ፣
የውበት ዐይኑ የሰለለ፣
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ አበባ እኮ አይደለም አለ፡፡
ያልታደለ፤…”
በመኾኑም፣ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የነበረው ተፈጥሮ የለገሰን ውበት በሚገፈፍ ጊዜ፣ ምን ዓይነት ኹኔታ ይፈጠራል? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ ይህን የሥነ ውበት ረድኤት በተመለከተ፣ ኹለት ፈላስፎች ተጠቃሽ አስተምህሯቸውን በሚከተለው መልኩ አስቀምጠውልን አልፈዋል፡፡
የመጀመሪያው፣ የ18ኛው መ/ክ/ዘ ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት፣ በወሳኝ የሥነ ውበት ድርሳኑ (Critique of Judgment)፣ ሥነ ውበትን በመሠረቱ ሲተረጉመው* “Purposiveness without a purpose” ይለዋል፡፡ ይህም ማለት፣ “ይህ ነው” ተብሎ በግኡዛዊ መስፈርት የማይለካ ኾኖ ግብ ያለው እንደ ማለት ነው፡፡ በእርሱ አገላለጽ፡- ተዝናኖት፣ አማሕልሎት እና ሥነ ውበት ያለው ተፈጥሮም ኾነ ጥበብ፣ ከውስጡ ቀጥተኛ የኾነ የተሰፈረ ዓላማ፣ አመክንዮ ወይም ጥቅም የተቀመጠለት አይደለም። ይልቁንም፤ ውብ የኾነ ነገር ማለት፤ ከውስጡ ምንም ቀጥተኛ ጥቅም ሳናገኘበት፣ በውበቱ ብቻ የምንወደው ወይም የምናደንቀው፤ የረቂቁ ሰብአዊ ተፈጥሯችን የሥነ ውበት አድናቆት ስሕበትና “ረኃብ” በሚፈጥርብን ልዩ ፍላጎት ብቻ የምንወደው ማለት ነው፡፡
ይህን ካንታዊ የሥነ ውበት ገለጻ፤ በሀገራችን ነባር አስተምህሮ ለማንጸር ብንሞክር፣ በቤተ ክህነት የሥነ ፍጥረት ትምህርት ያለውን አጠይቆ እንደ አብነት መጥቀስ እንችላለን፡፡ እንደ አስተምህሮው፣ አዝማደ ፍጥረታት በየወገናቸው ስለ ሦስት ምክንያት (ረብሕ) ተፈጥረዋል፡፡ እኒኽም፣ አንደኛው* ለአንክሮ (ለመደመም)፣ ኹለተኛው* ለተዘክሮ (ለተምህሮ)፤ ሦስተኛው* ለምግበ ሥጋ ወነፍስ ናቸው፡፡
ኢማኑኤል ካንት፣ “ቀጥተኛ የተሰፈረ ጥቅም የሌለው ግን ረብ ያለው፤” የሚለውን አገላለጹን፤ ጥንታዊው የቤተ ክህነት አስተምህሮ፣ “ምክንያተ አንክሮ” ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረው፣ ጥቂቱን ለጥቅመ ሥጋ ወነፍስ ሲኾን፤ ብዙውን ግን ለአድናቆት፣ ለመደመም፣ “ወይ የአምላክ ሥራ!” ብለን በአንክሮ የመለኮትን ምስጢር እንድናስተውል፣ የመንፈስ ተመስጦና የልቡና ሐሤት እንድናገኝበት ነው፡፡ ይህን ተሰጥሞ ልቡና እና መንፈሰ ሐሤት የቤተ ክህነቱ አስተምህሮ፥ “አንክሮ” ይለዋል፡፡
ይህን የኢትዮጵያ ጥንታዊ አስተምህሮ እና የኢማኑኤል ካንት “የአንክሮ እና የተደሞ” መሠረተ ሐሳብ፤ ከዛሬው የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ የአድማሱ ጸጋዬ አስተዳደር መጠበቅ የዋህነት መኾኑን፣ በዛፍ ምንጠራ – ተማስሎ – ድርጊት ፍንትው ብሎ ታይቷል፤ አስተዳደራዊ አስተሳሰቡ፣ ሥነ ፍጥረት፣ ከጥቅመ ሥጋ ያለፈ ረብሕ እንደሌለው በማያሻማ ኹኔታ አሳይቷልና፡፡
ፍሬድሪክ ሺለር የተባለው የ19ኛው መ/ክ/ዘመን የሥነ ጥበብ ሰው፣ “Letters on the Aesthetic Education of Man” በሚል ርእስ በጻፈው ጦማር፣ ስለ ሥነ ውበት ምንነት በእጅጉ አስደማሚ የኾነ አጭር ጽሑፍ አቅርቧል፡፡ ጽሑፉ፣ በርከት ያሉ ርእሰ ጉዳዮችን ቢያነሣም፣ ከፍጥረት የሚገኝ ውበት ሰውን ሊያጎናጽፍ ስለሚችለው ሐሤት እንደሚከተለው አትቷል፤
ሺለር እንደሚለው፣ የግለሰቡም ኾነ የማኅበረቡ ልዩነት፣ ሥነ ውበት ፊት ሲቀርብ፣ ልዩነቱ ኹሉ ይቀርና በመስሕቡ ተማርኮ ኹሉም፣ እያንዳንዱም ያለ ልዩነት እኩል ለሥነ ውበት ይማልላል፡፡
ይህን የሺለር ሐሳብ ይዘን፣ ዩኒቨርሲቲውን በምናይበት ጊዜ፣ ትላንት ዛፉ ሳይቆረጥ፣ ማንኛችንንም ሊያግባቡን ያልቻሉ* የብሔር፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የጾታ፣ የመደብ… ወዘተ. አመለካከቶች ሳያግዱን፤ በግቢው ውስጥ የነበረውን መስሕብ ያለው ዐጸድ ያለ ልዩነት በአንድነት እናደንቅ ነበር፡፡ በአኹኑ ወቅት ግን፣ ይህ ዐጸድ ተጨፍጭፎ በፎቆች ሲተካ፣ ሺለር እንዳለው፣ ከተፈጥሮ ውበት ይገኝ የነበረው ንጽረታዊ አንድነት ተጓድሎ፣ ኹላችንም የጋራ አጽድቆት በማንሰጠው ፎቅ ተተክቷል፡፡
እዚኽ ላይ፣ አስተውሎት እንዲኖረን ይገባል ብዬ የማስበው፣ አገዛዙ፣ የጋራ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዕሴቶችን የመናድ ባሕርያዊ መገለጫው፤ በቅጽሩም ላይ፣ እንደተለመደው፣ ዜጎች ወደ ግቢው ሲዘልቁ የሚያገኙትን ተፈጥሯዊ የጋራ ደስታ በማውደም እንድንለያይ የማድረግ ተግባሩን እንደተያያዘው እንገነዘባለን፡፡
ሐ/ ፎክሎር
የሰው እና የሥነ ሕይወት መስተጋብር፣ በቅርቡ ከምዕራቡ ዓለም የተዋስነው ወይም በሰበካ የተቀበልነው ጉዳይ ሳይኾን፣ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ የአገራችን ማኅበረሰብ ባህል ውስጥ የነበረ አስተሳሰብና ልማድ ነው፡፡ በአገራችን ማኅበረሰቦች ነባር ባህል ውስጥ፣ ስለ ዛፍ ያለው እሳቤ የተለያየ ቢኾንም፣ በአብዛኛው ዛፍ በሰው ልጅ ሕይወት ያለው አገልግሎት ሥሉጥ እንደኾነ እንረዳለን፡፡
ከአገልግሎቱም መካከል፣ ዛፍ፡- መሰብሰቢያ፣ እርስ በርስ መመካከርያ፣ መጠለያ፣ ዕርቅና አፈርሳታ ማካሔጃ ከመኾኑም በላይ፣ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ በመኾን ያገለግላል፡፡ ዛፍ፣ በአንዳንድ ማኅበረሰብ ባህል ውስጥ የማንነት ትእምርት ሲኾን፣ ዛፍን ከሕይወት መሠረት ጋራ በማያያዝ፣ የራሳቸውን ጥንተ አመጣጥ በሐተታ – ተፈጥሯዊ – ሚት መልክ የሚያቀርቡ ማኅበረሰቦች በአገራችን እንዳሉ፤ ሰሎሞን ተሾመ፣  “ፎክሎር፤ ምንነቱ እና የጥናቱ የትኩረት አቅጣጫ” በሚለው መጽሐፉ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም፣ “ዛፍ የሌለው ደብር* ጽሕም የሌለው መምህር” እንዲሉ፣ አብያተ ክርስቲያናትን በርቀት እይታ የምንለያቸው፣ በዙሪያቸውና በግቢያቸው በከበቧቸው ታላላቅ ዐጸዶች ትእምርታዊነት ነው፡፡ ገዳም ማለትም፣ በአንድ ገጹ* ዱር፣ ጫካ፣ የአራዊት መናኸርያ እንደማለት ነው፡፡(ኪዳነ ወልደ ክፍሌ፣ 302)
ማጠቃለያ
ሰው ምሉእነትን የሚጎናጸፈው፣ ለቁመተ ሥጋው የሚያስፈልገውን ምግብ ስላገኘ ብቻ አይደለም፡፡ ታላቁ መጽሐፍ እንደሚለውም፣ “የሰው ልጅ በእንጀራ ብቻ አይኖርም፡፡” ይልቁንም፣ ከፍጥረታት ኹሉ የሚለየው የአእምሮ እና የመንፈስ ምግብ ጥያቄው ትልቅ ቦታ ይይዛል፡፡ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ተቀዳሚ ሚና፣ ይህንኑ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ለማወቅ በብርቱ የሚሻውን አእምሯዊና መንፈሳዊ “መፍቅድ” ለማሟላት መጣር ነው፡፡
ከላይ የጠቀስናቸው ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን፣ “በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በኅብረ ሠናይ (Common Good) እና በጥቅም – ተኮር – ሠናይ (Utilitarian Good) መካከል ውጥረት ይኖራል፤” ይላሉ፡፡ በእነኚኽ ተፃራሪም ተደጋጋፊም ውጥረቶች መካከል፣ አንድ ዩኒቨርሲቲ በጎ መልክ ይዞ ሊወጣ የሚችለው፣ የጋራ ሠናይ ፍላጎትን፣ ከጥቅም ተኮር ፖሊሲ በላይ በማስቀደም ሲጓዝ ነው። ይህ ሲኾን ግን፣ ጥቅም ተኮር ሠናይነትን አምዘግዝጎ ይጥለዋል ማለት ሳይኾን፤ ይኸው ጥቅም ተኮርነት በጋራው ሠናይ ፍላጎት ውስጥ ተካብቶ የሚቀመጥ በመኾኑ ነው። በአንጻሩ፣ ጥቅም ተኮር ሠናይ፣ የጋራ ሠናይ ፍላጎትን በምልአት ይዞ አይገኝም፡፡
ፕሬዝዳንት አድማሱ፣ የዩኒቨርሲቲውን ልዕልና እና አካዳሚያዊ ንጽሕ (Chastiti) በማስደፈር፣ መንግሥት* “ዕድገት እና ልማት” የሚለውን ፖሊሲ ለማንሰራፋት በሙሉ ልብ ስለ ተሰማሩ፣ በቅጽሩ ውስጥ ያሉት ዐጸዶች ተቆርጠው፣ “ልማት” ለሚባለው ጣዖት ሰለባ እንዲኾኑ አድርገዋል፡፡ ከአእምሯዊ ይልቅ አካላዊ መስፋፋትን አብልጦ አትኩሮት መስጠት፣ የትምህርት ፈላስፎች እንደሚሉት፣ በ“ዳይናሶራዊ ሲንድረም” መለከፍ ነው፡፡
ይኸውም፣ ዳይናሶር፣ ስዒረ ፍጥረት የደረሰበት አካላዊ ግዘፉ እየፋፋ፣ አእምሯዊ ኃይሉ እያጸጸ ቆይቶ፣ ራሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ወደማይችልበት ክስመት ደርሶ ህልውናው በመጥፋቱ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም፣ ከምሥረታው አንስቶ የካበተ ምሁራዊ ጥሪትና የታላላቅ ልሂቃን እርሾ ባይኖረው ኖሮ፣ እንደ ፕሬዝዳንት አድማሱ ተግባር፣ የዳይናሶር ሲንድረም ሰለባ ይኾን ነበር፡፡
በተጨማሪም፣ ዩኒቨርሲቲው የተፈደቀለትን በጀት ሙሉ በሙሉ ባለመጠቀም፣ በየዓመቱ በርካታ ሚሊዮን ብሮችን ተመላሽ እንደሚያደርግ የታወቀ ነው፡፡ ይህም ኾኖ እያለ፣ ለዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ገቢ እየተባለ በፕሬዝዳንቱ ቢሮ ፕሮጀክት ተቀርጾ* ከበሬ ማድለብ እስከ ዕንቁላል መሸጥ፤ አልፎም የሱፐር ማርኬት የንግድ ሱቆች የማቋቋሙን ተግባር ተያይዞታል፡፡ እዚኽ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን፣ የገንዘብ እጥረት በሌለበት ኹኔታና የተፈደቀለትንም በጀት በአግባቡ ሳይጠቀም፣ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልገኛል በሚል ሰበብ፣ ከዕውቀት ጋር ባልተያያዙ ንግዶች ላይ መሰማራቱ በብዙ መልኩ ስሕተት ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ኹሌም ሊተጋበት የሚገባው፣ ነገር ግን፣ ኹሌም በምልአት የማያሳካው ዋናው የአእምሮ ጥሪትንና ጠፍታን ማካበትና ማረጋገጥ ኾኖ ሳለ፣ ባላገደደው ንግዳዊ ተልእኮ ውስጥ መሰማራቱ አስገራሚ ነው፡፡ ምናልባት፣ የመጀመሪያ ተልእኮውን (የአእምሮ ሥልጥንና) ካሟላ በኋላ ወደ ንግድ ቢገባ፣ ችግር አይኖረውም ይኾናል፡፡
በርግጥ ዩኒቨርሲቲው፣ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋራ እንደ ዩኒቨርሲቲ ሲለካ፣ ደረጃው እያሽቆለቆለ መምጣቱ ከማንም ያልተደበቀ እውነታ ቢኾንም፤ የግቢው “ግርማ ሞገሳዊ” የውጭ ገጽታ ግን፣ ኹሌም የሚደነቅና በተለያዩ ሀገራት ጎብኚዎች ጭምር የተመሰከረለት ነበር፡፡ ይህን ግርማ ሞገሱን፣ ዛሬ በፕሬዝዳንት አድማሱ ተነጥቆ ዕርቃኑን ቆሟል፡፡
የዛፉ ምንጣሮ፣ ለዩኒቨርስቲው አካላዊ መስፋፋት አማራጭ የሌለው አመክንዮ ተደርጎ በእነ ፕሬዝዳንት አድማሱ ጥቅም ተኮር አስተሳሰብ ይገለጽ ይኾናል፡፡ ከኹሉ በፊት፣ “አማራጭ የለሽ” ይሉት ይኸው ህወሓታዊ ሜታፊዝክስ(የእኛ ሐሳብ* ትክክለኛው እና ብቸኛው ነው፤ የሚል የሐሳብ ሞኖፖሊ)፣ በተለያዩ አጀንዳዎች እንዳየነው፣ አስቀድሞ የተቆረጠንና የተፈጠመን ነገር፣ ያለተገዳዳሪ ሐሳብ ለማስፈጸም የሚጠቀሙት ዘይቤ ነው፤ ፕሬዝዳንቱም፣ የዚኹ፣ “አማራጭ የለም፤” ባይ የሥርዓቱ ፍልስፍና ሰባኪና አስፈጻሚ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ በአንጻሩ፣ ዩኒቨርሲቲው፣ እንደ መካነ አእምሮ፣ የአማራጭ የለሽ ፍልስፍናን ሽሮ፣ ለተለያዩ ፕሮብሌሞች ኊልቊ መሳፍርት የሌላቸው አማራጮችን የማቅረብ ሓላፊነት አለበት፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሚፈልገው የማስፋፊያ ሥራ ሌሎች የቦታ አማራጮችን መጠየቅ ሲችል፤ ሥነ ውበትን ገርስሶ፣ የኮንስትራክሽን ጣቢያና የፎቆች ጫካ የመሰለ ትዕይንት መፍጠር ተገቢ አይደለም፡፡
የደን ምንጣሮውንና የሕንፃ ማስፋፊያውን፣ ከፕሬዝዳንቱና ከበላይ ሹሞቻቸው ሕጸጽ አኳያ በየአንጻሩ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ በዚኽ ጉዳይ ላይ፣ የዩኒቨርሲቲው ግድፈት የሚያሳየው፣ የ“ኤፒስቲሚክ” እና የ“ኤስቴቲክ” ችግርን ብቻ ሳይኾን፤ የአንድ ቢሊዮን ብር ፕሮጀክትን በ‘ካፒቴንነት’ ለማስተዳደር ከመሻት የመነጨ እንደኾነ መገመት አያስቸግርም፡፡ መቼም፣ ዜጎች ብቻ ሳይኾኑ፣ “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል” እንዲሉ፣ የአማሳኞቹ ቡድን በስም ዝርዝር ባይነገረንም፣ ስለ ሙስናው መንሰራፋት አንዳንድ የሥርዐቱ ሹመኞችም ቢኾኑ በይፋ ያመኑበት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሙስና ዕንብርት ተብለው የተለዩና ብዙዎችን ካስማሙት ቀዳሚዎቹ፡- የመሬት አስተዳደር፣ የመንገድና የሕንፃ ግንባታ፣ የገቢዎች እና ጉምሩክ አሠራር ላይ የሚታየው ምዝበራ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም፣ የአንድ ቢሊዮን ብር በጀት በተያዘለት የግንባታ ፕሮጀክት ውስጥ ሲገባ፤ በተለይ ኦዲት ተደርጎ የማያውቅ ተቋም ከመኾኑ የተነሳ፣ ምንም ዓይነት የሙስና እንቅስቃሴ በፕሮጀክቱ ላይ አይካሔድም ብሎ ማመን ተላላነት ነው፡፡
ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት አጠያያቂ በኾነበት በአኹኑ ጊዜ፤ በየትኛውም ተቋም ስላለው ሙስና ሐቁን መናገር በጣም ያስቸግራል፤ ለዚኽም ነው፣ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ፣ “ፍኖተ አእምሮ” በተሰኘው መጽሐፋቸው፡- “ነጻነትን ተከባከቧት፤ እውነት ራሷን ትጠብቃለች” ያሉት፡፡ ነጻነት በሀገራችን ገና የተደላደለ ቦታ ስላላገኘች፣ ለጊዜው እውነት ሸሸግ ብላ ለመቀመጥ ስለምትገደድ፣ እኛም፣ ስለ ሙስና ከዚኽ በላይ ለማተት ኹኔታው እንደማይፈቅድልን በመረዳት፣ የያዝነውን በልባችን እንደያዝን ሐሳባችንን በዚኹ እናሳርፋለን፡፡

No comments:

Post a Comment