Sunday, February 5, 2017

የሸዋ ነገር – ከያሬድ ጥበቡ


ባለፈው የዕድሜ ቀጥል (ፌስ ቡክ) ዝክረ ነገሬ፣ ምን ይሻላል በሚል ርዕስ በክቡር አቶ ይልማ ዴሬሳ ልሳን የኦሮሞ ህዝብን አሰፋፈርና መስፋፋት ታሪክ ከዛሬው የአዲስ አበባ የፖሊሲ ጥያቄ ጋር አዳብሌ በማቅረቤ፣ በአቶ ይልማ ታሪክ የተናደዱት አንባቢዎቼ፣ የፖሊሲዉን ሃሳብ ተገቢውን ትኩረት ስላልሰጡት በጉዳዩ ላይ ለመመለስ አሰብኩ ፡፡ በዚያውም በስልክ ላይ ቁቤን በመጠቀም የሚደረግ ትንተና ከትንኮሳ አልፎ የልብን ስለማያደርሰ፣ እስቲ ደግሞ ቀልብን ሰብሰብ አድርጎ በላፕ ታፕ መተየቡ ይሻል እንደሆን ልሞክረው በማለትም ነው በጉዳዩ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ለመመለስ መወሰኔ ፡፡
ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ወዲህ በተግባር ካዋላቸው ምሶሶ ዕምነቶቹ መሃል፣ የታሪካዊት ትግራይ ተወዳዳሪ የነበረውን የዘመናዊ ኢትዮጵያዊነት እምብርት ሆኖ የቆየውን ታሪካዊ ሸዋን መምተር፣ ማዳከም፣ መበታተን መሆኑ ዛሬ መለስ ብለን ስናየው ባለፉት 24 አመታት አልፈናቸው የመጣናቸው የፖለቲካ ሜዳዎች ወለል ብለው ይታዮናል ፡፡ ለሸዋ መመተር ዋነኛ ምክንያቱ ቀዳሚ ማንነቱ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኘቱ ነው ፡፡ ስለሆነም የመጀመሪያ የጥቃት መስመራቸው በቀዳሚ ማንነት ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለትን ህገወጥ ማድረግና፣ ከዘር በላይ የቆመ ኢትዮጵያዊነት ሊኖር አይችልም የሚለውን ቀመራቸውን ሃገራዊ ፖሊሲ አድርገው ማስፈጸም ነበር ፡፡ ሁለተኛው ርምጃቸው፣ ክልሎችን በዋና ዋና ቋንቋዎች ዙሪያ ብቻ እንዲደራጁ በማስገደድ፣ ቢያንስ ከሦስት ብሄረሰብ ሕዝቦች (ከጉራጌ፣ አማራ፣ ኦሮሞ) የተጋመደውን የታሪካዊ ሸዋ ህዝብ በሦስት ክልሎች እንዲከፋፈል በማስገደድ፣ እንደ ሸዋ ህዝብ ይዞ የቆየውን ታሪካዊ ህልውና መደምሰስ ነበር ፡፡ ሦስተኛውና በአፋጣኝ ተግባራዊ የተደረገው የሸዋን ተወላጅ ከመንግስት ቢሮክራሲው ማጽዳትና በምትኩ በትግሬ ወያኔዎች መሙላት ነበር ፡፡ አራተኛውና አስከፊው የዚሁ ሸዋን የማዳከም ፖሊሲ አካል ደግሞ፣ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን መርዳትና፣ በተለይ በታሪካዊ ሸዋና ኦሮሞ ህዝብ መሃል የእርስ በርስ መፈራራትና በአይነ ቁራኝ የመተያየት ሁኔታን በመፍጠር፣ ወያኔ በህግ አስከባሪነትና ገላጋይነት ስም ሁለቱም ሳይወዱ የሚቀበሉት ሓይል እንዲሆን የስነ ልቡና ጦርነት ማካሄድ ነው ፡፡ አዲስ አበባን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የማስገባቱም ውጥን ከዚሁ በሸዋ አማርኛና ኦሮሞኛ ተናጋሪዎች መሃል ቀጣይ ውጥረትን በመፍጠር፣ ወያኔ የሠላም ሐይል መስሎ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም መሆኑ በግልጽ ይታያል ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ተወዳዳሪ እንዲሆን ለሁለት አሥርተ አመታት በወያኔ ሲረዳ የቆየው የኦሮሞ ብሄርተኝነት፣ ዛሬ ጥርሱን የነቀለበት ዕድሜ ላይ በመድረሱ፣ በተለይ ከመለስ ሞት በኋላ ባሉት አመታት፣ የወያኔ ተገዳዳሪና ተቀናቃኝ እየሆነ በመምጣቱ፣ በማስተር ፕላኑ ዙሪያ በተቀሰቀሰው አለመግባባት እንዴት ፈጥኖ ወደንብረት ወደማና ሕይወት ማጥፋት እንደተሸጋገረ ሁላችንም ያየነው ነው ፡፡ ወያኔ ለ24 አመታት የተከተለው ፖሊሲ ውድቅ መሆኑን የሚጠቁም ይመስለኛል ፡፡ አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብ ማቅረብም ተገቢ ነው ፡፡
ከሸዋ እስቲ እንጀምር ፡፡ ከነጋሲ ዘመን ጀምሮ እስከ ምንሊክ የራሱ ንግስና ያለው በመርእድ አዝማቾች፣ አቤቶዎችና ንጉሶች ራሱን ችሎ ሲተዳደር የኖረ ህዝብ ነው የሸዋ ህዝብ ፡፡ በኦሮሞ ፍልሰትና መስፋፋት በተራሮች መሃል ተሸሽጎና፣ የኦሮሞ ፈረስ ከማይደርስበት ገደላገደል ከጭላዳና ዝንጀሮ ጋር እየታገለ መኖር የሰለቸው አማርኛ ተናጋሪ ሸዌ፣ የቅድም አያቶቹን መሬት ለማስመለስ ወደ ደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ መትመም ጀመረ ፡፡ ኦሮሞዎች ሲስፋፉ እንዳደረጉት፣ የተዋጋቸውን እየገደለ፣ ሴቱንና ሕጻኑን አማራ እያደረገ መሄድን አልመረጠም ፡፡ ትዳሩን ጎጆውን ይዞ፣ ባህሉን ቋንቋውን ይዞ ለመንግስትም ሆነ የጦር አበጋዞቹ እስከገበረ ድረስ፣ በማንነቱ ላይ መዝመት አላሰፈለገውም ፡፡ አማራ እንዲሆን አላስገደደውም ፡፡ በዘመኑ ከነበረው ጭካኔና፣ ኦሮሞው ራሱ በመስፋፋት ዘመኑ ከተጠቀመባቸው ኦሮሙማ የማድረግ ፖሊሲ በንፅፅር ሲታይ፣ እጅግ የተሻለ ነበር ፡፡ ከዚህም ተነፃፃሪ ጨዋ ባህርዩ በመነጨ የሸዋው አማራ መስፋፋት የኦሮሞ ባላባቶችን ፍቅርና ትብብር ለማግኘት የቻለ ይመስለኛል ፡፡ በእርገጠኝነት መናገር የምንችለው፣ የሸዋ ኦሮሞ ባላባቶችና የጦር አበጋዞች የራሳቸውን ነፍጠኛ ጦር በመመልመል፣ በተለይ የሸዋው ንጉስ ምንሊክ ወደደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ባደረጓቸው መስፋፋቶች፣ ቀንደኛ መሪዎቹና ዋነኞቹ የጦር አበጋዞች ኦሮሞዎቹ ራሳቸው የሆኑበትን ሁኔታ ፈጠረ ፡፡
ከዚህም የኦሮሞና የጉራጌ የጦር አበጋዞች የሸዋ ሥርወ መንግስት አድራጊ ፈጣሪ መሆን ጋር፣ ከሸዋው አማራ አሪስቶክራሲ (የገዢው ክፍል) ጋር በጋብቻ የመዛመድ፣ የመዋለድና፣ የመዋሃድ መስተጋብር ምክንያት ሆነ ፡፡ ይህም መዋሃድና ቅልቅል፣ ከዘር በላይ ማሰብ የሚችል፣ ከቋንቋ እስር የተላቀቀ ኢትዮጵያን ማለምና መመኘት የሚችል ህዝብን ፈጠረ ፡፡ በተለይ አስቀድሞ ወደ ደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ በተደረጉት ዘመቻዎች ምርኮኛ ተደርጎ የነበረው በየሸዋው ጎጆ ይገኝ የነበረው በባርነት የተያዘ ዜጋ ነፃ ሲወጣና ከአማራውና ኦሮሞው ጋር በደም ሲቀላቀል፣ የዘር ግንዱን ከአማራውም ሆነ ኦሮሞው ወይም ጉራጌው መጎተት ቁብ የማይሰጠው፣ ልዩ የሆነ ኢትዮጵያዊ አዲስ አበባን ማእከሉ አድርጎ ብቅ አለ ፡፡ በዶክተር ተኮላ ሓጎስ አንደበት ‹‹መሐል ሠፋሪ›› የሚባለው፣ ይህ ከምንሊክ እስከ መንግስቱ ሐይለማርያም ድረስ የዘመናዊ ኢትዮጵያን ቢሮክራሲ ሲያንቀሳቅስ የቆየውና፣ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በስህተት ‹‹የአማራ አገዛዝ›› ሲሰኝ የኖረው ዘመንና ሃገራዊ ሐይል ነው ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ከቅርብ አመታት ወዲህ የወያኔን መሪዎች ያነጋገሩ ነጮች፣ ከደቡቡ ጋር ያልተቀላቀሉት እውነተኞቹ ሴማውያን በትግራይ ተራሮች እቅፍ ውስጥ የኖሩት ትግሬዎች በመሆናቸው፣ በአንደኛው ምሌንየም ያስገኙትን ሥልጣኔ፣ እንደገና በሦስተኛው ምሌንየም ይደግሙት ይሆናል የሚል አመለካከት መሰማት የጀመረው ፡፡ የመለስ የሚሌንየም ንግግር ላይም ጨረፍታውን አድምጠነው ነበር ፡፡ የአዲሱ ገዢ መደብ አዲስ ጉራ መሆኑ ነው እንግዲህ ፡፡ የወያኔ ፍትሓ ነገሥት ፡፡ አንኮበር ላይ ያዘቀዘቀችው ፀሀይ አድዋ ላይ ስታሻቅብ ፡፡
ሸዋ በደርጉም ዘመን ሆነ በወያኔ አገዛዝ የጥቃት ኢላማ የተደረገው የዘመናዊት ኢትዮጵያ ማገርና ካስማ ሆኖ በመገኘቱ ነው ፡፡ የኢትዮጵያን ሥርወ መንግስት በመሳሪያ ሐይል የተቆጣጠሩት እነዚህ ሁለት ሐይሎች፣ በላቡና በደሙ አዋድዶ ያሰረከባቸውን ሃገር እያመሰገኑ እንደማስተዳደር፣ ሸዋን ካልደመሰሱ እንቅልፍ የማይወስዳቸው መስሎ ተሰማቸው ፡፡ለዚህም ደርጉ በ45 እና በ75 እድሜ ክልል ያሉትን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ባለሥልጣናት ሲፈጅ፣ ትኩረቱ ከሸዋ በመነጩት ላይ መሆኑ የአጋጣሚ ከቶ ሊሆን አይችልም ፡፡ ወያኔም ቢሮክራሲውን ሲያፀዳም ሆነ፣ በመአህድ ሰበብ ፍጅት ሲያካሂድ፣ ወይም አዲስ በፈጠረው የአማራ ክልል የሸዋ ሰው ዝር እንዳይልና፣ ክልሉንም በአመዛኙ በሰቆጣ አገዎች አፍኖ ሲይዘው፣ ሸዋን በማግለል ፖሊሲ የተጨማለቀ ለመሆኑ ዛሬ ይበልጥ ግልጽ ሆኖ ይታየናል ፡፡

No comments:

Post a Comment