Thursday, February 2, 2017

የአዲስ አበባ ሥራ አጥ ወጣቶችን የማባበል ዘመቻ በይፋ ተጀመረ


  • መንግሥት “ጥያቄያችሁ ተሰምቷል” የሚል ማስታወቂያ እያስነገረ ነው
ዋዜማ ራዲዮ- ከትናንት ማለዳ ጀምሮ በእድር ጡሩንባ ጭምር በመታገዝ የአዲስ አበባ ወጣቶች በነቂስ ወጥተው ለሥራ እንዲመዘገቡ ቅስቀሳ ማድረግ ተጀምሯል፡፡ ይሁንና ምዝገባው ላለፉት ጥቂት ወራት ዉስጥ ዉስጡን ሲካሄድ የቆየ እንደነበር የገለጹ አስተያየት ሰጪዎች እንዲህ በይፋና በዘመቻ መልክ በከፍተኛ ቅስቀሳ ታጅቦ ሲካሄድ ግን የመጀመርያው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከትናንት ጀምሮ በወረዳዎች የሚገኙ የወጣት ማእከላት በባንዲራና በመፈክር አሸብርቀው ታይተዋል፡፡
እስከዛሬ ይፋ ባልሆነ መንገድ ሲካሄድ የነበረው ምዝገባ የሚፈለገውን ያህል ወጣት ተመዝጋቢ ሊያስገኝ እንዳልቻለ ይነገራል፡፡ ፈቃደኛ ተመዝጋቢዎቹም እንደታሰበው ከኢህኤደግ ቁጥጥር የራቁ አዳዲስ ወጣቶች ሳይሆኑ ቀድሞም የወጣት ሊግ አባላት የነበሩ፣ በወረዳዎች መዋቅር ዉስጥ የተሰገሰጉ መሆናቸው ምዝገባው በአዲስ መንፈስ በመስተዳደሩ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኩል በተሟሟቀ ሁኔታ እንዲካሄድ አስገድዷል፡፡
መንግሥት የወጣቶቹን ጥያቄ ሰምቶ ሥራ ሊሰጣቸው አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የሚገልጸው ይህን ክፍት የሥራ  ማስታወቂያ መስተዳደሩ ሁሉንም የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች ተጠቅሞ እያስነገረ ነው፡፡ ከተለመዱ የማስታወቂ ዘዴዎች በተጓዳኝ በእድሮች በኩል፣ በኮንዶሚንየም የነዋሪዎች ማኅበራት፣ እንዲሁም የወረዳና የክፍለ ከተማ ኃላፊዎች የሚይዟቸው ማዝዳ ፒክ አፕ መኪናዎችን ጭምር በመዋስ በሀሎ ሀሎ ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡ የተንቀሳቃሽ ድምጽ ማስታወቂያዎች በከተማው እምብዛምም አገልግሎት መስጠት ባቁሙበት በዚህ ወቅት ጆሮ በሚበጥሱ ሞንታርቦዎች አዲስ ዘመቻ መከፈቱ ነዋሪዎችን አስገርሟል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት በተጓደሉ የክፍለ ከተማ የይዞታ አስተዳደር ቢሮ ክፍት ቦታዎች ወጣቶች ብቻ እንዲቀጠሩ ትእዛዝ ወርዶ እንደነበር የዋዜማ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ 10 ዓመት የሥራ ልምድ ለሚፈልጉ ቦታዎች ሳይቀር “አዲስ የተመረቁ ወጣቶችን ቅጠሩ፣ እየሰሩ ይለምዳሉ” ተብለናል ይላል ለዋዜማ ሀሳቡን ያጋራ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ባለሞያ፡፡
አሁን በአዲስ መንፈስ የተጀመረው የሥራ ተመዝገቡ ቅስቀሳ ያልተለመደና ሥራው ምን እንደሆነ በዉል ያልተገለጸበት ነው፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቂርቆስ የገበያ ማዕከል መግቢያ አካባቢ አይሱዙ ላይ በተሰቀለ ድምጽ ማጉያ የባህል ልብስ የለበሱ ወጣት ተወዛዋዦች የመኪና ጭነት ላይ ቆመው ከበሮ እየደለቁ የአካባቢው ወጣቶች ለሥራ ፈጥነው እንዲመዘገቡ እየቀሰቀሱ ታይተዋል፡፡ በርካታ ነዋሪዎቹ ምን መጣ በሚል ከያሉበት ወጥተው ክስተቱ በአግራሞት እየተመለከቱ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የድምጽ ማጉያ ግዙፍ ሞንታርቦዎች የተገጠሙላቸው ለጽሕፈት ቤትና ለወረዳ ሥራ አስፈጻሚ ሹማምንት ታድለው የነበሩ ወርቃማ ቀለም የተቀቡ መኪናዎች በዋና ዋና ጎዳናዎች እየተዟዟሩ የምሥራች እየለፈፉ ሲሆን በየመሐሉ ለወጣቶች የሚስማሙ ሙዚቃዎች በዲጄዎች እየተለቀቁ ነበር፡፡
ትናንት ረፋድ ላይ የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድን የሚወክል ባነር የለጠፈ አንድ ነጭ ማዝዳ ፒክ አፕ ተሸከርካሪ ‹‹መጪው ጊዜ የወጣቶች ነው፣ ኢንቨስተር ወጣቶችን በአጭር ጊዜ እንፈጥራለን›› የሚል መፈክር ለጥፎ በቅስቀሳ ላይ ታይቷል፡፡ ይኸው ተሸከርካሪ በተለምዶ ተረት ሰፈር በሚባለው አካባቢ በመዘዋወር ‹‹የምሥራች ወጣት ሥራ አጥ ለሆናችሁ የወረዳችን ነዋሪዎች፣ በመጨረሻም ጥያቄያችሁ ተሰምቷል…” የሚል አስገራሚ ቅስቀሳ ሲያደርግም ነበር፡፡
ማስታወቂያው በዋናነት ሁሉም ሥራ አጥ ወጣቶች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የወጣት ማዕከል በመሄድ አልያም ቤት ለቤት ምዝገባ ለማካሄድ ለሚመጡ ሠራተኞች መረጃ በመስጠት ቀና ትብብር እንዲያደርጉ የሚለማመን እንጂ የሥራውን አይነት የለየ አይደለም፡፡
በከተማዋ ሁሉም የኤፍ ኤም ጣቢያዎች ከማለዳ ጀምሮ በተደጋጋሚ ያለ ክፍያ እንዲተላልፍ በተደረገ ተመሳሳይ የሬዲዮ ማስታወቂያ ደግሞ መስተዳደሩ ሥራ ለመስራት ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችን እየመዘገበ እንደሚገኝ ከገለጸ በኋላ መስፈርቶቹን ይዘረዝራል፡፡ እድሜው ከ18 በላይ የሆነ (የሆነች)፣ የቀበሌ መታወቂያ ያለው ወይም ያላት፣ በየትኛውም መሥሪያ ቤት ከዚህ በፊት ያልተቀጠረ (ያልተቀጠረች)፣ ሥራ አጥ ስለመሆኑ (ስለመሆኗ) ማረጋገጥ የሚችል (የምትችል)…እያለ የሚቀጥል ይዘት አለው፡፡
ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ተከትሎ ርዕሰ ብሔሩ የሁለቱን ምክር ቤቶች አዲስ የሥራ ዘመን ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር መንግሥት ለዘነጋቸው ሥራ አጥ ወጣቶች ልዩ ተዘዋዋሪ ፈንድ እንደሚዘጋጅ ቃል ከገቡ ወዲህ አብዛኛዎቹ ክልሎች ከፍተኛ ገንዘብ ለወጣቶች ሥራ በሚል ለመመደብ ተገደዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል 7 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለወጣቶች ሲመድብ፣ አማራ ክልል 3 ቢሊየን፣ የትግራይ ክልል በበኩሉ 2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለተመሳሳይ ዓላማ መድበዋል፡፡
ገንዘቡ እንዲሰጥ የታሰበው ወጣቶች አንድ ለአምስት ከተደራጁ በኋላ ሊሰሩ ያሰቡትን ሥራ በማስረዳት ብቻ ያለምንም የባንክ ማስያዣ (collateral) ገንዘቡ ፈሰስ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ የእሳት ማጥፋት ዘመቻ መልሶ ፓርቲውን እንሚያንኮታኩተው የሚተነብዩ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ገንዘቡ ሲለቀቅ ሌላ ጦስ ይዞ እንደሚመጣ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡
መንግሥት ለዚህ ዓመት ከያዘው 275 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ያልተካተተ የወጣቶች ፈንድ ሌላ 10 ቢሊዮን ብር ሲታከልበት፣ ለሠራተኛ የደሞወዝ ጭማሪ የሚያስፈልገውን ወጪ ጨምሮ ሁኔታው ብሔራዊ ባንክ ብር እንዲያትም ሊያስገድደው እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ይህ መጠን ያለው ገንዘብ አሁን ባለው የገንዘብ ዝውውር ላይ ሲረጭ ለኢኮኖሚው ግሽበትን የሚያስከትል መርዝ ሊሆንበት እንደሚችልና አገሪቱ ከዚህ ወዲህ ወደ ግሽበት ከገባች ደግሞ መውጫው ቀላል እንደማይሆን ይገምታሉ፡፡
እስከዛሬ ለወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተበተነው ገንዘብ ያመጣው ለውጥ አለመኖሩን የሚያትቱ ሌሎች ባለሞያዎች በበኩላቸው የገንዘብ አቅርቦት ብቻ ስላገኙ ራሳቸውን የለወጡ ወጣቶች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው የወሰዱትን ብድር ሳይመልሱ ጠፍተው የቀሩ እንደሚበዙበት አስረድተዋል፡፡
አምስት ወጣቶች ገንዘብ ስለተሰጣቸው ብቻ ሕይወታቸው ላይ ተአምር ይፈጥራሉ ብሎ ማሰብ አስቂኝ እንደሆነ የሚናገሩ  በርካቶች ናቸው፡፡ “ሥራ ፈጠራ ከገንዘብ አቅርቦት የበለጠ ክህሎት፣ ልምድና ተነሳሽነትን የሚፈልግ ነው፡፡” በሚል አስተያየቱን ያካፈለ በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዉስጥ ባልደረባ የነበረ የኢኮኖሚ ባለሞያ “ለኔ የሚገባኝ መንግሥት አጣብቂኝ ዉስጥ መግባቱን ብቻ ነው” ይላል፡፡
ባለሞያው “ሥራ አጥነት ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ በዚች አገር ስለተፈጠረ የመጣ ችግር እንዳልሆነ” ካብራራ በኋላ ችግሩ የሁሉም ታዳጊ አገራት ራስ ምታት ቢኾንም ልዩነቱ የሚመጣው ችግሩን በሚፈቱበት ስልት ላይ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
የአረብ ፀደይን ተከትሎ አንዳንድ አረብ አገራት ለወጣቶቻቸው ገንዘብ በመበተን ጊዝያዊ መተንፈሻ ለማግኘት እንደሞከሩና የተወሰኑት እንደተሳካላቸው ያስታወሰው ይኸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያ የኢህአዴግ መንግሥትም አማራጭ በማጣት ተመሳሳይ ስሌት ዉስጥ ገብቷል ብሎ እንደሚያምን ይገልጻል፡፡
ባለሞያው ጨምሮ እንዳብራራው መንግሥት አሁን ሊሄድበት የሞከረው መንገድ ራስን በገመድ ጠልፎ ከመጣል እንደማይተናነስ ያብራራል፡፡ ከዚያ ይልቅ ዘላቂነት ያለው በርካታ ወጣቶችን መቅጠር የሚችለውን የግል ዘርፉን ማገዝ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ቢያደርግ  አገሪቷን ወደተስፋ ሊመልሳት እድል ነበረው ብሎ ያምናል፡፡
በኛ አይነቱ ልል ኢኮኖሚ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በጥድፊያና በአንድ ጊዜ ፈሰስ የሚደረግ ፈንድ የምጣኔ ሐብት ቧልት (Farce in a ridiculous economy) ኾኖ እንደሚሰማው አስታውሶ “ኢህአዴግ ይህ ይጠፋዋል ብዬ ግን አላምንም፤  ምናልባት ፋታ እንኳ ባገኝ በሚል እየገባበት ያለ ትብታብ ሊሆን ይችላል” ሲል ሀሳቡን ይቋጫል፡፡
በተያያዘ ዜና ከወጣቶች ሥራ ፈጠራ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ግራና ቀኝ የመኪና ማቆምያ ክፍያ ተመን በእጥፍ እንዲጨምርና ከክፍያ ነጻ የኾኑ ጎዳናዎች ሁሉ ተለይተው ለወጣቶች ገቢ እንዲያስገኙ መንገዶቹን የመለየት ሥራ እንደሚሰራ ተመልክቷል፡፡ አሁን በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ የመኪና ማቆምያ ማማዎች ሲጠናቀቁም የተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዲያስተዳድሯቸው  ይደረጋልም ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከሁለት መቶ ሺ ያላነሱ ሥራ አጥ ምሩቃን እንደሚገኙ ይገመታል፡፡

No comments:

Post a Comment