የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ በፋሽስቱና በተስፋፊው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ቡድን የተፈጸመበትን የዘር ማፅዳትና በትግሪያዊነት የመተካት እኩይ ወንጀል ለመመከትና ለመቀልበስ እንዲሁም በመጥፋት ላይ የሚገኘውን ዘሩን ከፈፅሞ ጥፋት ለማዳን ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ሲያደርግ የኖረውን ህዝባዊ ተጋድሎ በወልቃይት ህዝብ አማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ አማካኝነት የካቲት 24, 2008 ዓ.ም ጎንደር ከተማ “ላንድ ማርክ” አዳራሽ ውስጥ በተጠራ ታሪካዊና ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ለጎንደር ህዝብ የሃገር ሽማግሌዎችና ተወካዮች ትግሉን በይፋ ማስረከቡ ይታወቃል።ይልቁንም ይህን ታሪካዊ የትግል ቅብብሎሽ ከሃምሌ 5, 2008 ዓ.ም ጀምሮ እዛው ጎንደር ከተማ ላይ በተከፈለው ታላቅ ህዝባዊ መስዋዕትነት የጎንደር ህዝብ ስለወልቃይት የገባውን ቃልኪዳን በደሙ አፅንቶና አትሞት ያለፈ ሲሆን። ይህ ጎንደር ላይ በንፁሃን ወገኖቻችን ደም የታሰረው ታሪካዊ ውል፤ በቆራጥ የአማራ ህዝብ ልጆች ውድ የህይዎት መስዋዕትነት የፀና፣ መላውን ኢትዮጵያዊ በደም ካሳ ያስተሳሰረና፣ ወጣቱን ትውልድ ከወልቃይት ህዝብ ትግል ጋር በማይጠፋ ቃልኪዳን ያቆራኘ የህዝባችን ለዘመናት ያደረገው ትግል ታላቁ ድልና ስኬት ሆኖ አግኝተነዋል።
የወልቃይት ህዝብ የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ ማለት የጎንደር ህዝብ “ድንበራችን ተከዜ ነው!” እያለ ደሙን እንደ ጅረት ያፈሰሰለት፣ የጎጃም ወጣት “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!” እያለ ምድሪቱን በደሙ ያጨቀየለት ፣ የኦሮሞ ኤጆሌ “ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ይፈታ!” በማለት ከነህይወቱ በቢሾፍቱ ገደል በግፍ የተወረወረለት፣ ኢትዮጵያዊና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ በአንድነት “የንጹሃን ወገኖቻችን ደም በግፍ ማፍሰስ ይቁም!” “ወልቃይት አማራ ነው!” እያሉ በዓለም ታላላቅ አደባባዮች ቀን ከሌሊት፣ ክረምት ከበጋ የተሰለፉለትና የጮሁለት፣ በአጠቃላይ ህዝባችን በአንድነትና በህብረት ሆኖ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የታገለለትና መስዋዕትነት የከፈለለት የኢትዮጵያውያን ሁሉ ተቀዳሚ አጀንዳ፣ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ግንባር ቀደም ጥያቄ ነው!
ይህን ህዝባዊ ጥያቄ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ህዝብ በአደባባይ በጠየቀው መሰረት መመልስ የነገውን ህዝባዊ ቁጣና ቅጣት አሻግሮ መመልከትና ከታሪክ መማር የሚችል የማንኛውም አካል ተቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ልሳነ ግፉዓን ድርጅት በፅኑ ያምናል። ነገር ግን ከጅምሩ የኢትዮጵያና የህዝቧ ጠላት ሆኖ የተነሳው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ቡድን ይህን ሃገርንና ትውልድን ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ያሰለፈና ያስቆጣ ህዝባዊ ጥያቄ በሰላማዊና አግባብነት ባለው ህጋዊ መንገድ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በተቃራኒውና በተለመደው ፋሽስታዊ የሃይልና የጭካኔ መንገድ የህዝብ መሪዎችንና ተወካዮችን በጀምላ በማሰር፣ በተለያዩ የማሰቃያ ዘዴዎች በማሰቃየትና፣ በማሳደድ ለማንበርከክ መሞከርና በአላማቸው እስከ መጨረሻው የፀኑትንና በመራር ስቃይ ውስጥ ሆነው እንኳ ያልተንበረከኩትን ትንታግ የህዝብ ልጆች በግፍ በመግደልና አስከሬናቸውን በገበያ መካከል በመጎተት ህዝብን ለማሸበር መጣርና እስከ የማይቀረው ውድቀት ድረስ አጥፍቶ በመጥፋት ለመግዛት መሞከርን ነው።
ከላይ በአጭሩ እንደተገለፀው የወልቃይት አማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ ከህዝብ የተቀበለውን ታላቅ ተልዕኮና የትውልድ አደራ ለጎንደር፣ ለአማራና፣ ብሎም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እጅግ በተሳካ፣ ታሪካዊ ደረጃውንና፣ ሂድቱን በጠበቀ ሁኔታ ህዝባዊ ትግሉን አስረክቧልና ምንም አይነት ኢፍትሃዊ የጭካኔና የአፈና መንገድ በህዝባችን ላይ ቢተገበር ትግሉን ሊያጎለብተው እንጂ ሊቀለብሰውም ሆነ ሊያዳፍነው እንደማይችል የኢትዮጵያ ህዝብ የትግል ታሪክ ህያው ምስክር ነው።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በተደጋጋሚ የሚያስተላልፈውን የቁጣ መልዕክት ዛሬም ድረስ በሃይል እጨፈልቃለሁ የሚለው ፋሽስቱና አጥፍቶ ጠፊው የህወሃት እኩይ ቡድን እንደለመደው ሁሉ ዛሬም ህዝብን ወደ ባሰ ቁጣና ተቃውሞ የሚያስገባ ሌላ ተልካሻ ሴራ ውስጥ ተወሽቆ ሲንቦጫረቅ እንደሚውል በተጨባጭ መረጃ ለማረጋገጥ ችለናል። ይኸውም ፦
1ኛ. ሃሰተኛ የወልቃይት አማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ ማቋቋም
ህወሃት እንደ ለመደው በአንድ በኩል እውነተኛ የህዝብ ወኪሎችንና መሪዎችን በግፍ በማሰር እያሰቃየና በሽብር ወንጀል በመክሰስ በህግ ሽፋን ሞትና እድሜ ልክ እስራት ለማስፈረድ የተበላበትን የ“አኬልዳማ ክፍል …” ድራማ ላይ እየተወነ፤ በሌላ በኩል ለጊዚያዊ ጥቅም ባደሩና በተለያዩ ህወሃታዊ የማንበርከኪያ ወጥመዶች ተጠልፈው ለህወሃት ርካሽ የጥፋት አላማ በተንበረከኩ ደካሞችና ሆድ አደሮች ተጠቅሞ ሃሰተኛ የኮሚቴ አባላትና መሪዎች እየጠፈጠፈ መክረሙንና ህዝብን እንደ ህፃን ልጅ አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ እያለ ሲጃጃል እነሆ 25 ዓመታት እንደዋዛ አለፉ።
ትላንት በሌሎች እንዳየነው ሁሉ ዛሬ ደግሞ ተረኛ ሁኖ የተገኘው “የወልቃይት አማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ” አቅራቢ ኮሚቴ ነው። ምንም እንኳ የወልቃይት ህዝብ እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ በመሆን ከ 50 ሺ በላይ የህዝብ ፊርማ በማሰባሰብ “ትግሬ ሁን የተባልኩትና ወደ ትግራይ ክልል የተካለልኩት ያለአግባብ በሃይል ነው” “የአማራዊ ብሔርተኝነት ማንነቴ ይከበርልኝ!” “ድንበሬ ተከዜ ነው!” በማለት ጥያቄውንና ውክልናውን ለመረጣቸው ወኪሎቹ ከነ ሙሉ ፊርማው በመስጠት በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ምላሹ ግድያና እስራት ስለሆነ ዛሬም እምነቱንና ቃሉን ጠብቆ በፅናት ከወኪሎቹ ጋር በመቆም መራራውንና አስከፊውን ትግል እያደረገ ይገኛል።
ይህ ህዝባዊ ፅናትና ቁርጠኝነት ያርበተበተው ፋሽስቱ ህወሃት ዛሬም እንደ ትላንቱ ታማኝ ተላላኪዎቹንና አንዳንድ ለሆዳቸው ያደሩ ተንበርካኪዎችን በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር በማፈላለግ ለማሰባሰብና ሃሰተኛ የወልቃይት አማራ ብሔርተኝነት የማንነት ኮሚቴ ለማቋቋም እየዳከረ እንደሚገኝ በተጨባጭ ደርሰንበታል።
ለዚህም ርካሽ ተግባር ተባባሪ ሆነው የተገኙት የሃሰተኛው የወልቃይት አማራ ብሔርተኝነት የማንነት ኮሚቴ አባላት ሁለት አበይት ተልዕኮ የተዘጋጀላቸው ሲሆን እርሱም ፦
- በወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ መነሻነት በሃገሪቱ ለተከሰተው አለመረጋጋትና ለደረሰው ሃገራዊ ኪሳራና ለጠፋው የሰው ህይወት ሁሉ በወልቃይት ህዝብ ስም መንግስትን ይቅርታ መጠየቅና፣
- በወልቃይት ህዝብ ስም “የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄን” እንደ አዲስ ለትግራይ ክልል መንግስት አስተዳደር ማቅረብና የትግራይ ክልል በሚሰጠው “የራስ ገዝ” አስተዳደር ተስማምቶ ዳግም ወልቃይትን በህጋዊነት ሽፋን ከነዋሪው 90% ለሚሆነው የትግሬ ሰፋሪ ወልቃይትን በሃስተኛው ኮሚቴ ፊርማ ማስረከብን መዳረሻው ያደረገ እኩይ እቅድ ነው።
2ኛ. በእስር ላይ በሚገኘው የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ አባላት ላይ የሃሰት ምስክር አቅርቦ ማስመስከርና ማስፈረድ።
የወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ አቅራቢ ኮሚቴ ሰላማዊና ህጋዊ አባላትንና የህዝብ መሪዎችን በግፍ አስሮ ማሰቃየትና በሃሰተኛው የካንጋሮ ፍርድ ቤት ውስጥ በሚሰራ የተለመደ ተራ ድራማ በሞትና በእድሜ ልክ እስራት ለመቅጣት መሞከር ማለት የኢትዮጵያን ህዝብ “ጥፋተኛ ነኝ በጥልቅ እታደሳለሁና ጊዜ ስጡኝ” ያስለመነ፣ 100% ተመርጫለሁ ባለ በአመቱ 100% ካቢኔውን በአዲስ ለመተካትና፣ ሃገራችን በታሪኳ አይታው በማታውቀው ሁኔታ ከ6 ወር በላይ ለሆነና መቋጫው በማይታወቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በወታደራዊ አገዛዝ ስር እንድትወድቅ ያስገደደን ህዝባዊ ጥያቄና ቁጣ ላይ በመንግስት ደረጃ መሳለቅና በቀጣይ ከሚመጣው ህዝባዊ ቁጣ መውጫ ቀዳዳ እንዳይኖር አድርጎ በእራስ ላይና ቆሜለታለሁ በሚሉት ህዝብ ላይ አርማጌዶን እንደማወጅ ይቆጠራል።
በአንፃሩ ደግሞ በ200 ሺ ብር የገንዘብ ክፍያና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ተደልለው በወልቃይት የአማራ ብሔርተኝነት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላት ላይ ለመመስከር በህወሃት የተዘጋጁት
1ኛ. አቶ መኮንን ጋረድ
2ኛ. አቶ ሰጠኝ ለማ ገሪማ
3ኛ. አቶ ተገን መርሻ
4ኛ. አቶ ፀጋይ ሙሉ
መሆናቸውን በተጨባጭ መረጃ አረጋግጠናል። ሌሎች በድርድር ላይ ያሉትንም እንደ ሚወስዱት አቋም ተከታትለን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን።
ይልቁንስ ቀልዱን ለጊዜው እዚህ ላይ አቁሙትና በህግ ሽፋን በግፍ ታፍነውና በየማሰቃያ ቤቱ እየተሰቃዩ የሚገኙ የህዝብ ልጆችን ማለትም፦
ሀ) አዲስ አበባ ላይ የታፈኑ ለ) ጎንደር ላይ የታፈኑ
1ኛ. አቶ ነጋ ባንቲሁን 1ኛ. አቶ አታላይ ዛፌ
2ኛ. አቶ አዲሱ ሰረበ 2ኛ. አቶ አለነ ሻማ
3ኛ. አቶ ጌታቸው አደመ
4ኛ. አቶ መብራቱ ጌታሁን
5ኛ. ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ
6ኛ. ወጣት ንግስት ይርጋ
7ኛ. አቶ ክንድሺ ሃጎስ …..ወዘተ………
ሐ) በወልቃይትና አካባቢው ታፍነው ሁመራ በእስር ላይ የሚገኙ
1ኛ. አቶ አሊጋዝ አየለ 7ኛ. አቶ ሰጠኝ ድረስ
2ኛ. አቶ ሞላ ሃይሉ 8ኛ. አቶ ባየው ካሰኝ
…
3ኛ. አቶ ሰለሞን ግዛቴ 9ኛ. አቶ ሰጠኝ አረሩ
4ኛ. አቶ አሻግረው ገዛሃኝ 10ኛ. አቶ መሐመድ ያሲን
5ኛ. አቶ ግዛቸው ድረስ 11ኛ. አቶ መኮነን ደስታ
6ኛ. አቶ ጎይቶም አማረ 12ኛ. አቶ ሊላይ ብርሃኔ….ወዘተ……
እንዲሁም በዚህ ዝርዝር ውስጥ ልናካትታቸው ያልቻልናቸውን የወልቃይት ተወላጆች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና ወደ ቤተሰቦቻቸውና ህዝባቸው እንዲቀላቀሉ እናሳስባለን።
በመጨረሻም ልሳነ ግፉዓን ድርጅት በአንክሮ ማሳሰብና ማስገንዘብ የሚፈልገው ነገር ቢኖር የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት በወልቃይት ህዝብ ላይ የፈፀመው ግፍና ያደረሰው መከራ የንጹሃንን መገፋት በሚያየውና በእውነተኛው ዳኛና ፈራጅ በሆነው በሃያሉ በእግዚአብሄር ፊት ፅዋው ሞልቶ ነበርና ህዝባችን ለዘመናት ዘሩን ከጥፋት ለማዳን ያደረገው ፍትሃዊ ትግል በሃምሌ 5, 2008 ዓ.ም ጎንደር ከተማ ላይ በተደረገው ታላቅ መስዋዕትነት ምክንያት በተቀጣጠለው የአማራ አናብስት ቁጣና ተጋድሎ የሚገባውን ታሪካዊ ክብሩንና ቦታውን ሊይዝ ችሏል። ስለሆነም ከዚያች ታሪካዊ እለት ጀምሮ የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ከወልቃይት ህዝብ እጅ ሊወጣ ችሏል። የወልቃይት ጥያቄ ከኮሚቴዎችና ከፍትህ ተቋማት እጅ ላይመልስ አፍትልኳል። ይልቁንም የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ የአደባባይ ጥያቄና የቀጣዩ ትውልድ የትግል አጀንዳ ወደ መሆን ተሸጋግሯል። እዚህ ላይ ከአዲስ አበባ የማስፋፋት ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ወጣቶች ያነሱትን የአደባባይ ጥያቄና ተቃውሞ እንዲሁም ህወሃት መራሹ መንግስት ለጥያቄው በአደባባይ የሰጠውን ምላሽ ልብ ይሏል።
ስለዚህ ለህዝባችን ጥያቄ መፍትሄው አንድና አንድ ብቻ ነው ብሎ ልሳነ ግፉዓን ድርጅት ብፅኑ ያምናል። ይኋውም የተለመደውን ተራ ቀልድና ድራማ በአስቸኳይ አቁሞ ህዝብ ከኮሚቴ ጥያቄ ወደ አደባባይ ትግል ያሸጋገረውን የአደባባይ ጥያቄ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአደባባይ ፍትህ መመለስ ብቻ ነው።
ጀግናውና ብርቱው ህዝባችን ሆይ! ለዘመናት ልጆችህን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ገብረህ የተጓዝክበት ትግል ዛሬ የጠላትህን የጣረሞት ጩሃት ለመስማት አብቅቶሃልና ደስ ሊልህ ይገባል። ነገር ግን ይህ ወደ ማይቀርለት ታሪካዊ ሞቱ በውርደት እየተሸኘ ያለው ፍሽስት ቡድን አጫፋሪና ፍርፋሪ ለቃሚ የነበሩት ጥቂት ግለሰቦች ሞቱ የተረጋገጠውን ህወሃት ለማዳን የመጨረሻ እድላቸውን ለመሞከር በሚል እላይ ታች መንቀዥቀዣቸውን ተያይዘውታል። ህወሃት ግን ከቶ ላይመለስ ሞቷልና የባንዳዎችን ልፈፋና ድለላ ሰምተህ ከድሉ ማዕድ ፊትህን እንዳትመልስ አደራ እንላለን! ይልቁንም አንድነትህን አጠናክረህና ሃያሉ ክንድህን አስተባብረህ የጠላትህ ግብአተ ፍፃሜ ላይ ተረባረብ!
ለህዝባችን ሃይል ፅናት የሆነውን ሃያሉን እግዚአብሄርን እናመሰግናለን!
ድል የህዝብ ነው!
ልሳነ ግፉዓን ድርጅት
ጥር 17, 2009 ዓ.ም