Tuesday, September 20, 2016

” ስልጠናው ከመምህርነት ሙያ ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ፋይዳ የሌለው ፖለቲካ ነው፡፡ ” የግል ት/ቤት መምህራን


ስልጠናውን ለመካፈል ከመንግስት ት/ቤት የሄዱ መምህራን በቀን ለአበል 150 ብር ለሻይ ቡና ደግሞ 20 ብር፣ በድምሩ 170 ብር እየተከፈላቸው ስልጠናውን በመውሰድ ላይ ናቸው
የግል ት/ቤት መምህራን ስልጠናው ከሙያቸው ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ከመሆኑም በላይ ለመንግስት ት/ቤቶች መምህራን የሚሰጠው የአበል ክፍያ የማይታሰብላቸው በመሆኑ ስልጠናውን አንካፈልም በማለት ጥለው ወጥተዋል ተብሏል፡፡ “ስልጠናው ባይኖርም ሥራ ላይ መሆናችሁ አይቀርም ነበር፡፡ ስለዚህም አበል ሊከፈላችሁ አይገባም” መባላቸውን የሚናገሩት መምህራኑ፤ ከሥራችን ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ስልጠና ለመውሰድ አዳራሽ ውስጥ ቁጭ ብለን ከምንውል መደበኛ ሥራችንን ብንጀምር ይሻለናል፡፡ ይህ ስልጠና ከመደበኛ ስራችን ውጪ በመሆኑ ተገቢውን የአበል ክፍያ ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡ በአንድ ህግና መንግስት በምትተዳደር አገር ላይ ሆነን አንድ አይነት ስልጠና ለመውሰድ እየተጠራን የግል ት/ቤት መምህራን በመሆናችሁ ስልጠናውን የምንሰጣችሁ ያለ አበል ክፍያ ነው መባሉ ህጋዊ ተግባር አይደለም” ሲሉም ተችተዋል፡፡
በስልጠናው ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀው ከስልጠናው አዳራሽ ከወጡት መምህራን መካከል ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ መምህር፤ “የስልጠናው ዋንኛ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው የፌደራሊዝም ጉዳይ ከመምህርነት ሙያ ጋር ፈፅሞ የማይገናኝና ለመምህራኑ አቅም ግንባታም ሆነ ክህሎት ማሣደጊያ አንዳችም ፋይዳ የሌለው ፖለቲካ ነው፡፡ ለአመታት በመምህራኑ ውስጥ ሲነሳ የቆየውን የፈቃድ አሰጣጥ ጉዳይ አጀንዳ አድርገው ያቀረቡትም ይህንኑ ፓለቲካዊ ይዘት ያለውን የፌደራሊዝም ጉዳይ ለመሸፈን እንዲረዳ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናውን ለመካፈል ከመንግስት ት/ቤት የሄዱ መምህራን በቀን ለአበል 150 ብር ለሻይ ቡና ደግሞ 20 ብር፣ በድምሩ 170 ብር እየተከፈላቸው ስልጠናውን በመውሰድ ላይ ሲሆኑ በከተማዋ የሚገኙ አብዛኛዎቹ የግል ት/ቤት መምህራን ስልጠናውን ለመካፈል ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ተበትነዋል፡፡ መምህራኑ ይህንኑ ጥያቄአቸውን በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውንና በትናንትናው ዕለትም ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረቡ መምህራን ስልጠናውን ባለመካፈል ውሳኔያቸው የፀኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

No comments:

Post a Comment