Wednesday, September 7, 2016

በኮንሶ 60 ቤቶች ተቃጥለው ነዋሪዎች ለስደት ተደርገው በከፍተኛ መከራ ውስጥ ይገኛሉ፡፡


በኮንሶ 60 ቤቶች ተቃጥለው ነዋሪዎች ለስደት ተደርገው በከፍተኛ መከራ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ከአካባቢው ህዝብ ተነጥለው ለመንግስት ያደሩ የኮንሶ ካድሬዎች በታጣቂ ኃይል ታግዘው አባሮባ ቀበሌ አማራ መንደር 60 ቤቶችን አቃጥለው ነዋሪዎቹ ለስደት መዳረጋቸውንና በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ዜጎች ቤት በተቃጠለበት ወቅት ድርጊቱን የተቃወመው አቶ አያኖ ሃልገዮ ተገድሏል፡፡
ቤታቸው የተቃጠለባቸው ነዋሪዎች ማለያ ሰገን ት/ቤት እና በጃርሶ ቀበሌ ‹‹ ሞራ›› (ሞራ- በኮንሶ ብሄረሰብ የመንገደኛ ማረፊያ ነው) ውስጥ ሰፍረው እንደሚገኙና የአካባቢው ነዋሪዎች የተቻላቸውን ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም ከአቅማቸው በላ በመሆኑ በተለይ እናቶች፣ ህጻናትና አረጋዊያን ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ፣የአካባቢው ምንጮች በከፍተኛ ሃዘን ስሜት ገልጸዋል፡፡
ይህንኑ ችግር ተከትሎ ተፈናቃዮቹ ካረፉባቸው አካባቢዎች የአገር ሽማግሌዎች ወደ አባሮባ ቀበሌ ስለሁኔታው ለመረዳትና ተፈናቃቹ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ለመጠየቅ ቢሄዱም ድርጊቱነረ በፈጸሙት ካድሬዎችና ታጣቂ ኃይሎች እንደተባረሩ የገለጹት ምንጮች ይህ በኮንሶ ህዝብ ለረጅም ጊዜ የተካሄደውን የአከላለል ጥያቄ ህዝቡን እርስ በርስ በማጋጨትና በመከፋፈል ጥያቄውን ለማፈን ፣እንዲሁም በቀጣይ በህዝቡ መካከል ያለውን ጠንካራ ማኅበራዊና ባህላዊ ትስስርና ቁርኝት ለማጥፋትና ጥርጣሬ ለመፍጠር ሆን ተብሎ የተፈጸመ የሴራ ድርጊት ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ ካድሬዎቹና ታጣቂ ኃይሉ አሁንም አካባቢውን ያለቀቁ መሆኑን ምንቾቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment