‹‹ነቀፌታን የማይቀበል መንግስት ዘላቂነት የለውም!››ድምፃችን ይሰማ መግለጫ
ሙስሊሙ 40 ዓመት የሞላውን የተቃውሞ መፈክር ዛሬም ዳግም ያነሣል!
አገር አቀፍ የተቃውሞ መርሃ ግብሮች የሚኖሩን ሲሆን ሙስሊሙ ህብረተሰብ ራሱን ዝግጁ እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን!
ቅዳሜ ነሐሴ 28/2008
ሙስሊሙ 40 ዓመት የሞላውን የተቃውሞ መፈክር ዛሬም ዳግም ያነሣል!
አገር አቀፍ የተቃውሞ መርሃ ግብሮች የሚኖሩን ሲሆን ሙስሊሙ ህብረተሰብ ራሱን ዝግጁ እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን!
ቅዳሜ ነሐሴ 28/2008
ትግላችን ከአምስት ዓመታት በፊት ሲጀመር ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎች ይዞ የተነሳ ሲሆን ጥያቄዎቹን ለማስመለስም ሰላማዊ እና ህጋዊ መንገዶችን ተከትሎ ዘልቋል። ይህም ሆኖ መንግስት ለጥያቄዎቻችን መልስ ከመመለስ ይልቅ የሀይል እርምጃ መውሰድን እና በአምባገነንነቱ መቀጠልን መርጧል። ኢትዮጵያዊው ሙስሊም በሙስሊምነቱ ብቻ ከድብደባ እስከ ቶርቸር፣ ከእስርና ስደት እስከ ሞት፣ ከቁርአንና ሂጃብ መቃጠል እስከ መስጂድ መደፈር ድረስ ጥቃት አስተናግዷል። ዛሬ ላይ ትግላችን ማዕቀፉን በማስፋት በሶስት ጥያቄዎች ሳይገደብ ብሄራዊ ጭቆናን ለመታገል እና ሙሉ መብታችንን በዘላቂነት ለማስከበር በሚል ዓላማ ቀጥሏል።
ትግላችን የአምባገነኖችን ምርኩዝ ሰብሯል!
አምባገነኖች ህዝብን ረግጠው ለመግዛት የሚጠቀሙበት ዋነኛው መሳሪያ ፍርሀትን በህዝብ ውስጥ መልቀቅ ነው። ህዝብን ከብዙ አቅጣጫ ሊያስፈራሩት ይሞክራሉ፡፡ ሞትንና አካል የሚያጎድልን ከባድ ቅጣት በመቅጣት፣ ‹‹የውጭ ጠላት መጣላችሁ›› በማለትና ህዝቡን ከፋፍሎ እርስ በርስ እንዲፈራራ በማድረግ ህዝብን ፀጥ ለጥ አድርገው ይገዛሉ፡፡ የኢህአዴግም መንግስት ወደስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በአገራችን አስፍኖት የነበረው ይህንኑ ስልት ነበር።
መንግስት በሀምሌ 2003 ግልጽ ያወጣው ቀጥተኛ የሆነ የሀይማኖት ጣልቃ ገብነት ህዝበ ሙስሊሙ ቤት ለቤት አውርቶት ወይም በጋዜጣና መጽሄት አንብቦት የሚቀር ጉዳይ አልሆነም። ፍርሀትን ሰብሮ መውጣት እና መብትን መጠየቅ ግድ ሆኖበታል። በዚህም የአምባገነኑን ስርዓት ትልቅ ምርኩዝ ዳግም ላይጠገን መስበር ችሏል። የሙስሊሙን ጥያቄ ሙስሊም ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን በጥርጣሬና በፍርሀት እንዲያዩት፣ ብሎም የመንግስትን ፍትህ አልባ እርምጃ እንዲደግፉ የሞከረ እና ሌሎችም በርካታ የፕሮፓጋንዳ ስራዎችን የሰራ ቢሆንም አንድ ጊዜ የተሰባበረ ፍርሀት ዳግም በህዝባችን ላይ ላይሰፍን ብን ብሎ ጠፍቷል። በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተቀጣጥሎ የምናየው እና ኢትዮጵያዊያን በአምባገነናዊው ስርዓት የጭካኔ እርምጃ ሳይበገሩ፣ ለንብረታቸውና ለነፍሳቸው ሳይሳሱ እያደረጉ ያለው ተጋድሎ ለዚህ ከምንም በላይ ማስረጃ መሆን ይችላል።
መንግስት ከሁለት አስርት አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ በአገራችን አስፍኖት የነበረው የፍርሀት ድባብ ተገፏል፡፡ አምባገነንነትን ያሰፈነው የፍርሀት መጋረጃ ተቀዷል። የአገሪቱ ሁለት ትላልቅ ብሄሮች (የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች) በተቃውሟቸው ሰፊ የአገሪቱን ክልል እያዳረሱ ነው። ከስህተቱ መማር የማያውቀው ስርዓት ግን አሁንም የህዝቦችን ጥያቄ ከመስማትና ከመመለስ ይልቅ በአረመኔያዊ እርምጃው ህዝባችንን በማሸማቀቅ ዳግም ፍርሀት ለማንገስ ሲማስን ይስተዋላል። የሙስሊሙን ህብረተሰብ የእምነት ተቋማት በመድፈር እና እሴቶቻችንን በማውደም በአምልኮ ቦታችን ውስጥ ሳይቀር በግፍ መግደሉን ቀጥሎበታል። ይህ ሁሉ ከንቱ ልፋት የህዝባችንን የመታገል አቋም ይበልጥ ቢያጠናክረው እንጂ ዳግም ፍርሀት በጫንቃችን ላይ ሰፍኖ ዘላቂ መብታችንን ለማስከበር ከምናደርገው ትግል እንድናፈገፍግ አያደርገንም።
የኢህአዴግ መንግስት የተነሳበትን የህዝብ ቁጣ ለመቀነስ፣ ብሎም አቅጣጫ ለማሳት የተለያዩ ሙከራዎችን አድርጓል። ራሱ ያቀነባበራቸውን ‹‹የሽብር ስራዎች›› የሚተርኩ ዶኩመንታሪዎችን ሰርቶ በመገናኛ ብዙሃን ለቋል። ጥይት ከመተኮስ አልፎ ቦንብ እስከመወርወርም ደርሷል። ታህሳስ 01/2008 በአንዋር መስጊድ በተላላኪዎቹ የቦንብ ጥቃት እንዲሰነዘር አድርጓል። ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ በምዕራብ ሀረርጌ መሰላ ወረዳ መስጊድ ላይ ቦንብ በመጣልና የእምነት ተቋማችንንም በማቃጠል ከሀያ በላይ ሙስሊሞች ገድሏል። ይህ እርምጃ ባለፉት አምስት አመታት ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ የደረሰውን በደል ከፍ የሚያደርግ እና ሙስሊሙን እና እስልምናን በተመለከተ ስርዓቱ ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ እና አቋም የሚያሳይ ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ በዛሬው እለት በቅሊንጦ ማረሚያ ቤት በተነሳ ቃጠሎ እና የተኩስ እሩምታ በርካታ ታሳሪዎች ስለመጎዳታቸው የተሰማ ቢሆንም መንግስት በጉዳዩ ላይ የተጣራ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለማጣራት የሞከሩትን በማባረርም ከአንድ ሰው ውጭ ህይወቱ ያለፈ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ በትንሹ ከ22 ሰዎች በላይ ህይወታቸው እንዳለፈ የወጡ መረጃዎች መኖር እና የመንግስትም የማጣራት እገዳ ታክሎበት አንዳች ተንኮል መኖሩ የሚያጠራጥር አይመስልም፡፡ ዜጎች በሃሰት ክስ እስር ቤቶች ገብተውም ሰላም እንደማያገኙ እስከዛሬ የነበሩት በርካታ ክስተቶች ምስክር ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ክስተት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ማእበል አማካይነት ስርዓቱ የገባበትን ጭንቀት እና ከማይወጣበት አሮንቃ ውስጥ መዘፈቁን፣ መጨረሻውም ሩቅ አለመሆኑን የሚያመላክት ሲሆን ሙስሊሙ ህብረተሰብም ከአምስት አመታት በፊት የጀመረውን ህዝባዊ እምቢተኝነት አቀጣጥሎ ለመቀጠል እንደሚገደድ ግልጽ ነው፡፡
‹‹ነቀፌታን የማይቀበል መንገግስት ዘላቂነት የለውም!››
ዛሬ በአገራችን ሙስሊሙንም ጨምሮ የተነሳው ተቃውሞ በመሸንገያ ለውጦች የሚቆም አይሆንም። ለህዝቡ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ጥያቄ በጥይትና በቦንብ ምላሽ ለመስጠት መሞከር ከንቱ ጥረት መሆኑን ስርዓቱ ሊረዳው በተገባ ነበር። ይህ አይነት እርምጃ ህዝብን ለበለጠ ቁርጠኝነት የሚያበቃ እና ከመታገል ውጭ አማራጭ እንደሌለው ግልጽ በማድረግ የሚያጠናክር እንጂ ከትግሉ እንዲያፈገፍግ አያደርገውም። ህዝባዊ ጥያቄ ተጨማሪ አፈና በማድረግ፣ ተጨማሪ የአፈና መዋቅር በመዘርጋት፣ ተጨማሪ ደም በማፍሰስ፣ ተጨማሪ የማስመሰል ለውጦች በማሳየት የሚቆም አይደለም። ጥቂት ግልገል ካድሬዎቹንና የበታች ባለስልጣናቱን ለእርድ በማቅረብ የሚገላገለውም አይሆንም። ከዚህ እውነታ በመነሳት ከዛሬ 40 አመታት በፊት ለአጼው ስርዓት መንኮታኮት በር ከፋች በነበረው እና ህዝበ ሙስሊሙ ባደረገው ትዕይንት ላይ ተሰምቶ የነበረውን መፈክር ዛሬም ላይ ለስርዓቱ እናስታውሳለን – ‹‹ነቀፌታን የማይቀበል መንግስት ዘላቂነት የለውም!››
አዎን! የህዝብን ድምፅ ማዳመጥ እና ለጥያቄው ፍትሃዊ መልስ መስጠት አንድን መንግስት ታማኝ እና ጠናካራ ያደርገዋል። በተቃራኒው የህዝብን ድምፅ አለመስማት ደካማ ያደርገዋል፡፡ የደካማ ስርዓት ማክተሚያ ደግሞ ሩቅ አይሆንም፡፡ ‹‹ብሶት የወለደው›› ኢህአዴግ ሌላ ብሶት የወለደውን ህዝባዊ ማእበል በዘላቂነት መቋቋም የሚችልበት ሁኔታ በፍጹም አይኖርም።
ህዝበ መስሊሙ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል!
የጀመርነው የዙልሂጃ ወር ትልቅ የአምልኮ ወር ነው። በዚህ ወር ለዲናቸው ሲሉ ራሳቸውን ለእሳት አሳልፈው የሰጡትን፣ ‹‹እኔ ፈጣሪ ነኝ›› ይል የነበረን አምባገናዊ ስርዓት ለብቻቸው ገጥመው የረቱትን፤ ልጃቸውን ለእርድ አቅርበው ለመሰዋት ቁርጠኛነታቸውን ያሳዩትን፣ በሰላታችን ሁልጊዜ በተሸሁድ እሳቸውን እና ቤተሰባቸውን የምናስታውሳቸውን የነብዩላህ ኢብራሂምን ታሪክ እንዘክራለን። በዚህች አላፊ ዱኒያ ላይ ስንኖር ፊት ለፊታችን የሚደቀኑብንን እንቅፋቶች ለማለፍ የሚያስችልን ታሪካዊ ክስተት በማስታወስ ለየትኛውም ኢ-ፍትሃዊ ስርዓት በማንበገርበት ወኔ እና ጽናት ራሳችንን እናንጻለን። ለሙሉ መብታችን መከበር የምናደርገውን የትግል ቁርጠኝነት እናድሳለን፡፡ ብሄራዊ ጭቆናን በዘላቂነት ለማስወገድ የምናደርገውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን። ይህንንም በተመለከተ አገር አቀፍ የተቃውሞ መርሃ ግብሮች የሚኖሩን ሲሆን ሙስሊሙ ህብረተሰብ ራሱን ዝግጁ እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በቅርቡ በምዕራብ ሀረርጌ መሰላ ወረዳ በመስጂድ ሳሉ የስርዓቱ የሽብር ሰለባ ለሆኑ ሙስሊሞች አላህ ጀነተል ፊርደውስ እንዲወፍቅልን እየለመንን ለቤተሰቦቻቸውም ጽናቱን እንመኛለን። በዚህ ዓመት የሀጅ ስርዓት ላይ ለመሳተፍ ለበቁ ሙስሊሞችም አላህ ጉዟቸውን እንዲቀበላቸው እየተመኘን ‹‹ሀጁን መብሩር!›› እንላለን።
በሁሉም የአገራችን ማዕዘናት በተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነት እየተዋደቁ ላሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ለፍትህ መዋደቅ ልዩ ክብር መሆኑን በመግለጽ ዛሬ ላይ የሚፈሱ ደሞች እና የሚከሰከሱ አጥንቶች ለነገይቱ ፍትሃዊት ኢትዮጵያ በር ከፋች በመሆናቸው ለፍትህ የምናደርገው ትግል ላይ በአንድነት ጸንተን እንድንቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment