Tuesday, September 20, 2016

የአገሪቱ ምሁራን የት ገቡ? ፍርሃት?…አድርባይነት?… ከሃላፊነት መሸሽ??


ባለፉት ጥቂት ወራት የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የተለያዩ ዕውቅ ኢትዮጵያውያንን አነጋግረን ለፖለቲካ ቀውሱ መፍትሄ ነው የሚሏቸውን ሃሳቦች ስናስተናግድ ቆይተናል፡፡
የአገሪቱ ምሁራንም በችግሮቹ ዙሪያ ሀሳባቸውን የመፍትሄ አቅጣጫ ይሰጡን ዘንድ ጥረት ብናደርግም ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ከሶስት ምሁራን ውጭ አብዛኞቹ “ትንሽ ይቆየን፤ አሁን ይለፈን” በሚል ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ ምሁራን በአገራቸው እንዲህ ያለ ፖለቲካ ቀውስ ተከስቶ፣ ለምን ራሳቸውን አገለሉ? ብዙዎች ፍርሃት ስላለባቸው ነው በሚለው ይስማማሉ፡፡
አገር በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ስትገባ፣ ምሁራን ቀዳሚ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚናገሩት ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም፤ ምሁራኑ ከማንም በፊት ለህዝብ መቆም አለባቸው ይላሉ፡፡ ችግሩ ግን በፍርሃት ተቀፍድደዋል ባይ ናቸው፡፡ በየትኛውም አገር ለህዝብ መብቶች በመታገል ጉልህ ሚና የሚጫወቱት ምሁራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ሚዲያው እንደሆኑ የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፤ ሦስቱም ግን በፍርሃት ተሸብበዋል ይላሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ፅሁፍ መምህሩ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራም የፕሮፌሰሩን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡
“ምሁሩን ከመድረኩ ያራቀው የፍርሃት ጉዳይ ነው” የሚሉት ዶ/ር በድሉ፤ “የምሁራኑ ፍራቻ የመጣው ካለፈው የደርግ ስርአት ጠባሳና ይሄም ስርአት የሀሳብ ልዩነቶችን ለማስተናገድ ስነልቦናዊ ዝግጅት ስለሚጎድለው ነው” ሲሉ ያስረዳሉ – ግድያና እስራት በራሱ በማንኛውም ሰው ላይ ፍርሃት እንደሚያመጣ በመግለፅ፡፡
“ማህበረሰቡ ተበደልኩ ብሎ ሲጮህ በብዙ ልፋት ያስተማረው የራሱ ልጅ የሆነው ምሁሩ ነው ድምፁን ማሰማት የነበረበት” ሲሉም ምሁራኑን ይወቅሳሉ፡፡ “ታሳሪ የሚበዛው አሳሳሪ ሲበዛ ነው፤ ሟች የሚበዛው አስገዳይ ሲበዛ ነው” የሚሉት ዶ/ር በድሉ፤ ‹‹ሰው ለምን ይታሰራል፤ ለምንስ ይገደላል? የሚል ምሁር መጥፋቱ አድርባይነት መንሰራፋቱን ያመላክታል ባይ ናቸው፡፡
ምሁሩ ከዚህ ፍርሃትና አድርባይነት ተላቆ ለመንግስትም ለህዝብም የሚበጁ ሃሳቦችና አስተሳሰቦችን ወደ መድረክ ይዞ መውጣት እንዳለበት ይመክራሉ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ የኢኮኖሚክስ ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤ በእንዲህ ያለ ግጭትና ተቃውሞ ወቅት የምሁሩ ሚና የላቀ ነው ይላሉ፡፡  “ምሁራን በኦሮሚያ፣ በአማራና በሌሎች ክልሎች ያለው ቀውስ መነሻው ምንድን ነው? ወጣቱ ለምን በዚህ ቀውስ ውስጥ ገባ? የማንነት ጥያቄው ምንድን ነው? ላለፉት 25 አመታት የተተገበረው ፌደራሊዝም ምን ውጤት አመጣ? የመንግስት መዋቅሩ ምን ይመስላል? የሚሉና ሌሎች ጉዳዮችን እያነሱ ምርምርና ጥናት በማድረግ፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማመላከት አለባቸው” በማለት የምሁራኑን ሚና ያብራራሉ፡፡
ምሁሩ ሚናው የሽምግልና ሣይሆን የመፍትሄ አመላካችነት ነው የሚሉት ኢኮኖሚክስቱ፤ እስከዛሬ በታየው ሂደት ምሁራን ከህዝብ መድረኮች ተገልለው መቆየታቸውና ተገቢውን ሚና አለመጫወታቸው ሃገሪቷን ብዙ አጉድሎባታል ይላሉ፡፡
ምሁራን ዝምታን የሚመርጡት ኑሮአቸው እንዳትነካባቸው ነው፤ ነገር ግን ሃገሪቱ ለከፋ ችግር ከተዳረገች የመጀመሪያ ተጠቂ የሚሆኑት እነሱ ናቸው ያሉት ዶ/ሩ፤ ምሁራን የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎችንና ችግር ፈቺ መፍትሄዎችን ማቅረብ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ምሁራን ከፍርሃታቸው ተላቀው ለመናገር ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ ምሁራኑ የመፍትሄ ሃሳቦችን ይዘው ወደ ህዝብ መድረክ እንዲወጡ ይገፋፋሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና ፖለቲከኛው ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በበኩላቸው፤ ምሁሩ ራሱን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አግልሏል ይላሉ፡፡ “ከአገሪቱ አሳሳቢ ችግር ራሱን አግልሏል፤ ለዚህም ምክንያቱ የዲሞክራሲ እጦት ነው፤ የመናገርና የመደራጀት መብቱን ለመተግበር ምሁሩ በገዢው ፓርቲ ፍራቻና ተፅዕኖ ሥር ነው” ብለዋል ኢንጂነሩ፡፡
ሆኖም በዚህ ምክንያት ምሁራን ዝምታን መምረጣቸው ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ የቀድሞው የ“አንድነት” መስራችና ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግዛቸው ያስረዳሉ፡፡ “መማር ማለት ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን የመለየት ክህሎት መላበስ ነው፤ ስለዚህ ትክክል የሆነውን ትክክል፣ ትክክል ያልሆነውን ትክክል አይደለም  ብለው በድፍረት መናገር አለባቸው” ያሉት ኢንጂነሩ፤ ኢህአዴግም ምሁራንን የማሳተፍ ባህል የለውም በማለት ገዢውን ፓርቲ ይወቅሳሉ፡፡

No comments:

Post a Comment