
ከየትኛው ዳገት ላይ ሆነን ስንጮህ ይሆን ድምጻችንን የምትሰሙት (ዘጠኝ ወራት ሙሉ ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከክልል እስከ ፌደራል መንግስት ፣ አልፎም በአደባባይ ለዓለም ህዝብ ጮሄናል) ? ከዚህ የከፋ ምን ሲደርስብን ይሆን ህመማችን የሚያማችሁ (ወጣቶች የጥያት እራት የሆኑበት፣ መንደር ሙሉ ተቃጥሎ ነዋሪው የተሰደደበት፣ አምስት ወር ሙሉ ደመወዝ የተከለከለበት፣ …) ? ምን ስናደርግ ይሆን ከትግላችን ተሞክሮ የምትቀስሙት (የባህል መሪ፣ ኃይማኖት አባቶች፣ ከህጻናት እስከ አረጋዊያን፣ ከመንግስት ሠራተኛ እስከ አርሶአደር፣ ከገጠር እስከ ከተማ፣…በአንድ የቆሙበት፣ተፈናቃይና ተጎጂዎችን ህዝቡ በአቅሙ የደገፈበት ..) ? የተበጣጠሰና የተከፋፈለ የተናጠል ትግል መስዋዕትነቱን ያበዛዋል፣ የመከራና ሥቃይ ጊዜኣችንን ያረዝመዋል፡፡
በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚደረጉትን የ‹በቃኝ› ህዝባዊ እምቢተኝነት የለውጥ ትግል አስተባብሮና አቀናጅቶ የሚመራ አንድ ጠንካራ ፖለቲካዊ ኃይል/ማዕከል ያለመፈጠሩ ነው እነዚህን ጥያቄዎች እንድናነሳ ያስገደደን፡፡ እርግጥ ነው በአገር ውስጥም በውጪም የሚታየው ከመቼውም ጊዜ የተለየ የአንድነት /ትብብር ስሜት የሚያበረታታን የትግል ስንቅ ሆኖናል፤ ግን እስከመቼ ነው ከፖለቲካ ኃይሎችና የአገራችን ልህቃን በዚህ መልክ በተናጠል ስንመታ፣ ስንታፈን በተናጠል ቆማችሁ የምትመለከቱት ? ስለምንስ የአገራችን የፖለቲካ ኅይሎችና ልህቃን በአንድ መቆም ተሸነፋችሁ ? የድረሱልን – የአድማጭ ያለህ ጥሪያችን- የኮንሶ ህዝብ ብቻውን በተናጠል የድል፣ የመብቱና ነጻነቱ ባለቤት አይሆንምና ስለ ኮንሶ ህዝብ ብቻ አይደለም ፡፡ጥያቄኣችን ኢትዮጵያዊ ነው፤ ይህን በአራቱም የአገራችን አቅጣጫ የተፋፋመውን ህዝባዊ እምቢተኝነት የሚያስተባብር አንድ የአመራር ኃይል/ ማዕከል በመፍጠር፣ ትግሉን በማቀናጀት፣ በዝቅተኛ ዋጋ የሥቃይ ዘመናችንን ለማሳጠር በአንድ የምትቆሙት ወይም ምክክር እንኳ የምትጀምሩት ወይም በቪዥን-አትዮጵያ/ኢሳት የተጀመረውን የምትቀጥሉት፣ የምስራች የምታሰሙን መቼ ነው የሚል፡፡
ለዚህ ተግባራዊ የጋራ መልስ እንጂ የተናጠል ድርጅታዊ መግለጫችሁ፣ በመገናኛ ብዙሃንና በሰልፍ መርዶኣችን መንገራችሁ ፣ የመረረ ሃዘናችንን መግለጻችሁና ማስተጋባታችሁ፣… የዲፕሎማሲያዊ ዘመቻችሁ ፣ ትግሉን ቢያግዝም ፣ለድሉ አስተዋጽኦ ቢኖረውም …የሚከፈለውን መስዋዕትነት በሚቻለው መጠን አይቀንሰውም፣ የድሉን ቀን እስከሚቻለው አያቀርበውም፣ ከድል በኋላ የሚመጣው ለውጥ ዘላቂ፣አስተማማኝና የተረጋጋ ለመሆኑ መተማመኛ አይሆንም፡፡ ስለዚህ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንጠይቃችሁ- መቼ ነው– አገራችንን ህዝባችን ላይ ስለደረሰውና እየደረሰ ስላለው፣ የጋራ ድምጻችሁን የምንሰማው፣ የተቀናጀ የትግል አመራራችሁን፣ … የምንጠብቀው፣ አስተማማኝና ዘላቂ የጋራ የመፍትሄ አማራጫችሁን በትብብር የምታቀርቡል ??
በድል ታጅበን ከአዲሱ የለውጥ ዘመን ለመድረስ የጀመርነውን ጉዞ በጋራና በመተባበር አጠናክረን እንቀጥል፣ ወደፊት፡፡
አዲስቱ አንዲት ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኖራለች፤ አንጠራጠርም፡፡ መስከረም 03/ 2009 ፡፡
No comments:
Post a Comment