”
“ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን በቅናሽ ዋጋ ይፈልጋሉ? .. ታላቅ ቅናሽ በኢትዮጵያውያን ቤት ሰራተኞች ላይ አድርገናል !!”
ባህሬን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር ገርሞት የለጠፈውና እዚያው ባህሬን የሚገኝ ስራተኛ አስቀጣሪ ድርጅት ማስታወቂያ የሚለው ነው ከላይ የተጠቀሰው። ምናልባት ይህ ማስታወቂያ በጋዜጦች ሁሉ የታተመ ሊሆን ይችላል። እንዲህም ይላል . ኬንያውያን ቤት ስራተኞችን በ600፣ ኢትዮጵያውያንን ግን በ500 የባህሬን ዲናር መቅጠር ይችላሉ .. ለአንድ ወር የሚቆይ ታላቅ ቅናሽ !
ድሮ ለዕቃ እንጂ ለሰው እንዲህ በአደባባይ ዋጋ ወጥቶለት አይሸጥም ነበር። የባሪያ አሳዳሪ ጊዜ በባህሬን ተመልሶ የመጣ ይመስላል። እኛ ላይ መቼም የማይበረታ የለም። የሥራ ችሎታ እንደግለሰብ የሚለያይ ቢሆንም ድርጅቱ ግን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ ዓይነት ከሁሉም ያነሰ ዋጋ ሰጥቶ በአደባባባይ እያሻሻጠን ነው። ለነገሩ ከጥቂት ዓመት በፊት ሳውዲ አረቢያ “ይህን ያህል ኢንጂነሮች ከህንድ፣ ይህን ያህል የቤት ሰራተኞች ደግሞ ከኢትዮጵያ ላስመጣ እፈልጋለሁ” ስትል ማስታወቂያ ያወጣች ጊዜም ነው ውርደቱ የጀመረው። ከኢትዮጵያ ያለ ጽዳት ሠራተኛ ሌላ ባለሙያ አይወጣም ማለቷ ነው። እኔ መንግስት ብሆን፣ ይህን ማስታወቂያ ካላረምሽ በቀር አንድም ስው አንልክም እል ነበር።
ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም “ተደፍረናል፣ ተዋርደናል” አሉ እየተባለ በምርም በቀልድም ይነሳል። እሳቸው አሉም አላሉም፣ በርግጥም ግን ተደፍረናል፣ ተዋርደናል። እንደ አገር ተዋርደናል .. የትም ብትሄዱ ድሮ የነበረን ዝናና ክብር የለም፣ .. ትኑር አትኑር ብዙም የማናውቃት፣ ብናውቃትም ባናውቃትም ምንም የማትመስለን ማላዊ፣ ወይም ማሊ፣ ወይም ታንዛኒያ .. ብትሄዱ፣ አንድ የነዚህ አገር ፖሊስ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስሮና አንበርክኮ ፣ ለጋዜጠኞች “አገራችን በህገወጥ መንገድ ገብተው አገኘናቸው” አያለ ሲደሰኩር ብዙ ጊዜ እየሰማን ነው። የተከበረ አገር ቢኖረን ፣ ቢያገኘን እንኳን ቀስ ብሎ ኤምባሲ ምናምን ነገሮ ይሸኘን ነበር። መንግስት የሌላቸው የመን እና ሊቢያ እንኳን ብንሄድ፣ ችግርና መከራ ያለበት ቦታ እኛም አለንበት። መቶ ኢትዮጵያውያን ባህር ገብተው ሞቱ ቢባል የሚደነግጥ የዓለም መንግስት የለም። 5 አሜሪካውያን ከሞቱ ደግሞ ዓለም ቀውጢ ይሆናል። አልፈርድባቸውም።
በግላችንም ራሳችንን አስንቀናል፣ አዋርደናል። እዚህ አሜሪካ ብናይ፣ አበሻ በዛ ያለበት መስሪያ ቤት ሄደን ብንጠይቅ፣ “አንዱ ሌላውን እያጋፈጠ” ከሥራ የሚያስወጣው፣ ወሬ እያቀበለ እገሌ እንዲህ አርጓል የሚለው ራሱ ኢትዮጵያዊው ነው። ርስ በርስ መጠላለፋችን (ማንም ሳያስገድደን)፣ በማያውቁን የሌላ አገር አስሪዎች ዘንድ ቢያስንቀን ምን ይገርማል?
ራሳችን፣ የራሳችንን ሰለማንናከብር፣ ራሳችንን በማስናቃችን ማንንም ልንወነጅል አንችልም። የአበሻ መዝናኛ መጥቶ በአንድ ቢራ ያዙኝ ለቀቁኝ የሚለው፣ አስተናጋጆቹን እያመናጨቀ ፣ ሲፈልግም ደረትና መቀመጫ ካልነካሁ የሚለው፣ ሁለተኛ ቢራ ሲደግም ደግሞ ጠርሙስ እየወረወረ ካልተፈናከትኩ የሚለው ሰው፣ ፈረንጅ መዝናኛ ሲሄድ 20 ቢራም ጠጥቶ አንገቱን ደፍቶ ነው የሚወጣው። የራሱን ፣ የአገሩን ሰው መዝናኛ ስለሚንቅ ነው። አሁን አሁንማ ሶማሌውም ፣ ናይጄሪያውም ድብድብ ሲያምረው አበሻ መዝናኛ እንሂድ ሳይል አይቀርም።
“አበሻ ሌባ ነው አትቅጠር ይሰርቁሃል” ብሎ አንዱ አንድ ነዳጅ ማደያ ያለው ህንድን ሲመክር የሰማ ሰው ነግሮኛል። አንድም የጅምላ ፍረጃ ነው .. ሁለትም ደግሞ የራስን ገመና በማሳጣት ደሞዝ ለማስጨመር፣ ለመወደድ መሞከር ነው ! የራስን ችግር በራስ መንገድ መፍታት አይቻልምን? ከዚያ በኋላ ህንድ የተባለ ሁሉ አበሻ አንቀጥርም ቢል “ዘረኛ” ልንለው ነው?
በየንግድ ቦታው በግል ባህሪያችን አስቸጋሪነት የተነሳ “ከአበሻ ጋር ቢዝነስ ይቅርብን” የሚሉ ባለሙያዎች ብዙ አሉ። የራስን ሰው ሥራ እናናንቃለን። ለራሳችን ሰው፣ ለራሳችን ባለሙያ 100 ብር ከምንከፍል ለተመሳሳይ ሥራ ለአሜሪካዊው 300 ብንከፍል የሚሻለን አለን። ብዙ አሰርተን፣ ብዙ ጠይቀን ክፈሉ ስንባል ወገቤን የምንል ብዙ እንዳለን ይነገራል።
አንዳንድ ጊዜ እንደ አገር መናቃችን እና ክብር ማጣታችን እንዳለ ሆኖ፣ እኛም ለራሳችን የምናሰጠውን ክብር የምናስቀንስ አለን። ማንም አለው ማን “ተዋርደናል፣ ተንቀናል”
ጥሩነቱ ልናስተካክለው እንችላለን። ሁላችሁም ከኔ የተሻለ ዕውቀት አላችሁ – መፍትሄውን ለናንተ ልተወው … እንዴት?
ወይ ባህሬኖች፣ “አበሻ በቅናሽ ከፈለጋችሁ!! ” አሉ ?
No comments:
Post a Comment