Tuesday, September 20, 2016

በአገሪቱ ለተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምሁራን፣ፖለቲከኞች፣ ዕውቅ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች የመፍትሄ ሃሳብ የሚሉትን መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል፡፡


በአገሪቱ ለተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ምሁራን፣ፖለቲከኞች፣ ዕውቅ ግለሰቦችና የአገር ሽማግሌዎች የመፍትሄ ሃሳብ የሚሉትን መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ሃሳባቸው ጆሮ አግኝቷል ወይ ለሚለው እርግጠኛ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ውጤቱን በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡ አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነትመናገር ይቻላል፡፡ የመፍትሄ ሃሳቦቹ አሁንም መቀጠል አለባቸው፡፡ መንግስት በአዲሱ ዓመት አገርን ወደ ሰላምና መረጋጋት የሚያመጣ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ይደርሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
የዚህ ውይይት ዓላማ፣በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ ሃሳቦችን በማንሸራሸር መፍትሄ ማፈላለግና መጠቆም ነው፡፡ በአገራችን ለተከሰተው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ወይም አስተያየት አለን ለምትሉ ወገኖች መድረኩ ሁሌም ክፍት ነው፡፡
“ህዝብ መንግስትን ይፈጥራል እንጂ መንግስት
ህዝብን አይፈጥርም”
ሻምበል ለማ ጉያ (ሰዓሊ)
እኔ ቀደም ብዬ በኦሮሚያ ጉዳይ ላይ አስተያየቶችን ስሰጥ ነበር፡፡ አሁን የተፈጠሩት ችግሮች እንደሚመጡ አስቀድሜ ለማውቃቸው አመራሮች ተናግሬያለሁ፡፡
ለአባ ዱላም ለጁነዲንም (ፕሬዚዳንት በነበረ ጊዜ) ነግሬያቸዋለሁ፡፡ “በንጉሡ ላይ የደረሰው ችግር ቆይቶ በእናንተም ላይ እንዳይደርስ ካሁኑ ሁሉንም ነገር አስተካክሉ፤ የኦሮሞን ህዝብ ችግሮች የምታስተካክሉት እናንተ ናችሁ፤ አስተካክሉ” ብዬ ተናግሬያለሁ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ብዙም ለሹመትና ለስልጣን ጉጉት የለውም፤ በገዳ ስርአት ነው የሚተዳደረው፡፡ በገዳ ስርአት ጊዜያቸው ሲደርስ ለተረኛው ስልጣናቸውን በደስታ ነው የሚያስረክቡት፡፡
ህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄው ከተመለሰ መልማትና መበልፀግን እንጂ የስልጣን ባለቤትነት አያሳስበውም። ከሌላው ማህበረሰብ ጋርም መኖር የሚችል ነው፤ ልዩነትን አይወድም፤ “ተው ልዩነትን አትስበኩ፤ አስተካክሉ” ብዬ ደጋግሜ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ከፋፍለህ ግዛ የሚለው ፖሊሲ፣ አለም አንድ መንደር በሆነችበት ዘመን አይሰራም፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ግንባር ቀደም ሆና ለአፍሪካ ነፃነት ስትታገል የነበረች ሀገር፤ ዛሬ በዚህ ችግር ውስጥ ገብታ ለምን የዓለም መሳቂያና መዘባበቻ ትሆናለች?
በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ማንም ሰው በደሉን ገልጾ ቢናገር፣ አይታሰርም ወይም ከስራ አይባረርም። ዛሬ ግን አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ አንዳንድ በስልጣኑ አካባቢ የሌሉ የኦሮሞ ተወላጆችን አነጋግሬ ነበር፡፡ “ችግሩን ስንናገር ኦነግ ናችሁ እየተባልን ወደ እስር ቤት እንሄዳለን” ይሉኛል፡፡ አማራዎቹም ችግሩን ሲናገሩ፤ ግንቦት 7፣ ቅንጅት እየተባሉ ወደ እስር ቤት እንደሚላኩ ነግረውኛል፡፡ ይሄ ሁሉ ትክክል አይደለም፡፡ ክብር የነበራት ሀገር አሁን የአለም መሳቂያ ሆናለች፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? ድሮ ዳር ድንበራችንን ወደ ውጪ እየተኮስን እናስከብር ነበር፤ ዛሬ ለምን አፈ-ሙዙ ወደ ውስጥ ይዞራል፤ ህዝብ ላይ አፈ-ሙዝ መዞር የለበትም፡፡ ማስተካከል አለባቸው፡፡ መሳሪያ ድንበር መጠበቂያ እንጂ ወደ ህዝብ መተኮሻ አይደለም፡፡ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የህዝብ ብሶት ማውጫ እንጂ የመንግስት ስልጣን ማስጠበቂያ መሆን የለባቸውም፡፡
እኔ አንዳንዴ አዝናለሁ፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ተሰብስበው ስለተፈጠረው ችግር መግለጫ ሲሰጡ አያለሁ፡፡ የሚያሳዝነው እነዚህ ሰዎች ችግሩን በሚገባ አይናገሩም። መንግስት የሚናገረውን እንደ ገደል ማሚቶ መልሰው ያስተጋባሉ፡፡ ህዝቡ የጠየቀውን በአግባቡ አስረድተው መንግስትን ሲያሳስቡና ሲገስፁ አይታዩም፡፡
እኔ ደጋግሜ ላገኘኋቸው ባለስልጣናት ሁሉ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ላይ የሰፈረው “እስከ መገንጠል” የሚለው እንዲወጣ ጠይቄያለሁ፡፡ አንቀጹ እስካለ ድረስ ደግሞ የመገንጠል መብት መፈቀድ አለበት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አንቀፅ ነቀርሣ ነው፤ መወገድ አለበት፡፡ ከትልቅ ዛፍ ላይ ቅርንጫፍ ከተገነጠለ በኋላ ድጋሚ እንደማይበቅል መረዳት አለብን፡፡ አሁንም ቢሆን ይሄ አንቀፅ ካልወጣ ይህቺ ሃገር መቅኖ አይኖራትም፡፡ ይሄ የማንነት፣ የድንበር፣ የመገንጠል ጥያቄ የሚነሣው ከዚህ ‹‹መገንጠል›› ከሚለው ነቀርሳ ነው፡፡ ኤርትራ ተገነጠለች፤ ጅቡቲም ተገንጥላ ነው፡፡ ግን አሁን እነዚህን ሃገሮች ማን ይመልሳቸዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር ሕዝብ መንግስትን ይፈጥራል እንጂ መንግስት ህዝብን አይፈጥርም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ይሄን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው፡፡ የችግሩን መንስኤ በአግባቡ እንዳልተረዱ ከሚያቀርቡት የመፍትሄ ሃሳብ መረዳት ይቻላል፡፡ ሰዎቹ ገና ችግሩን በሚገባ አልተረዱትም፡፡
ዛሬ በየከተማው የምናያቸውና የህዝቡን መሬት እየቸበቸቡ፣ ብር በቦርሳ አጭቀው የሚወጡት አየር ወለድ ከንቲባዎች ናቸው፡፡ በአብዛኞቹ ከተሞች የሚሾሙት የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ፣ ማህበረሰቡን የማያውቁ ፖለቲከኞች ናቸው። እነዚህ አየር ወለድ ከንቲባዎች የህዝብ ሃብት ከመበዝበዝ ወደ ኋላ አይሉም፤ ምክንያቱም ህዝቡን አያፍሩትም። ከዚያው የተወለዱ ቢሆንማ ትንሽ እፍረት የሚባል ነገር ይኖራቸዋል፡፡
ብዙ ጊዜ የሚሠጡ አስተያየቶች እሠማለሁ። እንደኔ መንግስት፤ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፣ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም የመሳሰሉ አንጋፋ ፖለቲካ አዋቂዎች፤ እዚህችው ሃገር ላይ ተቀምጠው የሚሰጡትን ምክር መስማት አለመቻሉ ብዙ አሳጥቶታል፡፡
ለምን እነዚህን ሰዎች አይሠማቸውም? ለምን ምክራቸውን አይቀበልም? ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ ሃገራቸውን ስለሚወዱ ነው እድሜ ልካቸውን ሃገር ውስጥ ተቀምጠው የሚጮኹት፡፡ ለምን እነዚህ ሰዎች አይደመጡም?
ምርጫችን ፕሬዚዳንታዊ መሆን አለበት ባይ ነኝ፤ምክንያቱም ሃገር ሊመራ የሚገባው አሁን እንዳለው በጓዳ ተመርጦ የሚመጣ ሳይሆን ህዝቡ በቀጥታ ድምፅ የሚሰጠው ሰው ነው፡፡
በእዚህ ጉዳይ ላይ ምክረ- ሃሳቦች በሰፊው ተሰባስበው፣ አካሄዱ መስተካከልና የህዝቡ ጥማት የሚረካበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡
===========================
“የአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ አሳሳቢ ነው”
ፓስተር ዶ/ር ዘካርያስ አምደብርሃን
የአሁኑ የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና አስቸጋሪ ነው፡፡ አስቸጋሪ የሆነበት ዋናው ምክንያት የመናበብ፣ የመደማመጥና የመመካከር ባቡር ላይ ተሳፍረን፣ ሃዲዱን የተከተለ መንገድ ላይ ያለን አይመስለኝም፡፡ ቅራኔዎች የሚፈጠሩት ጆሮና ምላስ ሳይቀራረቡ ሲቀር ነው፡፡ ምላስና ጆሮ ሲተላለፉ ማለት ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ይኸው ነው፡፡ መንግስት መናገርና ህዝቡን ማሳመንን እንደ ዋና ሥራው አድርጎ ተያያዘው፤ መናገር ብቻ አበዛ። ጆሮውን ዘግቶ በራሱ መንገድ ነጎደ፡፡ ህዝቡም ጆሮ ሰጥቶ ሲሰማው ቆየ፡፡ ለውጥ እንዳጣ ሲገባው፣ እንደ መንግስት ከጆሮ ወደ ምላስ መጣ፡፡ ህዝቡም መናገርን ተያያዘው፡፡ አሁን መንግስትም ይናገራል፣ ህዝብም ይናገራል፡፡ ሰሚ የለም፡፡ የማያባራ ችግር የሆነው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ ውይይት፣ ንግግር፣ መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ያልተጠየቀውን ለመመለስ ከመሞከር መታቀብ አለበት፡፡ የተጠየቀውን ጥያቄ ወደ ሌላ አቅጣጫ መውሰድም የለበትም፡፡ ይኼ መንገድ እንደማያዋጣ በተደጋጋሚ እየታየ ነው፡፡ ህዝቡም ጥያቄውን ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ማቅረብን ባህሉ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ወደ መፍትሄ ለመምጣት በመጀመሪያ መደረግ ያለበት የሚመስለኝ ብሄራዊ ዕርቅ ማውረድ ነው። ህዝቡን ወደ ቂምና በቀል የሚወስዱ መንገዶችን እርግፍ አድርጎ መሄድ ያስፈልጋል። ኢህአዴግም ላለፉት 25 ዓመታት ሲናገራቸው የነበሩ አሉታዊ ቃላትን ማረም አለበት፡፡ ተቃዋሚዎችም እንደዚያው። ለምሳሌ “ጠባብ”፣ “ትምክህተኛ”፣ “የጥቂቶች ጥያቄ” የመሳሰሉትን ቃላት መጠቀም ውጤት አያመጣም፡፡ ሰው ሁሉ የዘራውን ያጭዳል ይላልና ቃሉ፡፡ ሁለተኛው፡- መንግስት በህገ መንግስቱና በዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ቁርጠኝነት ማሳየት አለበት። ኢህአዴግ፤ “ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ሲንዱ ነበር” ብሎ እንደሚከሰው፣ “ከውስጥም የመናድ አደጋ ተጋርጦብናል” በማለት መታረም አለበት። ሶስተኛ፤ የመንግስት ሚዲያ ህዝቡን ወደ ሌላ አማራጭ ሚዲያ ከማስኮብለል መታቀብ አለበት። ሁላችንም እውነትን ከመንግስት ሚዲያ እንሻለን። የተከሰተውን ችግር አፍረጥርጦና ተነጋግሮ መፍታት መለመድ አለበት፡፡ በሚዲያው መታለል አንፈልግም፡፡ ለከት ያጣ የሚዲያ ፕሮፓጋንዳ መንግስትና ህዝቡን እያለያዩ ነው፡፡ መንግስትና ህዝቡን የማፋታት ተልዕኮውን ማቆም አለበት። ህዝቡ “በቃኝ ውሸት… ሰለቸኝ” እያለ ነው፡፡ አራተኛ፡- ህዝቡ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በምንም ይሁን በምን ማክበርን ባህሉ ማድረግ አለበት። መንግስት እንኳን ህገ መንግስቱን ሙሉ በሙሉ ለማክበር ባይፈልግ፣ ህዝቡ ለህገ መንግስቱ ጥብቅና መቆም አለበት፡፡ አምስተኛ፡- አሳታፊ ፖለቲካ ሊኖር ይገባል፡፡ ህገ መንግስቱ በተለይም የምርጫ ህጉም ሆነ ሌላው በውይይት መሻሻል ካለበት ማሻሻልና አገሪቱን መታደግ ይገባል፡፡ ህገ መንግስቱ የህዝቡ አብሮ የመኖር ሰነድ ነው፡፡ ህዝቡ ከፈለገ ማሻሻል ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁራን አይደለም፡፡ ስድስተኛ፤ ኢህአዴግ በተለያየ ዘርፍ ከአግባብ ውጭ የሚኖሩ አባላቱን ለማረም ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡
===========================
‹‹የፖለቲካ አካሄድ መሟጠጥ ነው ጥይት የሚያስተኩሰው››
ፀጋዬ ደቦጭ (የሙዚቃ ባለሙያ
ፀጋዬ ደቦጭ (የሙዚቃ ባለሙያ)
አሁን አገሪቱ ላይ የተከሰተው ችግር አይነካኝም አይመለከተኝም የሚል በአየር ላይ ያለ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ሁሉም ምድር ላይ ነው የሚኖረው። እኔም እንደ ማንኛውም ዜጋ ችግሩ ይሰማኛል፡፡ በእርግጥ ዛሬ ላይ ነገሮች ተጠራቅመውና ተባብሰው ሲመጡ ከበዱ፤ ነገር ግን ይሄ ከስር ከስር የሚነሱ ጉዳዮችን ያለመሰብሰብና ያለማዳመጥ ብሎም ምላሽ ያለመስጠት ውጤት ነው፡፡ ይሄ በመንግስት በኩል ያለ ጉልህ ድክመት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ነገሮች በቸልታ እየታለፉ መንግስትም ከውስጡ አንዳንድ ነገሮች እየሾለኩበት፣ የህዝብን ጥያቄ መመለስ እንዳለበት እየተሰማውም ያልተጠቀመባቸው ዕድሎች የዛሬውን ችግር የወለዱት ይመስለኛል በግሌ፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ልንሰማው የማይገባንን ነገር ለመስማት ተገድደናል፡፡
ላለፉት 25 ዓመታት የቆየ መንግስት፤ በዚህ ደረጃ ችግር ሲገጥመው መስማትም ማየትም አልነበረብንም፡፡ መንግስት እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ሲገባ በጣም ከባድ ነው፡፡ የእኛን ሙያ እንኳን ተይው፤ ሲረገጥ የኖረ ሙያ ነው፡፡ ለእኛ ሙያ ስርዓቱ ከመጀመሪያውም  መልስ አልሰጠንም። የእኛን ዝም ብለን ስንኖር ህብረተሰቡ ደግሞ ጥያቄዎቹን አነሳ፤ እኛም የህብረተሰቡ አካል ነን፤ ሙያችን የሚኖረው የሚያድገውም ህብረተሰቡ ሲኖር ነው። አድናቂያችን እድገታችን ህብረተሰቡ ነው። ህብረተሰቡን የሚነካውን ስሜት እያሰብን ነው የምንሰራው፤ ስለዚህ ችግሩ ይሰማናል፡፡ እኔ በግሌ እንደሚመስለኝ ሰዎቹ አዋቂ መሆን አለባቸው፤ አዋቂ መሆናቸው ተስፋ ይሰጣል፡፡ ዛሬም ባይሆን ነገ እነሱን ያኮራል፡፡ እናም ከመንግስት በኩል ማጎንበስን እጠብቃለሁ፡፡ ያኮረፈው የሚምልበት ህዝብ ነው፡፡ ያኮረፈው የሚያስተዳድረው ህዝብ ነው፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ አንድን ሰው አዋቂ የምለው ተበድሎም ቢሆን ይቅርታ የሚጠይቀን ሰው ነው፤ እንኳን በድሎ ይቅርና፡፡ እና መንግስት ይሄን መንገድ ቢከተል የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ወፉም አራዊቱም የወንዙም አወራረድ የሚያምረው አገር ሰላም ሲሆን ነው፤ እንኳን ሰው፡፡ በችግሩ ብዙ ንፁሃን ህይወት አልፏል፤ ይህ መሆን አልነበረበትም፡፡ ባለኝ መረዳት የመንግስት ትልቅ ሀብትና ኩራት ሊሆን የሚገባው ፖለቲካዊ አካሄድና ብልሀት ነው፡፡ የፖለቲካ አካሄድ የተሟጠጠበት መንግስት ደግሞ ምንም የለውም ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ አካሄድ መሟጠጥ ነው ጥይት የሚያስተኩሰው፡፡ ጥይት መተኮስ ደግሞ ሽንፈት ነው፡፡
በሌላ በኩልም መንግስት የሚሰጠውን መግለጫ ቢያስብበት ጥሩ ነው፡፡ ይሄ ማለት የሚሰጣቸው መግለጫዎች፤ ለህዝቡ ትርጉም የሚሰጡ መሆን አለባቸው እንጂ ማስፈራሪያ መሆን የለባቸውም። ህዝብን ይዞ በህዝብ ተደግፎ፣ ያንን ሀይለኛ የተባለውን ጦር ማሸነፍ እንደሚቻል ከእነሱ በላይ የሚያውቅ የለም፡፡ የመጡበትን መንገድ ዞር ብለው ቢመለከቱት፣ በህዝብ ድጋፍ እዚህ መድረሳቸውን ያጤኑታል፡፡ አሁንም የህዝብ ድጋፍ ማጣት እንደሌለባቸው ይገነዘቡታል፡፡ በበኩሌ አገራችን የበቀል አገር መሆን የለባትም፡፡ በሁሉም አቅጣጫ እርቅ መፈጠር አለበት ባይ ነኝ፡፡ ስለሆነም ህዝቡ የሚጠይቀው ነገር ወዲያውኑ መልስ ማግኘት አለበት፡፡ ሰከን ብሎ ማሰብና ችግሮችን በውይይት መፍታት እንጂ ኃይል አለኝ ማለት አያስፈልግም፡፡ ኃይል ሁልጊዜ መተማመኛ እንደማይሆን እነሱም ከደርግ መማር ይችላሉ፡፡ ይህን ሁሉ ዞር ብሎ አጢኖ አገሪቱና ህዝቦቿ ወደ ሰላማቸው ቢመለሱ ምኞቴ ነው፡፡
===========================
“አሁን ያለው ሁኔታ ለትንበያም አያመችም”
አርቲስት ተስፋዬ ማሞ
አርቲስት ተስፋዬ ማሞ
እኔ ነፍስ ካወቅሁበት ጊዜ አንስቶ በተለይም ከንጉሡ ዘመን የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የተለያዩ ተቃውሞዎችን አይቻለሁ፡፡ ምናልባት በእድሜ መብሰልም ሊሆን ይችላል፤ የቤተሰብ ኃላፊነትም ይሆናል፡፡ እውነቱን ለመናገር፣እኔ እንደዚህ ዘመን ፈርቼ አላውቅም፡፡ እንዲህ እንደ አሁኑ ሰግቼና ተሳቅቄ አላውቅም፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ በደርግ ጊዜ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መተንበይ ይቻል ነበር፤አሁን ግን ያለው ሁኔታ ለትንበያም አያመችም፡፡ በደርግ ከግራ ቀኝ የታጠቁ ኃይሎች ስለነበሩ ውጤቱ ይታወቅ ነበር፡፡ ይሄኛው ለመተንበይ የሚያስቸግር ነው፡፡ አንዱ ጋ የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚመስል፣ ሌላ ቦታ የማንነት፣ ሌላው ጋ የኢኮኖሚ ፍትሃዊነት፣ ሌላው የአስተዳደር የሚመስል የተደበላለቁ ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች እንዲህ ያለ ውጤት ያመጣሉ ብሎ ለመተንበይ ቀርቶ፣ መጪው ምን ይሆናል የሚለውን ለማወቅም እጅግ አዳጋች ነው፡፡ እንዲህ አይነት የህዝብ ቁጣና ተቃውሞ በየጊዜው የሚመጣ ቢሆን ኖሮ ይለመድ ነበር፡፡ ህዝቡ በየጊዜው ጠንከር ያለ ጥያቄ ማቅረቡ የሚፈለግ ነው፤ ምክንያቱም መንግስትን ያነቃል፡፡ የሚፈነዳው ነገር ሊፈነዳ እንደሚችል ሳይታወቅ ድንገት ከሚፈነዳ በየጊዜው ቢፈነዳ ኖሮ ከስጋት እንድን ነበር፡፡ አሁንም ያለው ሁኔታ ተከታታይና ያልተቋረጠ መሆኑ ያሳስባል። መንግስት በየጊዜው የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ቢያዳምጥና ከስር ከስር ምላሽ ቢሰጥ ኖሮ እንዲህ ያለው ደረጃ ላይ አይደረስም ነበር፡፡
መቃወም መብቴ ነው ብሎ ህዝብ በነፃነት የሚቃወምበት ሁኔታ ቢኖር፣ እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ ባልተገባ ነበር፡፡ ህዝብ ሲጮህ አዳምጦ፣ ከጩኸቱ የወጡ ሃሳቦችን የሚጠቀምባቸው ብልህ የሆነ መንግስት ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ያለ መንግስት ተቃውሞ ሲቀርብበት ተደናግጦ ግድያና የኃይል እርምጃ ውስጥ አይገባም፡፡ አሁንም ቢሆን የዘገየ አይመስለኝም፤ እውነታውን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማለት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ማለት አይደለም፡፡ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ፤አንድ ነገር ሰጥቶ ሌላ ነገር መቀበል ነው፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሲባል ደግሞ የእውነት ችግሮቹ በደንብ ታውቀው መፍትሄ መስጠትን ይጠይቃል፡፡
ይሄ ሁሉ ተቃውሞ መቼም ዝም ብሎ ከመሬት አይነሳም፤ምክንያት ይኖረዋል፡፡ አሁን በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ አሠልቺ ቃላት አሉ፡- መልካም አስተዳደር፣ የውጭ ሃይል ምናምን የሚባለውን ትቶ መፍትሄ በተግባር ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹መልካም አስተዳደር›› ጥቅል ነው፤ መበተን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መንገድ ካልተሄደ መፍትሄ ላይኖር ይችላል። ሆድ ውስጥ ባክቴሪያ እያለ ለማስታገሻ ፓናዶል የሚሰጥ ከሆነ፣ ስር እየሰደደ በመጨረሻ ካንሠር ነው የሚሆነው፤ ስለዚህ  በታማኝነት በእውነተኛ ቁርጠኝነት ለመፍትሄ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
ሌላው የመነጋገሪያ እውነተኛ መድረክ ማዘጋጀት ነው፡፡ ለምሳሌ በጣም ከሚያስቀኑኝ የመነጋገሪያ መድረኮች አንዱ፣ የቢቢሲ የክርክር መድረክ ነው፡፡ ሁለት የተለያዩ ሃሳቦች ያላቸው ቡድኖች፤ ሃሳባቸውን ይዘው መጥተው፣ ጥልቅ ውይይት በተሳታፊዎች ፊት ያደርጋሉ፡፡ ያለምንም ገደብ ይተቻቻሉ፡፡ መንግስት ይጠቅመኛል ካለ ሃሳቦቹን ይወስዳል፤ እኛም ጋ ይህ ያስፈልጋል፡፡
የመነጋገሪያ መድረኮች መስፋት አለባቸው። አለመነጋገራችን ነገሮችን እያከረረ እዚህ ደረጃ ላይ አድርሶናል፡፡ ስለዚህ ችግሮቻችንን ሳናለባብስ መነጋገር አለብን፡፡ ብቁ ካልሆን፣ ብቁ አይደለሁም፤ ከአቅሜ በላይ ነው የሚል ልማድም ማዳበር አለብን። ያለአቅማችን ተሸክመን ችግር መፍጠር የለብንም፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ሁሌ ይወራል፡፡ ለምን አልተፈታም? የአቅም ማነስ ችግር ነው፡፡ ይሄን ማስተዋል አለብን፡፡ አሁን የተፈጠሩትን ችግሮች የአለም ፍፃሜ አድርገን መመልከት የለብንም። እንደ መልካም አጋጣሚ ብንወስደው ጥሩ ነው። ለስህተት ማረሚያና ለተሻለ መንገድ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ብንቆጥረው መልካም ነው፡፡

No comments:

Post a Comment