Friday, April 15, 2016

የሃገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊው አቶ ወልደሥላሴ ወ/ሚካኤል በሙስና ወንጀል ከእህታቸውና ከወንድማቸው ጋር ጥፋተኛ ተባሉ

 


w-sellassie
መንግስታዊው ራድዮ ፋና ዛሬ እንዘገበው የቀድሞው የሃገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊው አቶ ወልደሥላሴ ወ/ሚካኤል በሙስና ወንጀል ከእህታቸውና ከወንድማቸው ጋር ጥፋተኛ ተባሉ:: ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር በነበራቸው የግል ችግር የተነሳና ከሕወሃት ሰዎች ምዝበራ ጋር በተያያዘ ብዙ መረጃዎችን በ እጃቸው በመያዛቸው በፓርቲው ውስጥ ጥርስ ተነክሶባቸው ወደ እስር ቤት እንደተወረወሩ የሚነገርላቸው እኚሁ የድህንነት አባል ከተከሰሱበት 12 የሙስና ክሶች ውስጥ በ7ቱ ጥፋተኛ ተብለዋል ተብሏል::
የራድዮ ፋና ዘገባ እንደወረደ ያንብቡት::
(ኤፍ.ቢ.ሲ) የቀድሞው የሀገር ውስጥ ደህንነት ሰራተኛ አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም እና ምንጩ ያልታወቁ ሃብት በማፍራት ከቀረበባቸው 12 ክሶች በ7ቱ ጥፋተኛ ተባሉ።
በክስ መዝገቡ የተካተቱት ወንድምና እህታቸው ደግሞ በሶስት ክሶች ጥፋተኛ ተብለዋል።
በኢንቨስትምንት ስም በወንጀል የተገኘ 6 ሚሊየን ብር ሰውረዋል ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ዶሪ ከበደ ክሱን በበቂ ሁኔታ በመከላከላቸው በነፃ ተሰናብተዋል።
የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ በቀድሞው የሀገር ውስጥ ደህንነት ሰራተኛ አቶ ወልደስላሴ ወ/ሚካኤልን ጨምሮ ወንድማቸው አቶ ዘርአይ ወ/ሚካኤል፣ እህታቸው ወ/ሪት ትርሀስ ወ/ሚካኤል እና የቅርብ ጓደኛቸውና በንግድ ስራ በሚተዳደሩት አቶ ከበደ ዱሪ ላይ 12 የተለያዩ ክሶች ላይ ነው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ የወንጅል ችሎት ዛሬ ብይን የሰጠው።
ከክሶቹ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል፣ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ማፍራትና ታክስ ስወራ የሚሉት ይጠቀሳሉ።
1ኛ ተከሳሽ አቶ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል በ2002 ዓ.ም “ቴረሪዝም ኢን ኢትዮጵያ ኤንድ ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ” የተሰኘ መጽሃፍ ባሳተሙበት ወቅት፤ ይህንን መጽሃፍ በስፖንሰር ለማሳተም ባደረጉት እንቅስቃሴ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ በየነ ገ/መስቀል የነበራቸውን ቀና አስተሳሰብ ተጠቅመው ያለአግባብ በልጽገዋል ነው የሚለው የክስ መዝገቡ።
መጽሃፉ በመስሪያ ቤታቸው ስም እንደተዘጋጀ በሚያስመስል ሁኔታ አቶ በየነ የሚመሯቸው የቦሌ፣ የብርሃንና ሰላም እንዲሁም የአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ሃላፊዎች በጋራ የአቶ ወልደስላሴን 3 ሺህ መጻህፍት በ124 ሺህ ብር እንዲያሳትሙ አድርገዋል ነው የሚለው ክሱ።
ማተሚያ ቤቶቹ በርካሽ ያሳተሙት አቶ ወልደስላሴ ከነበራቸው ተሰሚነትና ስልጣን መነሻነት መሆኑንና ይህንን መጽሃፍ ኢትዮ ቴሌኮም ምንም በማይመለከተው 10 ሺህ መጻህፍት የሚታተሙበትን የ385 ሺህ ብር ክፍያ ለአቶ ወልደስላሴ እንዲከፍል መደረጉንም ነው የክስ መዝገቡ የሚያስረዳው።
አቶ ወልደስላሴ የሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝና የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው፥ ሁለቱ ድርጅቶች 310 ኮፒዎችን በግድ እንዲገዙ በማድረጉ ስልጣናቸውን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል 1ኛ ክስ ጥፋተኛ ተብለዋል።
እንዲሁም በ3ኛ ክስ የተሰጠውን ስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከ1998 እስከ 1999 ባሉት ጊዜያት ወይዘሮ ግርማነሽ ይኹኑአምላክ ለተባሉ ግለስብ ለግል ጉዳይዋ በአዲስ አበባ ከተማና ውጪ ስትንቀሳቀስ የመስሪያ ቤቱን ተሽከርካሪ ነዳጅ በመሙላት እና ሰራተኛ በመመደብ እንድትገለገል አድርገዋል ይላል ክሱ።
እንዲሁም ተከሳሹ ለግላቸው ራሳቸው ማስፈፀም ያለባቸውን ከመስሪያ ቤቱ ሰራተኛና ተሽከርካሪ ለሁለት ወራት ለተለያዩ ጉዳዮች በመጠቀማቸው ጥፋተኛ ተብለዋል።
ተከሳሹ ከ2003 እስከ 2004 ዓ.ም አቶ ሳቢር አርጋው የተሰኙ ነጋዴን ለምሰራው ቤት ሴራሚክ ስለጎደለኝ የጣሊያን ስሪት ገዝተህ ስጠኝ በማለት፥ በስልጣናቸው አስፈራርተዋቸው የ65 ሺህ ብር ሴራሚክ ተቀብለዋል በሚለው 4ኛ ክስም ጥፋተኛ ሆነዋል።
ከ2001 እስከ 2005 ባሉት የግብር አመታት አሳትመው ከሸጧቸው መጻህፍት ካገኙት ገቢ ላይ መክፈል የነበረባቸውን ከ496 ሺህ ብር በላይ ለመንግስት አሳውቀው ባለመክፈል ህግን በመጣስ 5ኛ ክስም ጥፋተኛ ተብለዋል።
በተጨማሪም በ8ኛው ክስ ከተለያዩ ሽያጮች መክፍል የሚገባቸውን የተርን ኦቨር ታክስ ባለመክፈል የተመሰረተባቸውን ክስ ፍርድ ቤቱ በሁለት ተመልክቶታል።
በአመት አንድ የሚከፈለው ግብር ተከሳሹ እጃቸው የተያዘው ነሐሴ 2005 ዓ.ም በመሆኑና የግብር መክፈያ ጊዜ እስከ ጥቅምት 2006 ዓ.ም በመሆኑ አያስጠይቃቸውም።
ሆኖም በየወሩ የሚከፈለውን ግብር ከግንቦት ወር ጀምሮ እጃቸው እስከተያዘበት የሶስት ወር አለመከፈሉ ጥፋተኛ አስብሏቸዋል።
9ኛ፣ 10ኛ እና 11ኛ ክስ ላይ በተከሳሹ ላይ የቀረበው ክስ በተመሳሳይ የህግ ድንጋጌ ሊጠቃለሉ የሚችሉ በመሆናቸው በ9ኛ ክስ ተጠቃለው ጥፈተኛ ተብለዋል።
ተከሳሹ በሁለተኛ ክስ ከ26 ተቋማት መጽሀፍ ሸጠው ገንዘቡን ከወሰዱ በኋላ ዳግም አስገድደው መጽሐፉን ወስደዋል የሚለውና ከታክስ ጋር ተያይዞ በክስ 6 እና 7 የቀረበባቸው ክሶችን ጨምሮ በአራቱ ነፃ ሆነዋል።
2ኛ ከሳሽ ዘርአይ ወልደስላሴ ውክልና ወስደው ከመኖሪያ ቤት ውጭ ለሆነ አገልግሎት እንዲውል አድርገው በ14 ወራት ውስጥ 790 ሺህ ብር ገቢ አግኝተዋል በሚለውም ጥፋተኛ ከተባሉበት ሶስት ክሶች ተጠቃሽ ነው።
3ኛዋ ተከሳሽ እህታቸው ትርሃስ ወልደሚካኤል የታተመውን መጽሀፍ የሽያጭ ዋጋ 399 ሺህ ብር በባንክ ሂሳባቸው አስገብተዋል በሚለውና በሌሎች ሁለት ክሶች ጥፋተኛ ተብለዋል።
በኢንቨስትምንት ስም በወንጀል የተገኘ 6 ሚሊየን ብር ሰውረዋል ተብለው ክስ ተመሰርቶባቸው የነበረው አቶ ከበደ ዶሪ ክሱን በበቂ ሁኔታ በመከላከላቸው በነፃ ተሰናብተዋል።
ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግና ተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያና ማክበጃ ለማድመጥ ለሚያዚያ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

No comments:

Post a Comment