Friday, April 22, 2016

ቀለ ገርባ ከ4 ጊዜ የፍ/ቤት ምልልስ በኋላ ዛሬ በዝግ ችሎት የሽብርተኝነት ክስ ቀረበባቸው



(ዘ-ሐበሻ) በኦሮሚያ የተነሳው ሕዝባዊ ቁጣ ሃገሪቱን ባጋጋላትና የሕወሓትን መንግስት ባንቀጠቀጠበት ወቅት ከቤታቸው ተወስደው የታሰሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሐፊን ጨምሮ 22 ሰዎች ዛሬ ክስ እንደተመሰረተባቸው ተሰማ::
ከታሰሩ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 4 ጊዜያት ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ካለምንም ክስ ወደ ማረሚያ ቤት ሲመላለሱ የቆዩት አቶ በቀለ ገርባ ይህንን በመቃወም በ እስር ቤት የረሃብ አድማ ጭምር እስከማድረግ ደርሰው እንደነበር በወቅቱ ዘ-ሐበሻ መዘገቧ አይዘነጋም::
ዛሬ በፌደራሉ 19ኛው ችሎት የቀረቡት አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች 21 ሰዎች ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ ክስ ቀርቦባቸዋል:: የዘ-ሐበሻ የፍርድ ቤት ምንጮች እንደሚሉት በአቶ በቀለ ላይ የተመሰረተው ክስ በኦሮሚያ የተነሳውን የሕዝብ ቁጣ ከርሳቸውና ከተከሳሾቹ ጋር ለማያያዝ ተሞክሯል:: እንዲሁም ከኦነግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚገልጹ ክሶች ሁሉ ቀርበውባቸዋል:: የዛሬው ችሎት በዝግ የተካሄደ በመሆኑ ዝርዝር ክሶቹን እየጠበቅን ነው::
በዚህ በአቶ በቀለ ገርባ ላይ በተመሰረተው ክስ ላይ አንድ የኬንያ ዜጋ ያለው ግለሰብ እንደተካተተ የሚገልጹት የፍርድ ቤት ምንጮች ከተከሳሾች መካከል 6 ወይም 7 የሚሆኑት የኦሮሚያ ቋንቋ ብቻ የሚናገሩ በመሆናቸው ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ችሎት የኦሮሚያ አስተርጓሚ እንደኢቀርብ አዟል::
በነበቀለ ገርባ ላይ አመጽን ማነሳሳት እንዲሁም ይህንንም በመደገፍ የሚሉ የሽብርተኝነት ክሶችን የመሰረተው አቃቤ ሕግ ተጨማሪ ቀነ ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን ኤፕሪል 26, 2016 የፍርዱ ሂደት እንደሚቀጥል የዘ-ሐበሻ የዜና ምንጮች አስታውቀዋል::

No comments:

Post a Comment