Sunday, April 17, 2016

ሰማያዊ ፓርቲ አደጋ ላይ ነው :: ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጋር ቃለምልልስ



• ፓርቲው የውስጥ ችግሩን መፍታት ለምን ተሳነው?
• ለፓርቲው ቀውስ ተጠያቂው ማን ነው?
• የመበታተን አደጋ ያሰጋው ይሆን ?
ሰማያዊ ፓርቲ በተለይ ሊቀመንበሩና ሌሎች አመራሮች መዝብረዋል የተባለውን ገንዘብ መነሻ በማድረግ በአጋጅ ታጋጅ ድራማ ታጅቦ በቀውስ
እየተናጠ ይገኛል፡፡ በፓርቲው ችግሮች፣ በመፍትሄዎቹ፣ በፓርቲው የወደፊት እጣ ፈንታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አለማየሁ አንበሴ ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ጋር ጥልቀት ያለው ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-
ሰማያዊ ፓርቲን —– ከምርጫ 2007 ዓ.ም በፊትና በኋላ እንዴት ይገልጹታል?
አሁን ባለው ሁኔታ ሰማያዊ ፓርቲ ስራ እየሰራ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ነው ያለው፡፡ የተፈጠሩ ችግሮች ከእለት እለት ፓርቲውን እንደሚጎዳ ሁሉ፣ የህዝቡንም የደጋፊውንም ስነ ልቦና እየጎዳ ነው፡፡ በተለይ ዲሲፒሊንና ኦዲትና ኢንስፔክሽን የሚባሉት በመካሰስና በፍረጃ የተሞላ ስራ እየሰሩ በመሆኑ፣ በአሁን ሰአት አባላት በንቃት እየተሳተፉ አይደለም። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡
ፓርቲው አሁን ከገባበት ችግር አንፃር እየተዳከመ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ…
ፓርቲው ተዳክሟል ማለት አልችልም፡፡ ሊቀመንበሩ እኔ ነኝ፤ አሁን ያሉት ስራ አስፈጻሚዎች በትምህርት ደረጃቸውም የተሻሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን ሰማያዊ ውስጥ ስራ የሚያሰራ ሁኔታ የለም። ወደ ስራ እንዳንገባ ልዩ ተልዕኮና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች፣ እለት በእለት ትጉህ አባላትን በመክሰስ፣ በመደብደብ፣ የማይሆን ስም እየሰጡ በመፈረጅ ተጠምደዋል፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ከመስከረም ጀምሮ ስራ መስራት አልተቻለም፡፡ በእስር ቤት ያሉ የፓርቲው አባላትን ጭምር አባረናል የሚል ውሳኔ ሁሉ ተወስኗል፡፡ ቀደም ሲል አራት አባላት ተባረዋል ተባለ፡፡ ከዚያ አይባረሩም ተባለ፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ አባረናል የሚል ውሳኔ እየሰማን ነው። ከዚያም አልፎ እኔንም አባረንሃል እየተባለ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ስራ መስራት የሚቻለው?
የዲሲፕሊን ኮሚቴው በፓርቲው ውስጥ ያለው ስልጣን ምን ድረስ ነው?
እኔም ግራ የገባኝ ይሄው ነገር ነው፡፡ ብዙዎቹ በኮሚቴው ውስጥ ያሉት የአቅም ችግር አለባቸው። የህግ ትምህርት ያለው አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ እሱም በብዙዎች ውሳኔ የሚዋጥ ነው፡፡ መስራት አልቻለም፡፡ ሌሎቹ ግን የትምህርት ደረጃቸውም ሆነ እውቀታቸው የሚያወላዳ አይደለም፡፡ ከዚያም ባለፈ ሆን ብሎ አባላትን ለመጉዳት የመንቀሳቀስ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ “የለሁበትም፤ውሳኔ አልሰጠሁም” እያለ ሰዎች በሌሉበት ነው ወሰንን የሚሉት፤ ህገ ወጥ ውሳኔዎች ናቸው የሚደረጉት፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች የአባላትና የደጋፊዎቻችንን ስነ ልቦና እየጎዱ ነው፡፡
የኮሚቴው ስልጣን ምን ድረስ ነው?
እኔ በጠቅላላ ጉባኤ ነው የተመረጥኩት፡፡ ውሳኔያቸው ላይ ካየኸው “ተባሯል ግን ለጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ይቀርባል” ነው የሚለው፡፡ ሊቀ መንበር ከሆንኩ ይሄ ነገር ለምን አስፈለገ፡፡ ተባሯል የሚለውን ማለቴ ነው፡፡ ይሄ ሆን ተብሎ የእኔን ሰብዕና ለማጉደፍ የሚደረግ ነው፡፡ ሆን ብለው የህዝቡን ልብ ለመስበር የሚደረግ ጥረት ነው እንጂ ይሄን ያህል የተሰጠው ስልጣን የለም፡፡ እኔን የመረጠኝ ጠቅላላ ጉባኤው ነው፡፡
የሁሉም መነሻ እርስዎን ጨምሮ ለምርጫ የተመደበን ገንዘብ መዝብራችኋል የሚል ክስ ነው … በእርግጥ የተባለው ድርጊት ተፈፅሟል ?
አንድ በግልፅ የምነግርህ ጉዳይ ይሄ ነገር ሆነ የተባለው በ2005 ዓ.ም ነው፡፡ አሁን 2008 ላይ ነው ያለነው፡፡ በ2007 ጠቅላላ ጉባኤ አድርገን የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ገቢና ወጪ ላይ የጠፋ ገንዘብ እንደሌለ ተማምነን፣ ያ ሰነድ ፀድቆ ለምርጫ ቦርድ ገብቷል፡፡ አሁን ታዲያ የ2005 ክስ ለምን መጣ? ሲባል ምክንያቱ ግራ ያጋባል፡፡ አጠፋን የተባለው የገንዘብ ልክ እንኳ አልተጠቀሰም፡፡ እነዚህ ሰዎች ያለ ማስረጃ በሃሜት ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ እኛ በፍ/ቤት ልንከሳቸው እንችላለን፡፡ መጨረሻ ላይ መረጃ ሲያጡ፣ ባልታወቀ የገንዘብ መጠን ምዝበራ ተባራችኋል ነው ያሉት፡፡
165 ሺህ ብር ተብሎ የተጠቀሰውስ ?
ኧረ ምንም ነገር የለም፡፡ የቅጣት ውሳኔያቸው ላይ “ገና በኦዲት ሪፖርት ሲደረግ የሚወሰንባችሁን በሁለት ወር ውስጥ ትከፍላላችሁ” ነው የሚለው፡፡
እርስዎ ያጠፋሁት ምንም ገንዘብ የለም እያሉ ነው?
አዎ እኔ ምንም ያጠፋሁት ገንዘብ የለም፤ክስም አልቀረበብኝም፡፡ ከሳሽ ነው የተባለው አቶ ይድነቃቸው ከሰሞኑ በፌስቡክ ገፁ ላይ “እኔ አልከሰስኩም፤ ክሱንም አልተከታተልኩም” ብሏል። ታዲያ ክስ ሳይኖር ፍርድ አለ? ምስክር ከየት መጣ? ዳኛውም ከሳሹም የዲሲፒሊን ኮሚቴው ነው ማለት ነው? ከሳሽ የተባለው ሰው አልከሰስኩም እያለ ክሱ ከየት መጣ? እንደውም “ይሄን ነውረኛ ተግባር ሊቀመንበራችን መናገር ያለበት አሁን ነው” ብሎ ነው የጻፈው፡፡ ታዲያ ከሳሽ ሳይኖር ፍርድ አለ?
የዲሲፒሊን ኮሚቴው ይሄን ሁሉ ግድፈት ሰርቶ ፓርቲውን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ነው የሚል እምነት ካላችሁ፣ የፓርቲው ማዕከላዊ ም/ቤት ለምን ዝምታን መረጠ?
እንግዲህ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የሚባለውን እኔ አላቋቋምኩም፡፡ ኦዲትና ኢንስፔክሽን የሚባለው ነው ያቋቋመው፡፡ እኛ አናውቀውም፡፡ ይሄን ሁሉ ስህተት ሲሰሩ ዝም ያላቸው እሱ ነው፡፡ መቆጣጠርና መከታተል ያለበት እሱ ነው፡፡ ትልቁ ስህተት የኦዲትና ኢንስፔክሽኑ ነው፡፡  የሚመለከተው እሱን ነው፡፡
ሌላው ሊቀመንበሩ በቢሮ ተገኝቶ አያውቅም፣ ስራ አስፈፃሚውንም ስብሰባ ጠርቶ አያውቅም፣ በአጠቃላይ ፓርቲውን ትቶታል የሚል ክስም ይቀርባል?
ይሄ ውሸት ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚው በየጊዜው ይሰበሰባል፣ ስራውን ይሰራል፡፡ ነገር ግን ፅ/ቤት ውስጥ አንድ ችግር አለ፡፡ የፅ/ቤት አገልግሎት ኃላፊው ማህተሙን ይዞ አለቅም ብሎ ቁጭ ብሏል። ከጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ የፓርቲውን ንብረት አስረክብ ተብሎ አሻፈረኝ ብሏል፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ሰውዬ ደሞዝተኛ ነው፡፡ ለፅ/ቤት ሰራተኞች ደሞዝ ይከፍላል፣ ቼክ ላይ ይፈርማል፣ ከ10 ሺህ ብር በታች የሆኑ ወጪዎችን ያንቀሳቅሳል፣ የስራ አስፈፃሚውን ቃለ ጉባኤ ይይዛል፡፡ ይሄ ነው የሱ ስራ። አሁን እነዚህን ሁሉ ስራዎች እየሰራ አይደለም። ቢሮውንም አለቅም፤ማህተሙንም አልሰጥም ብሎ ቁጭ ብሏል፡፡ ፅ/ቤቱን የምመራው እኔ ነኝ፤ በሌላ አነጋገር ይሄ ሰውዬ ለኔ አይታዘዝም ማለት ነው፡፡ እንደውም አምባጓሮ በመፍጠር ሰዎችን ይዞ እየመጣ ድብድብ መፍጠር ጀመረ፤ ስለዚህ እኔ እንዲህ ያለውን ነገር አልፈልግም፣ቢሮ ባልገባም ባለሁበት ሆኜ የፓርቲዬን ስራ እሰራለሁ፤ ስራ አስፈፃሚውን እሰበስባለሁ፤ ለሚዲያ መግለጫ እሰጣለሁ፤ በአጠቃላይ ፓርቲዬን ወክዬ እየሰራሁ ነው፡፡ ፅ/ቤት ግን መግባት አያስፈልገኝም፡፡
አንድ የፅ/ቤት ሰራተኛ ማህተም አላስረክብም ሲል አመራሩ እንዴት ማስቆም ይከብደዋል?
አመራሩ ምን ያድርግ?!
በህግ ጠይቆ ማህተሙን ማስመለስ አይችልም?
እሱ እንግዲህ ወደ ህግ እንሂድ ቢባል ይቻላል፤ ነገር ግን ወደ እነዚህ ተቋማት ብንሄድ ችግሩን የበለጠ ነው የምናሰፋው፡፡ የህግ አስከባሪ የሚባሉት ተቋማት ደግሞ እንደማይረዱን እናውቃለን፡፡ ከዚህ በፊት በተለያዩ ፓርቲዎች ላይ የተፈጠረውን አይተነዋል፡፡ ይሄ ሰውዬ ይሄን ያደረገበት የራሱ ምክንያትና አላማ ይኖረዋል፡፡
ለምንድነው ከኃላፊነት እንዲነሳ የተወሰነው?
በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ተወዳድሮ የፓርቲው የምክር ቤት አባል ሆኗል፤ በደንባችን መሰረት ደግሞ የም/ቤት አባል የሆነ ሰው የፅ/ቤት ኃላፊ ሆኖ መስራት አይችልም፡፡ ስለዚህ ይሄ ሰውዬ በራሱ ጊዜ ነው የፅ/ቤት ኃላፊነቱን የለቀቀው፡፡ እኔ አይደለሁም ልቀቅ ያልኩት፤ የፓርቲው ደንብ ነው እንዲለቅ ያስገደደው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የፓርቲው ማህተም ህገ ወጥ ስራ ቢሰራበትስ?
እንግዲህ ምን እናድርግ እኛ! ወይ ፍርድ ቤት ወይ ምርጫ ቦርድ መሄድ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የሚሆን አይደለም፡፡ ምርጫ ቦርድ ጣልቃ ገብቶ ፓርቲዎችን ለብዙ  ችግር ሲዳርግ ነው የምናውቀው፡፡ ስለዚህ ያለኝ አማራጭ —— ድብድብ ከመፍጠር በውጭ እየሰራሁ ፓርቲው ወደነበረበት የሚመለስበትን መንገድ ማፈላለግ ነው፡፡ እኔ ፓርቲው ውስጥ የገባሁት ለግብግብና በጠመንጃ ጉልበት ለመታገል አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ነገሩን ለመሸሽ በውጪ የምሰራው፡፡
ችግር ፈጥረውብናል የምትሏቸው ሰዎች አላማቸው ምንድን ነው ትላላችሁ?
እኔ የደረስኩበት ድምዳሜ፣ የእነዚህ ሰዎች አላማ ፓርቲውን ማዳከም ነው፡፡ ፓርቲው ስራውን እንዳይሰራ በማድረግ፣ የነበረውን ጠንካራ እንቅስቃሴ መግታት ነው፡፡
ፓርቲው ከመዳከሙ የተነሳ ለቢሮ ኪራይ የሚከፍለው በወር 18 ሺህ ብር አጥቷል እየተባለ ነው፡፡ ይሄስ እውነት ነው?
ሰማያዊ በብዛት በውጭ ሀገር በህጋዊነት የተመዘገቡ የድጋፍ ሰጪ ማህበራት አሉት፡፡ እነዚህ በድጋፍ ውስጥ ትልቅ ድርሻ አላቸው፤ነገር ግን በአደባባይ አባላት እየተዘላለፉ፣ ንቁ አባላት እየተባረሩ —– በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለሰማያዊ ገንዘብ ለማሰባሰብና ለመርዳት እንቸገራለን ብለው ያለቻቸውን ገንዘብ ከ3 ወር በፊት ላኩ፡፡ አንድ መቶ ሺህ ብር ነች፡፡ ከዚያ በኋላ አልላኩም፡፡ የማይረዱበትን ምክንያት፣ ፓርቲው እርስ በእርሱ እየተወነጃጀለና ስም እየተጠፋፋ በመሆኑ ነው ብለው በግልፅ ተናግረዋል፡፡ እውነትም ነው! ሰው ገንዘቡን የሚሰጠው ትግሉ እንዲሳካ፣ በአንድ አላማ ተሰልፈን እንድንታገል ነው፡፡ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች የሚፈልጉት ደግሞ ይሄ እንዳይሳካ ነው፡፡
ፓርቲው በእንዲህ ያለ ቀውስ ውስጥ መግባቱ አባላቶቻችሁንና ደጋፊዎቻችሁን ተስፋ እያስቆረጠ አይመስልዎትም?
አይ፤ አባላትን በተመለከተ አሁንም ቢሆን ስራ ለመስራትና በንቀት ለመሳተፍ ፍላጎታቸው እንዳለ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ለቅቄያለሁ የሚል ሰው አላየሁም፡፡ ዮናታንም ቢሆን ከኃላፊነቱ ነው እንጂ የለቀቀው ከፓርቲው አይደለም፡፡ የሚያሳዝነው ግን በእስር ላይ እያለ ከፓርቲው ተባረዋል የተባሉት 4 የፓርቲው አባላት መጀመሪያ የተወሰነው ውሳኔ ችግር አለበት ተብሎ በፓርቲው ይቀጥሉ ተብሎ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ በድጋሚ አባረናቸዋል ተብሏል፡፡ እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ሰው ሞራሉ ቢነካ ምን ይገርማል፡፡ እኔን ጨምሮ ቢሮዬን መጠቀም እስከማልችልበት ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ ነገሮችን እስካሁን ይፋ ሳናደርግ የቆየነው ለህዝብ ካለን ክብር የተነሳ ነው፤አባላትና ደጋፊዎቻችን በስነ ልቦና እንዳይጎዱ በማሰብ ነበር፡፡ ይሄ ነገር አሁንም ቢሆን መፍታት ካልተቻለ፣ ፓርቲውም አስፈላጊ የማይሆንበት ደረጃ ይደርሳል ማለት ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየጊዜው እርስ በርስ እየተጠላለፋችሁ ስትፈርሱ፣ ይደግፈናል የምትሉትን ህዝብ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይመስልዎትም?…
በተለይ ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ እንደዚህ መሆን-
አሁን እኮ ችግሩ “የእናንተ እንዲህ መሆን —” የሚለው ነገር ነው፡፡ እኔና የስራ አስፈፃሚ አባላት በሙሉ ልብና በሙሉ አቅም ነው እየሰራን ያለነው። ችግሩ ያለው ዲሲፒሊን ኮሚቴ የሚባለው ጋ ነው፡፡
የእኔ ጥያቄ የውስጠ ፓርቲ ችግራችሁን እንዴት በተረጋጋ መንገድ መፍታት አትችሉም ነው? የዲሲፒሊን ኮሚቴ ነው ችግር ፈጣሪ ካላችሁ ለምን አታስተካክሉትም?
ዲሲፒሊን ኮሚቴውን እንዲያስተካክል ለፈጠረው ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን እነዚህ ሁሉ አወዛጋቢ ውሳኔዎች ከመምጣታቸው በፊት ደብዳቤ  ፅፌያለሁ፡፡ እስከዛሬ የነበሩትን ድክመቶች አመላክቼ ጠንካራ ደብዳቤ ፅፌላቸዋለሁ፡፡ እንግዲህ ያንን ተመልክተው የእርምት እርምጃ ይወስዳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በሰማያዊ ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ በማንኛውም ፓርቲ ውስጥ የሚያጋጥም ተራ ግጭት ነው ብሎ ማለፍ ይቻላል?
አይቻልም፤ ምክንያቱም ይሄ ሆን ተብሎ ታስቦና ታቅዶ እየተሰራ ያለ ሴራ ነው፡፡
የቢሮአችሁ ቀጣይ እጣ ፈንታስ ምንድን ነው?
በኔ እምነት ገንዘብ አይጠፋም ብዬ አስባለሁ፤ ፓርቲው ከጠነከረ ብር ያገኛል፡፡ ነገር ግን በዚህ ችግር ከዘለቀ ገንዘብ ማግኘት አይችልም፤ያኔ ቢሮ አልባ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ፓርቲው የመፍረስ አደጋ ላይ ነው ማለት ይቻላል?
ህጋዊ ሰውነቱን የሚያጣ አይመስለኝም፡፡ እዚህ ሀገር የማይፈጠር ነገር የለም፡፡ ጉዳዩ ምርጫ ቦርድ ዘንድ ቢሄድ የሚፈጠረውን መገመት ቀላል ነው፡፡ ፓርቲዬን ከመፍረስ ለመታደግ  በምንችለው አቅም ጥንቃቄ እያደረግን ነው፡፡
ላለመበታተን ምን ዋስትና አላችሁ?
ምንም ዋስትና የለንም፡፡ እዚህ ሀገር ህግ ዋስትና አይደለም፤ ኢህአዴግ የፈለገውን ነገር ማድረግ የሚችልበት ሀገር ነው፡፡ እኛ ግን ለህሊናችን ተጠንቅቀን የምንችለውን ሁሉ እንሰራለን፡፡
በቀጣይ እንግዲህ ኦዲትና ምርመራ፣ እጣ ፈንታችሁን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል … እንዴት ትቀበሉታላችሁ?
ኦዲት ከዚህ በኋላ በእኛ ላይ መወሰን የሚችለው ነገር የለውም፡፡ ምክንያቱም ከሳሽ የተባለው ግለሰብ አልከሰስኩም ባለበት ሁኔታ ምን ውሳኔ ይመጣል? ክስ በሌለበት የምን ውሳኔ ነው የሚጠበቀው፡፡ ማን ከሶኝ ነው የሚፈረድብኝ? ኦዲት አሁን ላይ ምንም የሚመረምረው ጉዳይም ሆነ የሚያስተላልፈው ውሳኔ የለም፡፡ ከነሱ የሚጠበቅ ምንም ውሳኔ የለም፡፡
ፓርቲያችሁን ከቀውስ ለማዳን የምትወስዱት የመጨረሻ እርምጃ ምንድን ነው?
እንግዲህ የመጨረሻው መፍትሄ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ፣ ኦዲትና ምርመራ ኮሚሽኑ እየፈጠረ ያለውን ችግር አስረድቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ ነው። ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተን ችግሩን የፈጠረው አካል እንዲሻር ማስደረግ ብቻ ነው መፍትሄው፡፡
ጉባኤውን ለመጥራት ታዲያ ለምን ዘገያችሁ?
ጉባኤያችንን ያደረግነው በቅርቡ ነው፡፡ በድጋሚ መጥራት ከአቅም አንፃር አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው፡፡ አሁን ግን ችግሮቹ እያፈጠጡ ስለሆነ ጉባኤ መጥራቱ የግድ ይሆናል፡፡
ጉባኤው መቼ ይደረጋል?
ችግሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሆናል፡፡
በዚህ ዓመት ይሆናል?
አዎ የግድ ነው፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የወደፊት እጣ ፈንታ ምንድነው?
እርግጥ ነው ፓርቲያችን ችግር አጋጥሞታል፤ግን የፓርቲውን መሰረታዊ ነገር የሚጎዳ ነው ብዬ አላምንም፤ሆኖም የፓርቲውን ስራ እንዳንሰራ ተሰነካክለናል፡፡ ፓርቲው ጉባኤ ካደረገ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናከራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ ከተቃዋሚዎች ጋር በተወያዩበት መድረክ ላይ ያልተገኛችሁት ለምንድን ነው?
አልተጠራንም፡፡ የሚጠሯቸው ከኢህአዴግ ቀለብ የሚቆረጥላቸውን ነው፡፡ በአለም ታሪክ ተቃዋሚ ከገዢ ፓርቲ ቀለብ የሚቆረጥለት በኛ ሀገር ብቻ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment