Sunday, April 17, 2016

በጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ በዳዳ ገልቹ የሚባል ወጣት በመንግስት ታጣቂዎች መገደሉ ተነገረ – VOA

Badada Gelchu
በኦሮሚያ ክልል አልፎ አልፎ በተማሪዎችና በነዋሪዎች የሚካሄደዉ ተቃዉሞና የጸጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃ ምላሽም ቀጥሏል። በጉጂ ዞን ኦዶሻኪሶ ወረዳ መጋደር በተባለ መንደር ባለፈዉ ማክሰኞ በዳዳ ጋልቹ የሚባል ወጣት በመንግስት ሃይሎች መገደሉን የአካባቢ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ገልጸዋል። በወረዳዉ የሻኪሶ ከተማ አስተዳዳሪዎች የወጣቱን ሕይወት ማለፍ እንደሚያዉቁ ለወንጀሉ ማን ሃላፊ እንደሆነ እንደማያዉቁ ግን ገልጸዋል።
ባዳዳ ገልቹ ከዩኒቨርሲቲ በኢንጂነርግ ማለትም የምህንድስና ዲግሪ የተመረቀ ወጣት ነበር። ከተመረቀ በኋላ ስራ በማጣት ሲዋትት ቆይቶ የራሱን ስራ ፈጥሮ ለመስራት እቅድ ነበረው።
ፍቃድ ጠይቆ የአካባቢዉ ባለስልጣናት ስላልፈቀዱለት ወደ ግብርና ተመልሶ ይሰራ እንደነበር ዳንኤል ቦሩ የተባለዉ የመጋደር መንደር ነዋሪ ገልጿል። ባለፈዉ ማክስኞ ሰለተከሰተዉ የበዳዳ አሟሟትም ዳንኤል እንዲህ ይላል፣ “ምንም አይነት ተቃውሞ አልነበረም በዚያ ዕለት። ከወር በፊት የአል አሙድንን የኦኮቴ ፕሮጀክት ( ወርቅ እና ማዕድን ማውጣት ላይ የተሰማራ) እና የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመቃወም በከተማው ተደርጎ የነበረውን የተቃሞ ሰልፍ በማስተባበር ጠርጥረውት ነበር ከዚህ በፊት። የተገደለ ቀን ገን የእርሻ ቦታው ላይ ደቦ ነበረው። ስራ ጨርሰው ሲወጡ አወል የሚባል ሰውዬ ወዴት እንደሚሄድ ጠይቆት ወደ ቤቱ መሄዱን ሲያውቅ ብርሃኑ ከሚባል ደህንነት ጋር መንገድ ላይ ጠበቋቸው። አግአዚዎችም ነበሩ። ከደቦ የሚመለሱት ሰዎች ሲደናገጡ አትፍሩ እኛ እናንተን አንነካም የምንፈልገው ሰው አለ ብለው በዳዳን ቁም አሉት፣ በጥይት መቱትና ህብረተሰቡ ተኩሱን ሲሰማ ተሰበሰበ። ብዙ ጥይት ተኩሰው ሰው እንዲበተን አደረጉ። በዳዳ ወደ አደላ ወዩ ሆስፒታል ቢወሰድም እዛ ሲደርስ (ከምሽቱ 2፡30 አካባቢ) ህይወቱ አልፏል።” ብሏል።
ሌላ ጋሪ ሱጌ የተባለ የአይን እማኝ፣ በዳዳ ገልቹ በጥይት ከተመታ በኋላ ታጣቂዎቹ ታርጋ በሌለው መኪና ወደ አዶላ ከተማ እንደወሰዱት እና ወዲያው እንደሞት ገልጿል። በጥይት የተመታውም፣ አንገቱን ጭምር በርካታ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ መሆኑን አይቻለው ብሏል።
የሸኪሶ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ ጨሉቄ ዱካለ በበኩላቸው፣ የወጣቱን መሞት አምነው ማን እንደገደለው ግን አልተጣራም ብለዋል። “ሙሉ መረጃ የለኝም አንጂ በዳዳ የተባለው ልጅ በአዶ ሻክሶ መሞቱን ሰምተናል። ህይወቱ የጠፋው ደግሞ በፌደራል ሃይል ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ነው። እዚያ በወቅቱ ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ነው። እሱ ይግደለው ሌላ ሰው እኔ የተጣራ ነገር አላውቅኩም።” ብለዋል።
የኦዶ ሻኪሶ ወረዳ የአስተዳደር እና የደህንነት ሃላፊ አቶ ታደለ ኡዶም ስለ በዳዳ ገልቹ ሞት ተጠይቀው ነበር። የተባለው ሰው ተመትቶ መገደሉን እኛም እናውቃለን ብለዋል። ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው፣ ሙሉ መረጃ ልሰጥ የምችለው ምርመራው ሲጠናቀቅ ነው ካሉ በኋላ፣ ወጣት በዳዳን የገደለው ሰው የመንግሥት አካል ነው ወይ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፣ “እኛ በአጭሩ ልንነግርህ የምንችለው ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር መሆኑን ነው። መንግሥት ልኮት አይደለም ግድያውን የፈጸመው። የመንግሥት አካል ይሁን አይሁን ግን ምርመራው ሲያልቅ እናሳውቃለን” ብለዋል።
ወጣት በዳዳ ገልቹ የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስ እጩ ተወዳዳሪ ነበር። የአፋን ኦሮሞ ስርጭት ባልደረባችን ናሞ ዳንዲ ያጠናቀረዉ
Vm
P

No comments:

Post a Comment