ከ500 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዕለተ ስቅለትን እንዴት ታከብር እንደነበር በመጠኑ ሊያሳዩን ከሚችሉ መዛግብት አንዱ ‹ዜና ደብረ ሊባኖስ› የተሰኘው መዝገብ ነው፡፡ ዜና ደብረ ሊባኖስ በ1586 ዓም የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ አምስት ነገሮችን ይዟል፡፡ የደብረ ሊባኖስን ታሪክ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት እስከ ዐፄ ሰርጸ ድንግል ዘመን፤ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ጥንታዊ ሥርዓተ ማኅበር፤ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ጥንታዊ ሥርዓተ ጸሎት፤ በመጽሐፈ መነኮሳት መልክ የተጻፈ የልዩ ልዩ መነኮሳት አስደናቂ መንፈሳዊ ሕይወት እና በዐፄ ሰርጸ ድንግል ዘመን የተፈጸሙ አንዳንድ ሀገራዊ ኩነቶች፡፡
እስካሁን በተደረገው ጥናት ዜና ደብረ ሊባኖስ ሦስት ቅጅዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው በፓሪስ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት፣ በአንቶንዮ ዲአባዲ ስብስብ ውስጥ በቁጥር 108 ተመዝግቦ የሚገኘው፤ ሁለተኛው ከደብረ ጽጌ ማርያም የተገኘውና በማይክሮ ፊልም ተነሥቶ በEMML 7346 ተመዝግቦ የሚገኘው፤ ሦስተኛው ደግሞ በደቡብ ጎንደር ማኅደረ ማርያም ደብር የሚገኘው ቅጅ ነው፡፡ ከሦስቱም ቁልጭ ብሎ የሚነበበው የማኅደረ ማርያሙ ቅጅ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከምናገኛቸው ጉዳዮች አንዱ በቤተ ክርስቲያን በዓላት ስለሚደረጉ ጸሎቶችና የጸሎቱ ሥነ ሥርዓት አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ ሥርዓቶች በዘመን ብዛት ተረስተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ተጎርደዋል፡፡ የጥንቱን ከዛሬው ማስተያየትና የጎደለውን ለመሙላት፣ የተረሳውን ለማስታወስ፣ የተሳተውንም ለማቅናት መሞከር ብልህነት ነው፡፡ እስኪ ለምሳሌ ሥርዓተ ዕለተ ስቅለቱን እንየው፡፡
ደግሞም የዕለተ ስቅለት ሥርዓት (ወግ) ይህ ነው፡፡ (ጠዋት) በ3 ሰዓት ቤተ ክርስቲያንን በወርቀ ዘቦ ግምጃ ካስጌጡ፣ ሥዕላትንም በየመስቀያቸው ካስቀመጡ በኋላ የመጻሕፍት ንባብ በየተራቸው ይሁን፡፡ የስቅለቱንም ሥዕል በመካከል ያኑሩት፡፡ ሦስት ማዕጠንቶችንም በፊቱ ይስቀሉ፡፡ ሁለት ዲያቆናትም አንዱ በቀኙ ሌላውም በግራው የሐር መነሳንስ ይዘው፣ የሐር ልብስም ለብሰው፣ ራሳቸውም ተሸፍኖ ይቁሙ፡፡ እስኪመሽና የስቅለቱ ሥዕል እስኪነሣ ድረስም እንዲሁ ይሁኑ፡፡
ወዳነሣነው ነገር እንመለስ፡፡
የመዓልቱን ቅኔ አድርሰውም በጌታችን ምሳሌ ይገረፉ ዘንድ ወደ ምሥራቅ ይሂዱ፡፡ ይህንንም ፈጽመው ወደ መዓልቱ ቅኔ ይመለሱ፡፡ ያመስግኑ፣ የመዝሙረ(ዳዊትንም) ቃል ሃምሳውን በሦስት ሰዓት፣ ሃምሳውን በስድስት ሰዓት፣ ሃምሳውን በ9 ሰዓት ይድገሙ፤ በምሽትም ጊዜ የስቅለቱ ሥዕል ከተገነዘ በኋላ 150ውን ይድገሙ፡፡ መዝሙረ ዳዊትም በሰሙነ ሕማማት ጊዜ ይድረስ፡፡ አንደኛው በመንፈቀ ሌሊት፣ አንደኛው በነግህ፣ አንደኛው በ3 ሰዓት፣ በ6 ሰዓትና በ9 ሰዓት ሃምሳ ሃምሳ በሰሙነ ሕማማቱ ሁሉ አምስቱ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ይድረስ፡፡ በአንድ ቀንም ሦስት ጊዜ (ሙሉው መዝሙረ ዳዊት) ይድረስ፡፡ ሰኞ ዕለትና ማክሰኞ ዕለትም እንዲሁ እስከ ዓርብ ድረስ ይደረግ፡፡ በዕለተ ዓርብ ግን አራት ጊዜ(ሙሉው መዝሙረ ዳዊት) ይድረስ፡፡ በ3 ሰዓት፣ በ3 ቃል ‹ግፍዖሙ እግዚኦ ወጽብዖሙ እግዚኦ› በዜማ ይበል፡፡ ሕዝቡም በግራና በቀኝ ሆነው እስኪፈጸም ድረስ እየሰገዱ ይቀበሉት፡፡ የስቅለቱንም ሥዕል ይግለጡት፡፡ መገለጡም ሰባት ጊዜ ይሁን፡፡ አንደኛው ‹ግፍዖሙ› ሲባል፣ አንደኛው ወንጌል ሲነበብ፣ አንደኛው ‹በመስቀልከ ንሰግድ› ሲባል፣ አንደኛው በቀትር ወንጌል ሲነበብ፣ አንድ ጊዜም ‹አምንስቲቲ› ሲባል ነው፡፡ በመጨረሻ ሦስት ጊዜ ‹አምንስቲቲ› ይበሉ፡፡
ከዚያም ተነሥተው መልክዐ ወልድን ‹ሰላም ለጸአተ ነፍስከ› እስከሚለው ድረስ ይቀኙ፡፡ ከግብረ ሕማማትም በኋላ መጻሕፍትን ማንበብ ይቀጥሉ፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅና መጽሐፈ ምሥጢር፡፡ ነገረ ማርያምም ከሁለቱ መጻሕፍት ይቅደም፡፡ ዳግመኛም መጽሐፈ ዶርሆ፣ ርቱዐ ሃይማኖት፣ ተስፋ ክርስቲያንና መልእክተ አቃርዮስ ዘሀገረ ሮሐ ይነበቡ፡፡ በ9 ሰዓት በንባበ ወንጌል ሰዓት ሥዕለ ስቅለቱን አንድ ጊዜ ይግለጡት፣ አንድ ጊዜ ደግሞ በምሽት ሁለት ዲያቆናት ሥዕለ ስቅለቱን ይሸከሙት፤ ቄሰ ገበዙም ‹ንሰግድ ለከ ክርስቶስ ምስለ አቡከ ሔር ሰማያዊ› ይበል፡፡ የሚከተሉትም በንዑስ የእዝል ዜማ ‹ኪርኤ ኤላይሶን› እያሉ በአራት መዓዝን መቶ መቶ ጊዜ ስግደትን ከማብዛት ጋር ይቀበሉት፡፡ ቁጥሩም ሲመላ ሥዕለ ስቅለቱን ጎንበስ ያድርጉት፡፡ ያልብሱት፣ በስቅለት ሥዕል ላይም መጋረጃ ይጋርዱ፤ በራሳቸውም ተሸክመውት ‹ኪርኤ ኤላይሶን› እያሉ ወደ ቤተ መቅደስ ይግቡ፡፡ እያንዳንዳቸውም በቀኝ ገብተው በግራ ይውጡ፡፡ መንበረ ታቦቱንም ሦስት ጊዜ ይዙሩት፡፡ ከዚያም በመንበሩ እግር ሥር በከርሰ ሐመሩ ሥዕለ ስቅለቱን ያስቀምጡት፡፡ ደም ባለበት በችንካሮቹ ሁሉ የከርቤ ዱቄት ይጨምሩበት ዘንድ ይግለጡት፡፡ ሲጨርሱም በልብስ ይሸፍኑት፤ መጋረጃውንም ይጋርዱት፡፡
ከዚህ በኋላም ቄሱ ስላረፉት ወገኖች ይለምን፡፡ እርሱም ‹ብቋዕ እግዚኦ› ነው፡፡ ወደ መዓልት ቅኔም ይውጡና መዝሙረ ዳዊትን ፈጽመው ያንብቡ፡፡ መጽሐፈ ሕማማትንም ያስከትሉ፡፡ ሲፈጸምም ካህኑ ‹ተሰቅለ ወሐመ› ይበል፡፡ ቀጥሎም ‹ንሴብሖ› ይበል፡፡ አስከትሎም ‹እግዚኦ ኢትጸመመኒ› የሚለውን ያንብብ፡፡ ሕዝቡም ‹ለይሁዳ ለወልዱ ላዕለ ውሉደ ውሉዱ› ይበሉ፡፡ ከዚያ ደግሞ ‹ብጹዕ ብእሲ›ን እስከ ፍጻሜው ያንብብ፡፡ መብራቶችንም ሁሉ አጥፍተው ወደየቤታቸው ይሂዱ፡፡ በዚያ ሌሊትም መጽሐፈ አፈወርቅንና መጽሐፈ ምሥጢርን ያንብቡ፡፡ ደግሞም ዳዊትን ከወንጌልና ከጸዋትው ጋር እንደ ሰሙነ ሕማማት አድርገው ያንብቡ፡፡
በነጋም ጊዜ(ቅዳሜ) መኃልየ መኀልይን ያንብቡ፡፡ ቀጥለውም ‹ቅዱስ፣ ዘተወልደ፣ ወዘተጠምቀ፣ ወዘተንሠአ› ይበሉ፡፡ መዝሙረ ያሬድንም ያስከትሉ፡፡ ‹ገብረ ሰላመ› ከተባለ በኋላ አስቀድመው ከቤተ ክርስቲያን ይውጡና ዲያቆኑ ‹ስግዱ ለእግዚአብሔር› ይበል፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው የሊቃነ ጳጳሳትን ቡራኬ ያንብብ፡፡ ይህቺም ሥርዓት ዳግመኛ በርእሰ ዐውደ ዓመት እንዲሁ ትፈጸም፡፡ በፋሲካ ዋዜማ ዕለት ከሁሉ የሚበልጠው(ሊቅ) ራእየ ዮሐንስን በቀትር ጊዜ ያንብብ፡፡ የቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰዓት ሲደርስም ‹አሌዕለከ› በሚለው ፋንታ ‹ይትነሣእ እግዚአብሔር› የሚለውን ይበል፡፡ ‹ሐዳፌ ነፍስ› የሚለውን ግን አይበል፡፡ ወደ ቤታቸውም አይሂዱ፣ ነገር ግን ወንጌላትንና መዝሙራትን፣ ጸሎታትንም ሁሉ እያነበቡ በቤተ ክርስቲያን ይደሩ እንጂ፡፡ አንደኛውም ወንጌለ ዮሐንስን በመንበሩ ላይ ያንብብ፤ ከዚያም ቄሱ ሥዕለ ስቅለቱን ከማንሣቱ በፊት ይጠን፡፡ ካህናቱም አፈወርቅንና መጽሐፈ ምሥጢርን ያንብቡ፡፡ ከዚያም ሙሉውን መዝሙረ ዳዊት ከወንጌልና ከጸዋትው ጋር ልክ እንደ ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት አድርገው ያድርሱ፡፡
ያን ጊዜም ዲያቆኑ ከወንጌል በፊት ከመዝሙረ ዳዊት ‹ወተንሥአ እግዚአብሔር› የሚለውን ይስበክ፡፡ ሦስት ወንጌላትንም ያንብቡ፡፡ አንደኛው ወንጌልም ለቁርባን ሰዓት ይቆይ፡፡ በዕለቱም መምህሩ ይቀድስ፡፡ እርሱም ካልቻለ በዕለተ ዓርብ ወንጌሉን ያደረሰው ይቀድስ፡፡ በትንሣኤ ምሽትም ካህናቱ በረከት ለመቀበል ተሰብስበው ‹ተስኢነነ› እንዲሉ ሥርዓት አለ፡፡ ይህም ከሌለ ደግሞ ‹እግዚአብሔር ነግሠ› አለ፡፡ ከፋሲካ ዋዜማ እስከ ግብር ፍጻሜ ድረስ ቡራኬ አለ፡፡ ይኼውም ‹ግብር ዘወሀብከኒ ዘውእቱ ጸጋ ዘአብ› የሚለው ነው፡፡ ከጾሙ እስከ ወርኃ ፋሲካ የሚሆነውን ‹ሥርዓተ ከኒሳ› ተፈጸመ፡፡ ነገር ማብዛቱን ትተን በአጭሩ አቀረብነው፡፡
No comments:
Post a Comment