የደም ባንክ በመኪና አደጋ ብዛት የደም እጥረት ያጋጠመው መሆኑን አስታወቀ
በኢትዮጵያ በየዕለቱ የሚሰቀጥጡ የመኪና አደጋዎችን መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤፍ ኤም ሬዲዩ ጣብያዎችም በየማለዳው ከተለያዩ አካባቢዎች መረጃዎችን በማጠናቀር የሚጠብቋቸውን የትራፊክ ባለሞያዎች በማስተናገድ የደረሱትን የመኪና አደጋዎች ለህዝብ ያስተላልፋሉ፡፡
የህክምና ባለሞያዎችና የትራፊክ ፖሊሶች በየጊዜው ከሚከሰቱ የመኪና አደጋዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩ በመሆናቸው በአደጋዎቹ ስለሚደርሱ የህይወት መጥፋትና የአካል መጉደል መረጃዎችን ሊሰጡም ይችላሉ፡፡በመኪና አደጋ በአብዛኛው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ህይወታቸው የሚያልፈው በቀጥታ ከአደጋው ጋር በተያያዘ ምክንያት አለመሆኑን ሲናገሩ መስማትም ልብን ያርዳል፡፡ተጎጂዎች በአብዛኛው የሚሞቱት በአደጋው ወቅት ብዛት ያለው ደም ስለሚፈሳቸውና ይህንን ደም መተካት የሚያስችል አቅም በደም ባንክ ውስጥ ባለመኖሩ ነው ይላሉ፡፡
ይህንን ችግር በመቅረፍም ህይወት የማትረፍ ኃላፊነት የተጣለበት ብሄራዊ የደም ባንክ ለለጋሾች ህይወትን እንታደግ የሚል ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡እያዳንዱ ጤናማና ዕድሜው ከ18 -65 የሚደርስ ዜጋ በአመት ውስጥ ለሶስት ጊዜያት ደም በመለገስ ህይወት እንዲያተርፍ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
በቅርቡ ብሄራዊ የደም ባንክ ከጋዜጠኞችና ባለሞያዎች ጋር ባደረገው ውይይት የደም ባንኩ ዳይሬክተር ዶክተር ሐብተማርያም ደሞዝ በአደጋ ወቅት ደም የሚፈሳቸውን ተጎጂዎች ህይወት ለመታደግ ደም መለገስ ጊዜ የማይሰጠው ሰብዓዊ ተግባር ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
በየዕለቱ የሚከሰተው የመኪና አደጋ ለደም ባንኩ ፈተና መሆኑን የተናገሩት ዶክተሩ ህይወት ለማዳን ሁልግዜም ባንካቸው ደም ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ነገር ግን አደጋው በመቀጠሉና የተጎጂዎቹም ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በየጊዜው የተጠየቀውን ደም ማቅረብ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አለም አቀፉ የጤና ድርጅት ህይወትን ለመታደግ የደም ጠብታ አስፈላጊ ነው በሚል መርሁ መሰረት ከ90 ሚልዩን ህዝብ በላይ በሚገኝባት ኢትዮጵያ በደም ባንክ ውስጥ ከአንድ ሚልዩን በላይ የደም መጠን መኖር የሚገባው ቢሆንም በባንኩ ውስጥ ያለው የደም መጠን ከ128.000 እንደማይበልጥ ዶክተሩ አስታውቀዋል፡፡‹‹የሚያስፈልገንን ያህል ደም ለማግኘትም ብዙ መስራት ይጠበቅብናል››ይላሉ፡፡
ለደም ባንክ ከ1989 ጀምረው ለ76 ጊዜያት የሰጡት የ50 ዓመቱ አቶ ሰለሞን በየነ ‹‹ህይወትን በደሜ መግዛት ለእኔ የሚሰጠኝ ደስታ የተለየ ነው፡፡በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ለህሊናዬ ነው፡፡ደም አዘውትሬ በመስጠቴም ለአፍታ እንኳን ተጸጽቼ አላውቅም››ብለዋል፡፡
ደም መስጠት ህይወትን መስጠት ነውና ህይወትን ለሚፈልጓት እንስጥ የእኛም መልእክት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment