Thursday, April 21, 2016

ኑሩ ቱርኪ – የነዳያን አባት | የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ሕብረት




nuru TurkiApril 20, 2016
በወያኔ እየተመራ ያለው መንግስት ባሰማራቸው የጥፋት መልእከተኞች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል መልኩን ቀይሮ እየባሰበት ሄዷል። በወገን ላይ የሚፈፀመውን ሰቆቃ በመቃወም ለፍትህና ለነፃነት የቆሙትን ንፁሐን የቁርጥ ቀን ልጆችን በሸፍጥ በታጀበ ውሃ በማይቋጥርና ሐቅ አልባ በሆነ ከገለባ የቀለለ የሐሰት ክስ መስርቶባቸው ዘብጥያ ተጥለው እየተንገላቱ የሃሰት ፍርድ በመጠበቅ ላይ ናቸው። ብዙዎቹም መንግስት ባሰለጠናቸው አባይ ምስክሮችና ከእውነት አፈንግጠው በሚዘገንን ሁኔታ ወደ ላሸቀ የሞራል ዝቅጠት በተንሸራተቱ ዳኞች አድሏዊ ፍርድ ተበይኖባቸው በወህኒ ቤት የሰቆቃ ሕይወት እየገፉ ነው።
በቅርቡም ከሕዝበ ሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አንዱ የሆነውና የ7 ዓመት እሥር ተፈርዶበት በዝዋይ ማረሚያ ቤት በሚገኘው በጀግናው ወንድማችን ኑሩ ቱርኪ ላይ የመግደል ሙከራ ተደርጎበታል። በሚያከናውናቸው የግብረ ሠናይ ሥራው “የየቲሞች ወይም የነዳያን አባት” እየተባለ በሕዝብ የሚጠራው ሩህሩሁ ኑሩ ቱርኪ የመግደል ሙከራው የተደረገበት በእሥር ቤት መሆኑና ድርጊቱንም የፈፀመው በማረሚያ ቤት በእሥረኞች ላይ ክትትል ለሚያደርጉት የመንግስት ሰላዮች መለያ በሆነው “አጥቋሪ” በሚል ስያሜ በሚታወቅ እስረኛ ስለሆነ የመንግስት እጅ እንዳለበት መገመቱ አስቸጋሪ አይሆንም።
በወያኔ እሥር ቤቶች በእስረኞች ላይ ጉዳት ማድረስ አዲስ ክስተት አለመሆኑን ቀደም ሲል የተፈፀሙትን ተመሳሳይ የሆኑ አሳዛኝ ተግባራትን መለስ ብሎ መቃኘቱ ጥሩ አመላካች ይሆናል። ወጣቱ ወንድም ሙባረክ ይመር በእስር ቤት ህክምና እንዲደረግለት ጠይቆ በመከልከሉ ከብዙ ስቃይ በኋላ የዘገየ መርፌ ሲወጋ ህይወቱ ወዲያው ተቀጥፏል። ሌላው ወጣት ወንድማችን የደህንነት መርማሪዎች ባደረሱበት ከባድ ድብደባ አካለጎደሎ በመሆኑ ፍርድ ቤት ለቀጠሮ የሚመላለሰው በሰው ጀርባ ታዝሎ መሆኑ በአደባባይ ታይቷል። የደህንነት ሰራተኞች አቦ በቀለ ነጋአ የተባሉ የኦሮሞ መብት ተከራካሪን ከደበደቡ በኋላ ከቤት እንዳይወጡና ለሚዲያ እንዳይናገሩ አስጠንቅቀው የተባለውን ከጣሱ ግን “እንገልሃለን ወይ በመኪና ገጭተን ፓራላይዝ እናደርግሃለን” ማለታቸው የወያኔ መንግስት የቱን ያህል ሕዝብን የማስፈራራትና የማሸበር ተግባር ላይ ተጠምዶ እንደሚገኝ ያሳያል። ዛሬ በኢትዮጵያ
በታሰረውና ባልታሰረው መካከል ያለው ልዩነት በጣም እየጠበበና ድንበሩ አልለይ እያለ መጥቷል።
እስረኖችን ምግብ መከልከል፣ በቂ ህክምና እንዳያገኙ ማድረግና ቤተሰብ እንዳይጠይቅ ማገድ ታሣሪዎችና የታሳሪ ቤተሰቦችን ለማሰቃየት ዘረኛው የወያኔ መንግስት ሙጥኝ ብሎ የያዘው የክፋቱ መገለጫ ጎዳና ነው። የሥልጣን ዘመኑንም ለማረዘም ከዚህ የከፋ ተግባር ከመፈፀም እንደማይመለስ መጠበቅ ብልህነት ነው።
ሥልጣን ጠመጃና ገንዘብ በእጃችን ነውና ዛሬ ቀኑ የእኛ ነው በሚል እብሪትና ጭካኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ እየዘረፉና እየጎዱ መሽቶ በነጋ ቁጥር ዛሬ የእኛ ነው የሚሉት ቀን የእነሱ ባልሆነ የሕዝብ ቀን እንደሚተካ የሚጠራጠር ሰው ሊኖር አይችልም።
ግፈኞች የሚዋረዱበት፣ ሕዝብ አንገቱን የሚያቀናበትና የነፃነት ትንፋሽ የሚተነፍስበት ቀን ርቆ የሚታየው ለአምባገነኖች ብቻ ነው። በወያኔ መንግስት የፍርሃትና የሽብር ጀልባ እየተንገላታ ያለው የአገራችን ሕዝብ ግን ያቺን ቀን በቅርብ ርቀት እየተመለከታት ነው።
በኢትዮጵያ ሙስሊም መሪዎችም ሆነ በየእስር ቤቱ ታጉረው በስቃይ ላይ በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ በሙሉ ለሚደርሰው ማንኛውም የአካል ጉዳትም ሆነ የህይወት መጥፋት የወያኔ መንግስት እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ህብረት “የየቲሞች አባት” በሆነው በወንድም ኑሩ ቱርኪ ላይ የተፈፀመውን የመግደል ሙከራ በጽኑ እንደሚያወግዝና የወያኔን መንግስት በሃላፊነት እንደሚጠይቅ ያረጋግጣል።
ትግላችን እስከድል ደጃፍ ድረስ በአላህ ፈቃድ ይቀጥላላል!
አላሁ አክበር!
የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ሕብረት
Share0  93  0 



No comments:

Post a Comment